ልጆቻችንን ለባርነት የምንሸጣቸው ክፉ ወላጆች እኛ ነን!


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

“ጾታዊ ጥቃት የበዛው፣ እኩልነት፣ መብትና ነፃነትም የጠፉት በወንዱ ያጠፋቸውም ወንዱ” እያልን ባሳደግንበት ትርክት፤ ወኔያቸውን ሰልበን፣ ራሳቸውን አስጠልተን፣ ኤርስ በእርስ አጣልተን፣ ለባርነት አሳልፈን፣ የምንሸጣቸው እኛ ነን!

ዛሬ በየቤታችን የምናሳድገው፣ በትምህርት ቤቶቻችን የምናስተምረው ትውልድ ወኔ-ተፈጥሮው፣ ወንድነት መክሊቱ በቁም እየተሰለበ ይገኛል። ይህ ስልበት ደግሞ የሚፈጸመው በባዕድ ወራሪ ብቻ ሳይኾን፣ “ለልጆቼ የተሻለ ሥልጣኔና እውቀት እሰጣለሁ” በሚል ስም ራሳችንን በካድን ወላጆች እጅ ነው።

ልጆቻችንን ገና በእንቦቀቅላነታቸው መርዝ እየጋትን፣ ነገ ሀገርና እምነት፣ እሴትን የሚረከቡ አርበኞችን ስናጣ፣ አድርባይ ባንዳዎችንም በቤታችን ስናፈራ፣ ለባርነት የሚሰለፉ “ምስኪን ጃንደርባዎችን” ስናገኝ “ከየት የመጡ ማን የዘራቸው ናቸው” አንበል።

ልጆቻችንን ገና ከጠዋቱ “ጾታዊ ጥቃት፣ እኩልነት፣ መብትና ነፃነት የጠፉት በወንዱ፤ ያጠፋቸውም ወንዱ ነው” የሚል ትርክት እንግታቸዋለን። ይህንን ግፍ ፈጻሚው ደግሞ “አባወራው” እንደኾነ ደጋግመን እንነግራቸዋለን። በፊልምና በድራማ አባወራነትን ቀልደንበትና ኮንነነውም እንስልባቸዋልን።

ወንዱ ልጅ ወንድ ሆኖ በመፈጠሩ ብቻ “ወንጀለኛ” እንደኾነ፣ ተፈጥሮውም “በዝባዥነት፣ ጨቋኝነትና በዳይነት” እንደኾነ ተደርጎ ሲሰበክ፤ በራሱ ማንነት ላይ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲያድርበት እናደርገዋለን። በራሱ የሚተማመን አባወራ ሳይኾን፣ በራሱ የሚያፍር ጃንደርባ ትውልድ የምንፈጥረው እኛ ነን!

በዚህ የተመረዘ ትርክት ውስጥ ያደገ ወንድ ልጅ፣ ተፈጥሯዊ ወኔውን፣ ድፍረቱንና እልሁን እንደ “ነውር” ማየት ይጀምራል። “ጥሩ ወንድ” ለመባል ሲል ማንነቱን ይሰውራል፣ ወንድነቱን ይሰልባል፤ ግርማውን ይጥላል።

አንድ ልጅ “ወንድ ኾኜ መፈጠሬ ሌሎችን ለመጨቆን ነው” የሚል ትረካ እየተጋተ ካደገ፣ በራሱ ማንነት ላይ ከፍተኛ የጥያቄ ምልክት ይፈጥራል።

“ወንድ መኾን ጥፋት ነው” የሚል የጥፋተኝነት ስሜት ስለሚሰማው፣ ተፈጥሯዊ ኃይሉንና ወኔውን እንደ ነውር ማየት ይጀምራል። ይህ ደግሞ ለራሱ ያለው ግምት የወረደ እንዲኾን እንዲጠላውም ያደርገዋል።

ራሱን እንዲጠላ የተገደደ ትውልድ ደግሞ የራሱ አቋም ሊኖረው አይችልም። እንዲህ ዓይነት ወጣት ነገ የቤተሰብ መሪ፣ የሀገር ጠባቂና የእሴት ተሟጋች መኾን አይችልም። ወኔው የተሰለበ ወንድ ለጠላት ወረራና ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለም እጅግ አመቺ ይኾናል።

ወንዱን እንደ “አውሬ” እና አባወራነትን እንደ “ጨቋኝ መዋቅር” አድርገው እንዲያዩ የተገደዱ ልጆች፣ “ጥሩ ወንድ” ለመባል ሲሉ ተፈጥሯዊ የወንድነት ጠባያቸውን (ድፍረትን፣ ቆራጥነትን፣ መሪነትን...) ኾን ብለው ይጠየፋሉ ይደብቃሉም።

ተቀባይነት ያጡለት ወንድነት ተፈጥሮአቸውን ደብቀው በማኅበረሰባቸውና በቤተሰባቸው ተቀባይነትና ይኹንታን ለማግኘት ሲሉ “እንከፍ ምስኪን” እና “ጃንደርባ” የኾነ፣ ለባርነት የተመቸም ዜጋ ይኾናሉ።

አባወራነት የጭቆና መገለጫ እንደኾነ እየሰማ ያደገ ልጅ፣ ነገ አድጎ የቤተሰብ መሪ የመኾን ፍላጎት አይኖረውም። ኃላፊነትን ከመሸከም ይልቅ የሚሸሸው “ተከታይና ተላላኪ” መኾንን ይመርጣል። ይህም ጠንካራ አባቶች የሌሉበት፣ ጠባቂ ያጣና መሠረቱ የላላ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል።

በተፈጥሮው በሰውነቱ የሚሰማው ወንድነት ስሜቱ እና በማኅበረሰቡ የሚነገረው “በዳይ ወንድነቱ” እርስ በእርስ ሲጋጩበት፣ ልጁ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ቀውስ ውስጥ ይገባል። ይህ ግራ መጋባት ለተለያዩ የባሕርይ ለውጦች መዛባቶችና ለተሳሳቱ የጾታ ግንዛቤዎች በር ይከፍታ፤ በዚያም ወንድነቱን ጠልቶ ሴትነትን ይናፍቃል።




በተጨማሪም በጾታዎች መካከል የጥልና የጥርጣሬ ግድግዳ የምንገነባውም እንዲሁ ነው። ወንዱን “በዳይ”፣ ሴቷን ደግሞ “ተበዳይ” አድርገን በመፈረጅ፣ በመካከላቸው ያለውን ተፈጥሮአዊ መደጋገፍና መሳሳብ እናጠፋዋለን። ይህም ቤተሰብን ያዳክማል።

ቤተሰብ የላላበት ማኅበረሰብ ደግሞ ለባርነት የተጋለጠ ነው። ቆፍጣናነት፣ ቆራጥነትና ጽኑነት በሌለበት ስብእና ውስጥ፣ የሚጫንን ማንኛውም ጨቋኝ ሕግ መሞገትና መቃወምም አይቻልም ።

ወኔው የተሰለበና በራሱ ማንነት ላይ ጥርጣሬ ያለው፣ ተፈጥሮውንም የተጠየፈ ትውልድ፣ የትኛውንም ዓይነት ባዕድ ብያኔ ያለ ምንም ተቃውሞ ይቀበላል።

አውዳሚ ሕጎችንና ባዕድ እሴቶችን ለመቃወም የሚያስችል ድፍረትና ጽናት ስለማይኖረው፣ ለጠላትና ለሆዳደሮች ፍላጎት በቀላሉ የሚንበረከክ ይኾናል።

ይህ ሁሉ በአጋጣሚ የመጣ ሳይኾን ኾን ተብሎ በእቅድ የኾነ ነው። ጠላት የትውልዱን እሴትና እምነት ለመለወጥ ሲፈልግ፣ አስቀድሞ ሊቃወማቸው የሚችለውን ወንድ ወኔ ይሰልቡታል።

እኛም በየመገናኛ ብዙኃኑ የሚቀርቡትን ወንድነትን ከተፈጥሮው አባወራነትንም ከእሴቱ ለይተው የሚያስተምሩትን “ሆዳደር ሊቃውንት” እየሰማን፣ ልጆቻችንን ለባርነት አሳልፈን እንሸጣለን። ስልበት፣ መኮላሸት ድሮ በአካል እንደሚደረገው ሁሉ፣ ዛሬ በልጆቻችን ሥነ-ልቦና ላይ እየተፈጸመ ይገኛል።

እንዲህ ዓይነት ትምህርት የሚጋቱ ልጆች፣ ነገ ሀገርን የሚረከቡ አርበኛ አባወራዎች ሳይኾኑ፣ ለባርነት የሚሰለፉ ምስኪን ጃንደርቦች ነው የሚኾኑት።

ይህም “አባወራነትን” ለማጥፋትና ትውልዱን ያለ መሪ፣ ያለ ጠባቂ ለማስቀረት የሚፈጸም የረቀቀ የባህል ወረራ ነው። በዚህም ወረራ የእኛ የወላጆቻቸው ፈቃድ አልያም ቸልተኝነት አለበትና ከተጠያቂነት አናመልጥም።

በዚህ ሁሉ ላይ በቤቱ አባቱ ሲናቅ፣ ሲገፋና በፍቺ ሲባረር ላየው፣ ከእናቱ ጋር ብቻ አልያም “ለማዳው የቤት እንሰሳ” ከተደረገው አባቱ ጋር ለሚያድግ ወንድ ልጅ ይህ እንዴት እንደሚከፋበት አስተውል።

Post a Comment

0 Comments