ራሱን በራሱ ትውልዱን በሊቃውንቱ መስለብ



ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ትውልዴ ከተጋተው ሸፍጥ የተነሳ ልጆቹን የሚያስተምረው፣ እርሱም የሚኖረው ክርስትና ከትውፊቱ የተለየ፣ ደረቅ ወጉን የያዘ፣ ጽድቅን የማይፈጽም ኾኖ ለባርነት ይሰጥበታል።

በቤተ መቅደሱና በጉባኤያቱ መካከል “ሊቃውንት” ተብለው የሚጠሩት፣ ነገር ግን ልባቸው በባዕዳን ትርክት የሰከረው ወገኖች፤ ዛሬ ትውልዱን የጀግንነት ወንድነቱን አጥፍተው፣ የክብርና የጽድቅ፣ የተስፋንም ትርጉሙን አሳስተው በጃንደርብነት ለባርነት አሳልፈው እየሰጡት ይገኛሉ። ይህ “መስለብ” በሥጋ ሳይኾን በመንፈስ፣ በአስተሳሰብ፣ በወኔ የሚካሄድ ስውር ሸፍጥ ነው።

ትውልዱ ከአባቶቹ የወረሰውን ባለቤትነትንና መሪነትን እንዲጥል ተደርጓል። ሊቃውንት ነን ባዮቹ ክርስትናን ከኢትዮጵያዊ እሴት፣ እምነትና እውነቱ ነጥለው፣ “ደረቅ ወግ ልማድም” ብቻ አድርገውት በቦታው ግን የባዕዳንን የጃንደርብነት ወግ አጽድቀው አቀርበውታል።

በቤቱ፣ በትንሿ ቤተመንግሥቱ የአባቶቹን የመሪነት ሚና፣ የተፈሪነት ግርማ፣ የጠባቂነት ሞገስ፣ የቅጠኝነት ክብር፣ የሥርዓት ድንበር መኾኑ ቀርቶ፣ ተንቆ፣ ተረስቶ፣ ተገፍቶ፣ ተኮንኖ፣ ተጥሎ፣ ተጠልቶ፣ ራሱም ተጠይፎት እንዲኖር ስልብ በመንፈሱ፣ ድኩም በአቅሙ፣ ሽልጥልጥ በአቋሙ አድርገው ለባርነት አመቻችተውታል።

ዛሬ አስገዳጅ እንዲኾንላቸው በተሯሯጡለት የቅድመጋብቻ ትምህርት ያዘጋጁት ትምህርት፤ የትዳር መካሪና አማካሪ፣ አሠልጣኝና አስተማሪ የኾኑትም ካራቸውን በሁለት ወገን የሳሉበት ስብከት ይኸው መጨረሻው ትውልዱን ለጠላት በባርነት የሚያግዝ እንጂ ወደ አባቶቹ ንግሥናን ከቅስና አስተባብሮ የሚያስጨብጥ የክብር አይደለም።

በዚህም ምክንያት ትውልዱ፦ ጀግንነትን እንደ ኋላቀርነትና እንደ ዓመፅ እንዲቆጥረው ተደረገ፤ ክብርን በባዕዳን ጽንሰሃሳብና በቁሳዊ ስኬት ብቻ እንዲለካው ተሰለበ፤ ጽድቅን ከማኅበረሰባዊ ኃላፊነትና ከቤተሰብ መሪነት የተለየ፣ የግል ስሜት እንከፍ ምስኪንነት አድርጎ እንዲቀበል ተደረገ።

ዛሬ ትውልዱ የሚኖረው ክርስትና “ጽድቅን የማይፈጽም” የቃላት፣ የአፍአ፣ የታይታ፣ የቅብጠት፣ የወግ፣ የልማድ፣ ደረቅ ሕይወት አልባ ኾኗል። አባወራው በቤቱ መሪነቱን ትቶ፣ መኾኑም ቀርቶ በሊቃውንቱ ለተሰበከለት የባዕዳን ትርክት ተገዢ ኾኗልና ልጆቹን ከዚህ ማውጣት አልቻለም፤ ይቻለው ዘንድ ያስታጠቀው እንደሚቻለውም ከድንዛዜው አንቅቶ የነገረው የለም።

ልጆቹን የሚያስተምረውም ከአባቶቹ ፈለግ፣ እነርሱ ከተመላለሱበት ዳና፣ ለልጆቻቸውም ካሳዩዋቸው ጥበብ ፍጹም የተለየ፤ ለባዕዳን የባርነት ርዕዮተ-ዓለም መንገድ የሚጠርግ “ለስላሳ፣ ቀለስላሳ፣ ልፍስፍና ሽልጥልጥ” አስተሳሰብን ነው። ይህ ደግሞ ትውልዱ በገዛ እጁ ራሱን ለባርነት አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያደርግ መንፈሳዊ ድንዛዜ ነው።

ይህ የተሰለበ ትውልድ በፖለቲካውም ኾነ፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበረሰባዊ ኑሮውና በራሱ ትውልድም ጭምር ባለቤት መኾን አይችልም። “የራሴ” የሚለው እሴት ጠልቶና ጥሎ፣ የአስመሳዮቹን ሊቃውንት ፈለግ ተከትሎ የወጣለትና የተዋጣለት አስመሳይ አድርባይ ኾኗልና በየጊዜው በሚመጡ የባዕዳን ትርክቶች እንደ ማዕበል ይነዳል እንጂ እንደ ዓለት ጸንቶ አይቆምም፤ አይጋፈጥም አይቃወምምም።

ልክ “ክርስትናው” ደረቅ ወግ እንደኾነው ሁሉ፣ ፖለቲካውም የጥቅም መሯሯጫና የባዕዳን አጀንዳ ማስፈጸሚያ ኾኖ ይቀራል እንጂ ፍትሕ ለተጠማው ወገኔ አንዳች ፋይዳ የለውም!

ይህን ስልታዊ የትውልድ፣ የማኅበረሰብና የሀገር ጥፋት ለመመከት የሚቻለው በሊቃውንቱ መድረክ ላይ በመከራከር ብቻ ሳይኾን፣ መሠረታቸው በኾነው ቤተሰብ ላይ በመሥራት ነው።

ከዚያ በፊት ቀድሞ የሚመጣው ግን የአባወራው (የአንተ) መመለስ ነው። አንተ ተፈጥሮአዊ ጸጋህን አውቀህ፣ የአባቶችህን ዳና ፈልገህ፣ ሀገርን የሠራ እሴት መርምረህ ልብህን በእውነት፣ እምነትና እሴቱ ገንብተህ ጽድቁን ትፈጽምበት ዘንድ ሠልጥነህበትም መገኘት ነው።

በቀጣይም እያንዳንዱ አባወራ የቤቱ መሪ፣ ጠባቂ፣ ተጠያቂ መኾን አለበት። የውጭው ትርክት ልጆችን ከመጥለፉ በፊት፣ አባወራው የአባቶቹን እውነተኛ የጀግንነትና የጽድቅ ታሪክ በቤቱ ውስጥ መተረክና በተግባር ማሳየት ይኖርበታል።

ክርስትናን ከኢትዮጵያዊ ጨዋነትና እሴት ጋር አቆራኝቶ ለትውልዱ በተግባር በሕይወት ማስተማር። ጀግንነት ለሀገርና ለእውነት መቆም መኾኑን፣ ክብር ደግሞ የራስን ማንነት ከመጠበቅ እንደሚመነጭ በቤተሰብ ውስጥ መቅረጽ።

ትውልዱ በባዕዳን ትርክት ከሰከሩ፣ ኢትዮጵያዊውን መልክ ከማይስሉ ዘመናዊ “ሊቃውንት” ይልቅ፣ ወደ ቀደሙት ምንጮች፣ ዘመን ወደማይሽራቸው መጻሕፍት፣ ጥበብና ወደ ኢትዮጵያዊው የሥነ-ምግባር መዓቀፍ እንዲመለስ ማድረግ።

ትውልዱን ከጥፋት የሚያድነው የቤተሰብ ጥንካሬና የአባወራው ንቁ ተሳትፎ ነው። “ክርስትናችን” መልኩን ቀይሮ ለሕይወት በተሰበከልን ክርስትና ትውልዱ እንዳይጠፋ፣ ትውልዱም ራሱን በሚያስጠፋው “ክርስትና” ቤተሰቡን እንዳያጠፋ እያንዳንዱ አባወራ የቤቱ፣ የሀገሩ እሴት ጠባቂ ኾኖ መቆም አለበት።

አስረጅ ብትፈልግ፦

ትናንት ክርስትያን የነበሩ፣ ክርስትናቸው በጦር ሳይኾን ባፍጢም በተደፉ አስመሳይ፣ አድርባይ ሆዳደር ሊቃውንቱ ተበርዞ፣ ትውልዱ ተስፋ ሕይወትን ሊሰማ ከሚመጣበት መድረክ ስር ለጠላት በጃንደርብነት ለባርነት በዝምታ እንደ ሙክት ተላልፎ የተሰጠበት፤ እምነት እሴቱን አጥቶ እውነት ሕይወቱ ጠፍቶት የመከነበትን የእንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አሜሪካ... ነገር ተመልከት!


Post a Comment

0 Comments