✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሊቃውንት ትውልድን ያጠፉበት ወቅት፤ አልጫነት ክርስትና፣ ጃንደርባነትም ጽድቅ የኾነ’ለት!
በኢትዮጵያ ምድር ክርስትና የሥልጣኔ መሠረት፣ የነፃነት አርማ እና የጀግንነት ማኅተም ነበር።
💪”የጀግንነት ማኅተም”
በኢትዮጵያ ታሪክ ክርስትና የአላዛኝ ነፍራቃ፣ የአልጫ ጃንደርባ ትውልድ ሳይኾን አርበኛ አባወራ ነበር ያፈራው።
አርበኝነትና ሰማዕትነት የማይነጣጠሉ ነበሩ። ለሀገር መሞት እንደ ሰማዕትነት ይቆጠር ነበር። አባቶቻችን “ስለ ሃይማኖቴና ስለ ሀገሬ” ብለው ወደ ጦር ግንባር ሲዘምቱ፣ ክርስትናቸው የጀግንነት ማህተም፣ ማተሚያ፣ መዝጊያ፦ ከዚያ ወዲያ ጀግንነት፣ ከዚያ ወዲያ ሰማዕትነት፣ ከዚያ ወዲያ ጀብደኝነት፣ የለም ሲል ማኅተም ይኾንላቸው ነበር።
ቤተክርስትያን ሕዝቡን በማገልገል፣ ሊቃውንትም ሕዝቡን የሚያገለግሉ እንጂ በሕዝቡ የሚገለገሉ ለጥቅም ያደሩ አልነበሩምና በዐድዋና በሌሎች ታላላቅ ውጊያዎች ታቦት ፊት ለፊት እየተጓዘ፣ ካህናት እያሳለሙ፣ አማኙ ደግሞ “ከባርነት ሞት ይሻላል” ብሎ እንዲዋጋ የሚያደርግ የጀግንነት መንፈስ የሚዘራ እምነት ነበር።
ይህም ከክርስትና በፊት ጀምሮ የነበረ፣ በክርስትና ወቅትም ተጠናክሮ የቀጠለ፣ ነገር ግን በእኛ ዘመን ሲደርስ ትውልዱን ከእሴት ትውፊቱ በመለየት መልኩን የቀየረ የታሪክ ሂደት ነው።
የጀግንነት ማኅተም ነበር” ስንል፣ ክርስትናው ሰውን ለሀገሩ፣ ለቤተክርስትያኑ፣ ለማኅበረሰቡ፣ ለቤተሰቡ መስዋዕት እንዲኾን የሚያደርግ አንበሳዊ ግርማ የሚያላብስ፣ በመጽሐፍ የተጻፈውን ተዋጊነት ድለኝነት የሚሰብክ ትምህርት ነበረው ማለታችን ነው።
ዛሬ ግን ይህ ጠንካራ ማንነት ተሸርሽሮ በምትኩ “አልጫነትና ጃንደርባነት” (ዝምታና ፍርሃት) ሰፍኗል። ☀️ ለሊቃውንቱ ዐዲስ ኪዳን የተሰበከው በ20ኛው ክፍለዘመን ነውን?
☀️ ከዚያ በፊት የነበሩት ወንጌል አልገባቸውም ነበርን?
☀️ ይህንን ያልጫ ክርስትና የጃንደርባ ወንጌል ከየት እንዳመጡት አንጠይቃቸውምን?
🌟 እነርሱስ ከአባቶቻችን ከአባታችንም የበለጠ አዋቂ ናቸውን?
የጥቁርን ሕዝብ ቀና አድርጎ ያስሄደው፣ ዓለምን ያስደመመው የዐድዋ ድል የተገኘው በጠላት ፊት በሚንበረከኩ፣ ባፍጢም በሆዳቸው በሚደፉ፣ አድርባይ ኢትዮጵያውያን ሳይኾን በታቦት ፊት በሚንበረከኩ፣ ልባም፣ ልበሙሉ፣ የኃይልና የእምነት መንፈስም የታጠቁ “አንበሶች” ነበር።
ያን ጊዜ ክርስትና ተጋድሎ ነበር። ከማን ጋር?
1ኛ ከራስ ጋር
2ኛ ከክፋት ጋር፣ እና
3ኛ ሀገርንና እምነትን ከሚደፍር ባዕድ ጋር።
ዛሬ ግን በአደባባዮቻችን የምናየው ክርስትና መልኩን ቀይሯል። አንድም ክርስትና መልኩን እንዲቀይር በራሱ ሆዳደር ሊቃውንት ተሠርቶበታል። ሊቃውንት ተብለው በወንበር የተሰየሙት፣ ትውልዱን በቃለ-እግዚአብሔር ስም፣ ስባሪ ሳንቲም በጣለላቸው ጠላት ስር “አልጫ” አድርገውታል።
ድፍረት እንደ ነውር፣ መጋፈጥ እንደ ዓመፅ፣ መቆጣት እንደ ኃጢአት፣ በአቋም መጽናት እንደ ግትር፣ መቁረጥ(ቆራጥነት) እንደ አንባገነን፣ ኃይል እንደ ወንጌል ያልገባው፣ ሥነ-ሥርዓት እንደ ማካበድ እየተቆጠረ፤ አማኙ “ለሰላም” በሚል ሰበብ ማንነቱን አሳልፎ የሚሰጥ ስልብ፣ ወኔቢስ ጃንደርባ ኾኗል።
አርበኛዊው ክርስትና አባወራዊውም ሥርዓት ተኮንኖ በምትኩ ወፍዘራሽ የኾነ፣ ከባዕድ የተበረዘ፣ በመጽሐፍ ጥቅስ የተንቆጠቆ፣ በመድረክ ዲኮር የተሽቆጠቆጠ፣ በመብራት ባለባበስም የቀበጠ፤
ነገር ግን ሕይወት የማይኾን፣ ሕይወት የማይሰጥ፣ ሕይወት የማያስቀጥል፣ የማይኖር የማያስኖር፤ በመድረክና በዩቲዩብ፣ ባፍና በመጣፍብቻ “የሚያስበላ”፦የእንከፍ ምስኪኖች፣ የአስመሳይ አድርባዮች፣ የአሰስ አልጮች፣ የስልብ ጃንደርቦች ክርስትና ይሄ ለእኛ የሚሰጠን ነው!
ለመራራዋ ዐለም ጨው እንዲኾን የተላከው ክርስትና አጫነትን መርጧል። እውነትን እውነት፣ ሐሰትን ሐሰት ለማለት የሚደፍር አንደበት ጠፍቷል። በየመድረኩ የሚሰሙት ስብከቶች ትውልዱን ለጽድቅ የሚቀሰቅሱ ሳይኾኑ፣ የሚያልፈሰፍሱ የአላዛኝና ነፍራቃ ኾነዋል።
ሁሉም በበላበት ይጮሃል! ክርስትና “መልካምነት” ብቻ ሳይሆን “ጽናትም” ጭምር መኾኑ ተረስቶ፣ ሁሉንም እሺ የሚል፣ አቋምና አቅም የለሽ፣ ግዴለሽም የኾነ ማኅበረሰብ ተፈጥሯል። ይህ አልጫነት እንደ ትሕትና እየተሰበከ፣ እየተቆጠረ፣ ትውልዱ እንዲጠፋ እንዲጋዝም ተፈርዶበታል።
በታሪክ ጃንደርባ መራባት የማይችል፣ እንዳይችልም ተስፋ ወኔውን፣ ዘር ፍሬውን የተሰለበ ነው። ዛሬም በመንፈሳዊው ዓለም “ጃንደርባ ትውልድ” ተፈጥሯል። ከእውነት፣ እምነት እሴቱ የራቀ፣ በእውቀት ብቻ የረቀቀ፣ ልቡ ለጽድቅ ያልሠለጠነ፣ ጽድቅ ይፈጽምበት ዘንድ የሚያስጨክነው ልቡ የተሰለበ ትውልድ!
ይህ ትውልድ በዐውደ-ምህረት ፊት ቆሞ ማልቀስንና ማላዘንን፣ ማዜምን፣ መነፋረቅ እንጂ፣ እንደ ኤልያስ ክፋትን መገሰጽን፣ እንደ ዳዊትም በእምነት ሰልፍን አያውቅም።
ጃንደርባነት ጽድቅ ተደርጎ ተሰብኳልና፤ ወደዚያ ያማትራል፣ ያስባል፣ ይሳባልም፦ምክንያቱም ጃንደርባ አይቃወምም፣ አይታገግልም፣ አያዝም፣ አይቀድምም፣ “አሜን” ብሎ ብቻ በታዛዥነት ለባርነት ይሰማራል እንጂ።
ዛሬ ባደባባይ የጸደቀው ቅብጠት፦ ታይታ ፈላጊነት፤ ነው። ባደባባይ በመድረክ፣ በታላላቅ ነገሥታትና መንግሥታት ፊት መታየት፣ “በጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድ” መመዝገብ የተመረጠበት የቀላጮች ዘመን ኾኗል።
በመንፈሳዊው መድረክ ላይ የሚታየው ትርዒት ከእውነተኛ መንፈሳዊነት ይልቅ “ላይክ” እና “ሼር” የሚፈልግ፣ የሰውን ይኹንታን የሚማጸን ነው።
ጀግናው አርበኛ አባወራ ግን የፈጣሪውን ይኹንታ፣ የቃሉን አለኝታ ብቻ ፈልጎ ወደ ጦር ግንባር ይተም ነበር፤ የዛሬው አልጫ ግን የሰውን ጭብጨባ፣ ታይታና ይኹንታውንም ሲሻ እውነቱን፣ እምነቱን እሴቱን ይሸጣል፤ ትውልድም ልቡ እየጠፋ በባርነት ለጠላት ይጋዛል።
ታሪክ ይቅር የማይላቸው ሊቃውንት ትውልዱን አንኳስሰውታል። ክርስትናን ከኃያላን ወደ የልምሻና የብሶተኛ፣ የቀስተኛ፣ የነፍራቆችም ይኾን ዘንድ ቀይረውታል።
የጥንቱ የኢትዮጵያውያን ክርስትና ባለበት፣ በነበረት፣ ከሰው ግዛት ደርሶ በማይዘርፍበት ስሙ ከሩቅ የሚያስፈራ ግርማ፣ የሚናፈቅም ሞገስ ነበረው ነበረው።
የዛሬው ግን “የበግ ለምድ” የለበሰ የአስመሳይ አድርባዮች ስብስብ፣ የአልጫ ምስኪናን ጉባኤ ኾኗል። ብዙኃን ጀግኖችን፣ ኃይለኞችን፣ ተፈሪዎችን ያፈራው እምነት ዛሬ “ጃንደርባዎችን” በብዛትና “በጥራት” እያመረተ ነው።
🌟☀️🚨🎯 ይህ ደግሞ በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አደራቸውን ቀርጥፈው በበሉ በሊቃውንተ ቤተክርስትያን የሚፈጸም መንፈሳዊ ሸፍጥ ነው።
እናንነተ ይህንን እንዴት እንደምታዩት አላውቅም! እኔ ግን ከራሴ አልፌ ለልጆቼና በዙሪያዬ ላሉትም ጭምር ዘወትር የማስጠነቅቃቸው፣ የማሳስባቸውም ነገር ነው።
🌟 የቀደሙ መጻሕፍትን አንብቡ፣ በዚህ ዘመን በተለይም የመድረክ ሸቃላ “ሊቃውንትን” በሸፍጥ የተሞላ ትርክት አትስሙ። አለበለዚያ ግን በሰማችሁት ቃል ልክ አባቶቻችሁን የማትመስሉ፣ አባታችሁንም የማትገልጡ አልጮች (Demoralized) ትኾናላችሁ።
በዚህ ያልጮች ክርስትና የክርስትያኑ በተለይም የተዋሕዶ ማኅበረሰቡ በቁጥርም በጥራትም እየተመናመነ ነው። ወንዱ በዚህ በተሰበከለት ክርስትና ምን ቢማር ማስትሬትና ዶክትሬትም ቢኖረው እንኳን ሚስትና ልጆቹን መላ ቤተሰቡን ቀርቶ፤ አንድ ራሱን መምራት የማይችል፣ ወዴት ሊመራ እንዳለውም የማያውቅ እንከፍ ምስኪን ይደረጋል።
ሴቷም በዚሁ የአባቶቻችንን የማይመስል፣ እናቶቻችንም ያልኖሩበትን ነገር ግን ሆዳደር ሊቃውንቱ በሳንቲም ተገዝተው የተቀበሉትን መርዘኛ ዘር በልቧ ይዘራሉ።
ከዚያም እንኳን ንክር ምስኪን እንከፍም ተደርጎላት እንዲሁም አስቀድማ የማታከብረው፣ የማትገዛለት፣ የምትንቀው፣ የማትታዘዘው፣ የማታግዘው፣ የማትወልድለት አንድ ወይም ሁለት እንደ አህያ ጡት ይኾናል። ይኹን እንጂ የምትሞግተው፣ የምትፎካከረውና ጫማ የምትለካካው እንድትኾን ትማራለች።
በዚያም የኦርቶዶክሱ ቤተሰብ ለፍቺ ይከንፋል፣ ማኅበረሰቡ አንድነት ውሕደቱን ያጣል፣ በሴትና በወንዱ መካከል መተማመን ይጠፋል፣ ነገር ግን ስሜት አላቸውና የትም ከማንም የማንም ሳይኾኑ መንጠላጠል ወግ ይኾናል፤ አመንዝራነት፣ ዲቃላ መጎተት፣ ልጆችን ያለወላጅ በተለይም ያለ አባት ማሳደግም ይስፋፋል።
🚨 ትውልድ ይጠፋል፤ ማኅበረሰብ ይመክናል!
በዚህ ሁሉ መካከል ግን የትዳር “መካሪና አማካሪ፣ አሠልጣኝና አስተማሪ ነኝ” ባዩ ሊቅ በመድረክና በዩቲዩብ፣ ባፍና በመጣፍ ይሸቅላል። አስቀድሞ ባልሠለጠነበት ሆዱ ባፍጢም ተደፍቷልና ስለ ትውልዱ፣ ስለ ማኅበረሰቡ ግድ አይሰጠውም!
ይህ ክርስትናን ያልጮች ትውልዱንም ጃንደርባ የማድረግ ሸፍጥ ነው!
0 Comments