ቤተሰቡን፣ ማኅበረሰቡን ሊታደግ ላለው አባወራ በጠንካራ ስብዕና በሚገነባው ቤቱ ትውልዱ ከጠላትና ከሆዳደሮች የጥፋት ትርክት ይመሸግበታል!
በዘመናችን ትልቁ የአርበኝነት ግንባር በእያንዳንዳችን ቤት ደጃፍ ላይም ይገኛል። ሀገራችን በጠላት የመረታቷ፣ ትውልዳችን በግዞት የመጋዙ ሽንፈት ከእያንዳንዳችን ቤት ሽንፈት ይጀምራል።
አርበኛው አባወራ የቤቱ ራስ፣ የትውልድ ዘበኛ እንደመኾኑ፣ በጠንካራ ስብዕና የሚገነባው ቤተሰብ ለሀገርና ለማኅበረሰቡ ብቸኛው ዋስትና ነው።
ዛሬ ትውልዱን “ልብ-አልባ” ለማድረግ የሚሰለፉ የባዕዳን ትርክቶችና በሊቃውንቱም የሚነግዱ የሆዳደሮች ሸፍጦች የሚሰበሩት፣ አባወራው የቤቱን ደጃፍ በእሴትና በማንነት ቀርጾ ሲያትመው ነው።
ይህ ምሽግ በድንጋይና ከሲሚንቶ፣ በአሸዋና በጠጠር ሳይኾን ከጽኑ የሞራል ልዕልና፣ ከኢትዮጵያዊ እሴትና ሕያው ከኾነ ክርስትና የሚገነባ የማይበገር የትውልድ መጠለያ፣ መሸሸጊያ ነው።
ይህንን የበለጠ ለመረዳት “ከእኛ ይልቅ ቴክኖሎጂውን በቀላሉ የሚያገኙ፣ ብዙ የተማረ ማኅበረሰብ ያላቸው፣ በፖለቲካዊ አስተዳደር የዘመኑ ምዕራባውያን ማኅበረሰባቸውን ላጠፋ ትርክት እንዴት ተሸነፉ?” ብለን ልንጠይቅ ይገባል።
በተለይም እንደ እንግሊዝ (UK) ያሉ ጥንታዊ አባወራዊ ክርስትና የነበረራቸው ማኅበረሰቦች ውድቀት ለኢትዮጵያ ትልቅ ማስጠንቀቂያ፣ ማስተማሪያም ነው።
እነርሱ የተሸነፉት በጠላት ጦር ሳይኾን፣ በቤታቸው ውስጥ የነበረውን የአባወራውን የቤተሰብ ምሽግ በገዛ እጃቸው በማፍረሳቸው ነው።
ይህንንም ደግሞ ያደረጉት አስቀድመው ባፍጢም ወድቀው፣ ከጠላት ተሻርከው፣ መርዘኛ ልብ አጥፊ ትምህርትን ለትውልዱ የጋቱ አስመሳይ ሆዳደር ሊቃውንቱ ናቸው።
ክርስትናን በታላላቅ ካቴድራሎች ውስጥ የታጠረ “የደረቅ ወግ” አድርገው ለታይታና ይኹንታ አቅብጠው፣ የቱሪስት መስህብ እንዲኾን፣ ገቢ መሰብሰቢያ ገንዘብ ማተሚያ አድርገውት አለፉ።
አባወራውም የቤቱ “መሪ፣ ጠባቂና ቀራጭ” እንዳይኾን “ገቢ አምጪ” ብቻ ኾኖ ከቤት እንሰሳት እንዳንዱ አልያም ከቤት እቃዎች እንዳንዳቸው እንዲቆጠር፦ እንከፍ ምስኪን፣ ስልብ ጃንደርባ እንዲኾን በአጉል መንፈሳዊነት በጾታ እኩልነት፣ መብትና ነፃነትም ጨርሰው ወኔውን ሰለቡት፣ አኮላሹት!
በዚያም ያለ ጠባቂ የቀረውን ትውልድ የደረሰው ቴክኖሎጂው አግኝቶት የጥፋትን መርዝ ወደ ልባቸው የሚያስርጽ መሣሪያ ኾነ እንጂ ሊታደጋቸው አልቻለም።
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ጥንታዊ፣ አርበኛዊ ማኅበረሰብ ከእነርሱ ውድቀት የምትማረው መራር እውነት አለ። እእሱም “ውድቀት የሚጀምረው ከአንተ እና ከእኔ ቤት ውስጥ” መኾኑን ነው።
የተማረ ሊቅና “ሊቀ-ሊቃውንት” ተብሎ የተሾመ ሰው እንኳ ሳይቀር ከእሴቱ ተነጥሎ በብሶት ትርክት ልቡ ሲጠፋና ስብዕናው ሲረግፍ “ልበ-አልባ” ኾኖ ትውልዱን ለጠላት ለባርነት ሲያሰናዳ ዐይተናል።
ይህንንም ደግሞ ምዕራባውያን ዐይተው ለይተው ነቅተው ስለ ጥፋት የሚተነትኑ ብዙ ቻናሎችና መጻሕፍት ቢኖሯቸውም እንኳ ትንታኔው ጭንቅላት ላይ እንጂ ልብ ላይ ስላልደረሰና በአባወራው በኩል ወደ ቤተሰብ መዋቅር ስላልወረደ ትውልዱን ሊታደጉት አልቻሉም።
ትውልዱን ከአባቶቹ ፈለግ ለመለየት የሚተጉ “የዘመኑ ሊቃውንት” በዕውቀት ስም የሚረጩት መርዝ፣ መድረሻው የአባወራው ቤት(ቤተሰብ) እንደኾነ መታወቅ አለበት።
ስለኾነም አርበኛው አባወራ የጥፋት ትርክቶችን የመለየት ንቃትና የሚመክትበት ሥልጣኔ ሲኖረው፣ ቤቱ የጥፋት ኃይሎች የማይደፍሩት ምሽግ ማድረግ ይችላል።
በዚህ ምሽግ ውስጥ የሚታነጽ ትውልድ ጀግንነትን ከተግባር፣ ክብርን ከታሪክ፣ ጽድቅን ደግሞ ሕያው ከኾነው የአባቶቹ እሴት ይማራል።
አባወራው በቃሉ ብቻ ሳይኾን በጠንካራ ስብዕናውና በአርአያነቱ ልጆቹን ሲመራ፣ የሆዳደሮች የሐሰት ስብከትና የባዕዳን ባርነት ስፍራ ያጣሉ።
የአባወራው ሥልጣን በቤተክርስትያን አልያም በመንግሥት፣ በሊቃውንቱ አልያም በልሂቃኑ መተካት እሴትን ካለማወቅ የተነሳ የሚመጣ፣ ራስንም ለጠላትና ለሆዳደሮቹ ልሂቃንና ሊቃውንት የሚያጋልጥ አደገኛ አካሄድ ነው።
የቤቱ፣ የቤተሰቡ ራስ ምን ጊዜም አባወራው መኾኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ከላይ እንዳነሳነው ምዕራባውያንና መሰሎቻቸው ትውልዳቸውን ለባርነት አሳልፈው የሰጡት ስለ ጉዳዩ እያወሩ ነገር ግን፣ የአባወራነትን ክብርና የቤተሰብን መዋቅር ከእሴታቸው ጋር ፍጹም በሚጣላው ማርክሳዊ ሸፍጥ በማፍረሳቸው ነው።
በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት አባወራው ቤቱን መምራትና መጠበቅ እንዳይችል፤ ሚስቱም እንዳትገዛው፣ እንዳትታዘዘውና እንዳታግዘው እንዳትወልድለትም ጭምር በሊቃውንቱ ስብከት አሳመጿት!
ከዚህ የነሳ በሁለት አባላት የተመሰረተ ቤታቸው፣ በባልና በሚስት ቦቻ የቆመ ትዳራቸው፣ በእናትና በአባት የሰፋ ቤተሰባቸው የጦርነት አውድማ ኾነ፤ በማን? ዐውደምህረት ላይ ቆመው ከግዴታና ከኃላፊነት ይልቅ “ደስ የሚል” ነገር ግን የማይኖር የማያስኖር እኩልነት፣ መብትና ነፃነትን ተከፍሏቸው ትውልዱን እንዲያልጩት በተላኩ ሆዳደር ሊቃውንት!
ይህንን ያውቃሉና፤ ሀገርን ከመገንቢያ ጡቧ እርሱም ቤተሰብ ያፈርሱ ዘንድ የተማሩ ነገር ግን ልባልባ ሊቃውንት እንግሊዝን እንዳጠፏት ከእኛም ዘንድ ሊያጠፉን እንቅልፍ ያጣሉ።
አርበኛው አባወራ ቤቱን ሲመሽግ፣ ማኅበረሰቡም አብሮ ይመሸጋል፤ ሀገርም ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች ትጠበቃለች።
ይህ አባወራዊ ንቅናቄ የመንግሥት ወይም የውጭ ድርጅት ድርሻ፣ ተልዕኮ፣ ኃላፊነትም ሳይኾን፣ በእያንዳንዱ አባወራ ልብ፣ ቀጥሎም በቤቱ የሚጀመር የሕልውና ዘመቻ ነው።
ወንድሞቼ!
🚨 ትውልድ እያጣን ነው!
🚨 ቤተሰብ እየፈረሰ ነው!
🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!
🚨 ጋብቻ ትዳራችን መጠቋቆሚያ እየኾነ ነው!
🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!
🚨 ምን ቢማር ዶክተርና ኢንጂነር፣ ሊቅና ሊቀ ሊቃውንት ቢባል አልጫና አስመሳይ አድርባይ ሆዳደርም ትውልድ እያፈራን ነው!
🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያም እየኾንን ነው!
🚨 ማኅበረሰባችንም እየመከነ ነው!
🚨 ሆዳደሩ ምሁራን በቁማችን በልጆቻችንም እየነገዱ ነው!
ትውልድ ከጥፋት የሚተርፍበት የመጨረሻው ምሽግ ቤተሰብ መኾኑን አስተውል። በውስጡ የምትገነባው ጠንካራ ስብዕና ለልጆችህ ጋሻ፣ ለሀገርህ ደግሞ ጽኑ ግንብ መሠረትም ነው።
ዛሬ በቤትህ የምትተክለው እውነትና በኑሮህ በሕይወት የምትመራው የምትዘራው እሴት፣ ነገ የሚመጣው ትውልድ ቢቀበለው የነፃነትና የክብር አክሊል ኾኖ ይኖርበታል።
0 Comments