✍ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር
በዚህ በመንገድ ዳር ዝምታዬ ውስጥ ሆኜ፣ የኮቴያችሁን ድምፅ እሰማለሁ። አውቃለሁ፤ ሁላችሁም ወደ የትም እየተጣደፋችሁ ነው። አንዳንዶቻችሁ በብርሃን ውስጥ እየተጓዛችሁ እንደሆነ ታስባላችሁ፣ ሌሎቻችሁ ደግሞ እንደ እኔው በጨለማው ግርጌ ተቀምጣችሁ የሚመጸውታችሁን ተስፋ ትጠብቃላችሁ።
እኔ ግን ዛሬ ሳንቲም አልለምናችሁም። ይልቁንም ለነፍሳችሁ የሚሆን አንድ ታሪክ እንድሰጣችሁ ጥቂት ደቂቃዎችን እንድትመጸውቱኝ እማጸናችሁ ዘንድ እጄን ዘርግቻለሁ። ይህ ታሪክ ስለ እይታ ሳይሆን ስለ ማየት ነው፤ ስለ መቆም ሳይሆን ስለ መነሳት ነው፤ ስለ አሮጌ ልብስ መጣልና ስለ አዲስ ማንነት መጎናጸፍ ነው።
ታሪኬን ስተርክላችሁ በቃላት ድርደራ ብቻ ሳይሆን፣ በልባችሁ ጆሮ እንድትሰሙኝ በትዕግሥት እጠብቃችኋለሁ። ምክንያቱም እኔ የማወራው ስለ መራቆት ክብርና ስለ ጨለማው ምስጢር ነው። ይህ ጉዞ ከኢያሪኮ አቧራ ተነስቶ እስከ ቀራንዮ መስቀል ስር ድረስ ይወስደናል—እዚያም እውነተኛው ማንነቴ ማን እንደሆነ ትረዱታላችሁ።
እስከዚያው ግን፣ ከመንገዱ ዳር ተቀምጬ በፍቅር እጠብቃችኋለሁ። እስካሁን ካላችሁበት ፍጥነት ገታ ብላችሁ፣ ይህንን የነፍስ ጩኸትና የብርሃን ጉዞ እንድትከታተሉኝ በአክብሮት እጋብዛችኋለሁ።
በመጨረሻው ገጽ ላይ ማንነቴን እስክገልጥላችሁ ድረስ፣ የዝምታዬንና የጩኸቴን ምስጢር አብረን እንፈትሽ።
እንደ መግለቢያ፦
ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከመቀመጥ ወደ መጓዝ፣ ከባርነት ወደ ነፃነት የሚደረግ ጉዞ በአንድ ጀምበር የሚፈጸም ክስተት ሳይሆን በነፍስ ጓዳ ውስጥ የሚብላላ ረቂቅ ሂደት ነው። ይህ ተከታታይ ጽሑፍ፣ በታሪክ አቧራ ውስጥ ተቀብሮ የኖረን የአንድ ምስኪን ሰው ሕይወት በዓይን ብሌን እይታ ብቻ ሳይሆን በነፍስ መረዳት ጥልቀት ይመረምራል።
አንባቢያን ሆይ፤ ይህን ታሪክ ስታነቡ የዚያን ሰው ድምፅ ብቻ ሳይሆን የራሳችሁን የውስጥ ጩኸት ትሰሙበታላችሁ። በዚያ መንገድ ዳር የወደቀው ያ አሮጌ ልብስ የእያንዳንዳችንን ትላንትና ይወክላል። በመስቀሉ ስር የፈሰሰው ያ ብርሃንም የሁላችንንም ነገ ይተነብያል።
ታሪኩ ደረጃ በደረጃ ሲተረክ፣ በቃላት ረቂቅነትና በሃሳብ ልዕልና የታጀበ ነው። እያንዳንዱ ክፍል የራሱ የሆነ የዝምታና የጩኸት ምት አለው። ስለዚህም፣ ይህንን የነፍስ ጉዞ በትዕግሥት እንድትከታተሉትና በፍቅር እንድታጣጥሙት እጋብዛችኋለሁ። ምክንያቱም እውነተኛ ብርሃን የሚገኘው ሮጦ ለሚቀድም ሳይሆን፣ በጽናት ለሚጓዝ ነው።
የኢያሪኮ ፀሐይ እንደ ጋለ ናስ ቆዳዬ ትፋጃለች። ነገር ግን ለእኔ ብርሃን የሙቀት እንፋሎት እንጂ የሚታይ ነጸብራቅ አይደለም። ከአቧራማው መንገድ ዳር ተቀምጬ፣ የሰዎችን ኮቴ እና የሀዘን ትንፋሽ እለካለሁ። እዚህ ጋር እኔ የቆሻሻና የጥላቻ ተረፈ ምርት ነኝ፤ የሚመጸውቱኝ ሰዎች እንኳን የሚጥሉልኝን ሳንቲም የሚያዩት እንደ ግዴታ እንጂ እንደ ርኅራኄ አይደለም።
በውስጤ ግን አንድ ትልቅ ዓለም አለ። ዓለምን የማየው በዓይን ሳይሆን በድምፅ ሞገድና በዝምታ ጥልቀት ነው። ዙሪያዬን የከበበኝ ጨለማ ለእኔ መቃብር ሳይሆን፣ የፈጣሪን የሹክሹክታ ድምፅ የምሰማበት "ቅድስተ ቅዱሳን" ነው። ሰዎች በዓይናቸው በሚያዩት ነገር ተታለው ሲዳክሩ፣ እኔ ግን በመታወር ውስጥ የሚገኘውን ፍጹም እውነት አያለሁ።
ያ ቀን ግን የተለየ ነበር። አየሩ በጭንቀትና በተስፋ ተሞልቷል። የመንገዱ መንቀጥቀጥ የአንድ ትልቅ ኃይል መምጣትን ይናገራል። "ማነው?" ብዬ አልጠየቅኩም፤ ምክንያቱም ነፍሴ ቀድማ አውቃዋለች። የሚመጣው እርሱ ነው—የዘመናት ናፍቆት፣ የታሪክ ማጠንጠኛ፣ ከዳዊት የዘር ግንድ የበቀለው የጽድቅ ፀሐይ።
ዙሪያዬ ያሉ ስጋዊ አይኖች "ዝም በል!" ብለው ገሰጹኝ። እነርሱ የሚያዩት ልመናዬንና አቧራዬን ብቻ ነው። እኔ ግን የማየው የእርሱን መለኮታዊ ማንነት ነው። አይኖቼ ባይከፈቱም፣ ልቤ ግን ከሚታየው ዓለም ባሻገር ያለውን የሰማይ ደጅ ተመልክቷል። "ማረኝ!" ብዬ ስጮህ፣ ምህረት የፈለግኩት ስለ ዓይኖቼ መከፈት ብቻ አልነበረም፤ በጨለማ ውስጥ ሆኜ ያየሁትን ያንን ብርሃን ለመጨበጥ እንጂ።
አጠገቢ ሲደርስ፣ እርሱ ቆመ። የዓለም ሩጫ በእኔ ጩኸት ምክንያት ተገታ። ጊዜ ቆመ። ሰዓት መቁጠር አቆመ።
ልብሴን ጣልኩት። ያ የቆየ ማንነቴ፣ የመከራዬ ምልክት፣ የጭለማዬ መጋረጃ ነበር። ወደ እርሱ ስጠጋ የተሰማኝ ስሜት በቃላት አይገለጽም። እርሱ "ምን ላድርግልህ?" ሲለኝ፣ ጥያቄው የፈተና ሳይሆን የፍቅር ጥያቄ ነበር። እኔም "አይ ዘንድ!" አልኩት። ይህ "ማየት" ግን የቀለማትን መለየት ብቻ ሳይሆን፣ የተሰወረውን ምስጢር የመረዳት ናፍቆት ነበር።
ብርሃን ወደ እኔ መጣ። መጀመሪያ ያየሁት የፊቱን መለኮታዊ ግርማ ነበር። ያኔ ተረዳሁ፤ እውነተኛ አይነ ሰውርነት ዓይን ማጣት ሳይሆን፣ እርሱን እያዩ አለማወቅ መሆኑን።
ይቀጥላል.......
0 Comments