የኖኅ መርከብ፦ በደረቅ ምድር ላይ የበቀለ ተስፋ

ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ

ዓለም ሁሉ በአንድ 'እብድ' በተባለ አረጋዊ እና 'በደረቅ ምድር' ላይ በሚሠራው ግዙፍ የእንጨት ግንባታ ላይ ሲሳለቅ... ሰማይ ግን የጥፋት ውኃን ለማፍሰስ እየተዘጋጀ ነበር። ዛሬ፣ የመቶ ዓመቱን ትዕግሥትና የመታዘዝ አርማ የሆነውን የአንድ ልባም አረጋዊ ታሪክ እንመለከታለን።

ጠያቂ ትምህርት  ክፍል ፲፭

​በጥንታዊው ምድር ላይ ፀሐይ ስትወጣ፣ የምታበራው በውበት ላይ ሳይሆን በግፍና በውድቀት ላይ ነበር። የሰው ልጅ ልብ የክፋት መፈልፈያ ሆኖ፣ ምድር በዓመፅና በደም ረክሳለች። በእውነት እንደሚነገረው፣ የቃየል ልጆችና የሴት ልጆች የተቀደሰውን መስመር አጥፍተው፣ ዓለም ወደማትመለስበት የጥፋት አፋፍ ላይ ደርሳ ነበር።

​በዚህ እጅግ ጥቁር ጭጋግ ውስጥ ግን፣ አንዲት የማትጠፋ የብርሃን ነጥብ ነበረች። እርሱም ኖኅ ነው። ለሰዎች እብድ ለእግዚአብሔር ግን የተወደደ ነቢይ ነበር።
​ዓለም በጭፈራና በስካር ጩኸት ስትናወጥ፣ ኖኅ ግን በጸጥታ ከፈጣሪው ጋር ይራመድ ነበር። ኖኅ በትውልዱ መካከል "ፍጹም" የተባለው ስለማይሳሳት ሳይሆን፣ ልቡ ለእውነት ክፍት ስለነበረ ነው። አንድ ምሽት፣ ያ በምስጢር የተሞላው ሰማያዊ ድምፅ ወደ ኖኅ መጣ። ድምፁ እንደ ነጎድጓድ የሚያስፈራ፣ እንደ ነፋስም ሹክ የሚል ነበር።

      ​«የሥጋ ሁሉ ፍጻሜ በፊቴ መጥቷል፤ ምድር ከእነርሱ የተነሣ በግፍ ተሞልታለችና፤ እነሆም ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።» (ዘፍጥረት ፮፥፲፫)

​እግዚአብሔር ለኖኅ የሰጠው ትእዛዝ ለሰብአዊ አእምሮ የሚከብድ፣ ለዓለማዊ ጥበብ ደግሞ "ዕብደት" የሚመስል ነበር። በደረቅ ምድር ላይ፣ ባሕር በሌለበት፣ ዝናብ ምን እንደሆነ በማይታወቅበት ስፍራ ግዙፍ መርከብ እንዲሠራ ታዘዘ።

አሰራሩም እንዲህ ነው፦

- ​የጎፈር እንጨት፦ የማይበሰብስና ጽኑ የሆነው እንጨት።

- ​ቅጥራን፦ መርከቧን ከውስጥና ከውጭ የሚሸፍን፣ ከጥፋት ውኃ የሚጠብቅ ምስጢራዊ ቅባት።
- ​መለኪያው፦ ርዝመቱ ሦስት መቶ ክንድ፣ ስፋቱ አምሳ፣ ከፍታው ሠላሳ።

​ይህ ትእዛዝ ለኖኅ መታዘዝ ብቻ ሳይሆን "ትዕግሥት" የተዘራበት የመጀመሪያው ዘር ነበር።

​ኖኅ "ለምን?" ብሎ አልጠየቀም። "ባሕር የት አለ?" ብሎ በመለኮት እውቀት ላይ የራሱን መላምት አንጠልጥሎ አልተከራከረም። ይልቁንም ያንን ሰማያዊ ንድፍ በልቡ ሰሌዳ ላይ አሳረገው። ዓለም ወደ ጥፋቷ ስትሮጥ፣ ኖኅ ግን የተስፋን መሣሪያ ለመቅረጽ መጥረቢያውን አነሳ። እያንዳንዱ የተፈለጠ እንጨት፣ እያንዳንዱ የተመታ ምስማር የኖኅ "አምናለሁ" የሚል ምስጢራዊ ጩኸት ነበር።

"ኖኅ ገና ስለማይታየው ነገር ተረድቶ እግዚአብሔርን እየፈራ ቤተሰቦቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ..." ዕብራውያን ፲፩፥፯

​ትርጓሜው፦ ኖኅ ዝናብን ሳያይ፣ ማዕበሉን ሳይመለከት በእግዚአብሔር ቃል ብቻ ተመርኩዞ በመሥራቱ "ዓለምን የኰነነበት የእምነት ጽድቅ ወራሽ" ሆኗል። ኖኅ መርከቧን መሥራት የጀመረው ገና ዝናቡ ሳይዘንብ ነው። ይህ ማለት እውነተኛ መታዘዝ የሚጀምረው ውጤቱን ካዩ በኋላ ሳይሆን፣ ቃሉን ከሰሙ በኋላ መሆኑን ያሳያል። እምነት ኖኅ በደረቅ ምድር ላይ መርከብ ሲሠራ፣ በዙሪያው ያሉት ሰዎች "እብድ" ይሉት ነበር፤ እርሱ ግን ከሰዎች ጩኸት ይልቅ የፈጣሪውን ዝምታ መረጠ።

ጊዜው መፍሰስ ጀመረ። ቀናት ወደ ሳምንታት፣ ሳምንታት ወደ ወራት፣ ወራትም ወደ ዓመታት ተቀየሩ። ኖኅ በመርከቧ ግንባታ ላይ አንድ መቶ ሃያ ዓመታትን አሳለፈ። ይህ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የታየ እጅግ ረጅሙና አስቸጋሪው «የመታዘዝ ፈተና» ነበር።
​ኖኅና ሦስት ልጆቹ (ሴም፣ ካም፣ ያፌት) በየቀኑ ወደ ጫካ ይሄዳሉ። ግዙፍ የጎፈር እንጨቶችን ይቆርጣሉ፣ ይጠርባሉ፣ በጀርባቸውም ተሸክመው ወደ ግንባታው ስፍራ ያመጣሉ። መጥረቢያው በረጅም ርቀት ላይ ይሰማል፤ እያንዳንዱ ምት ግን ለዓለም የንስሐ ጥሪ፣ ለኖኅ ደግሞ የመታዘዝ መዝሙር ነበር።

​መርከቧ ከቀን ወደ ቀን እያደገች ስትሄድ፣ በደረቅ ምድር ላይ እንደ ግዙፍ የእንጨት ተራራ ቆመች። በዙሪያዋ ግን የውኃ ሽታ አጠራጣሪ ሁኔታም ጭራሽ አልነበረም።

​የዚያ ዘመን ሰዎች ግን ግንባታውን ለማየት በየቀኑ ይሰበሰባሉ። እነርሱ በታላላቅ ከተሞች ግንባታ፣ በጭፈራና በሥጋዊ ደስታ ተጠምደው ነበር። ኖኅን ሲያዩት በንቀት ይሳለቁበት ነበር፦

        ​«አንተ አረጋዊ! መርከቧን በደረቅ ምድር ላይ የሠራሃት በምን ልታንሳፍፋት ነው? ዝናብ የሚባል ነገር ከሰማይ ሲወርድ ማን አይቶ ያውቃል?» ይሉት ነበር።

​ኖኅ ግን መጥረቢያውን አላቆመም። በመካከላቸው ቆሞ «ንስሐ ግቡ! የጥፋት ውኃ ሊመጣ ነው!» እያለ ይሰብካቸው ነበር። እነርሱ ግን በላዩ ላይ ይተፉበት፣ ድንጋይም ይወረወሩበት ነበር። መታዘዝ ማለት እንዲህ ነው—ዓለም ሁሉ «እብድ» ስትልህ፣ አንተ ግን የፈጣሪህን ድምፅ ብቻ ሰምተህ መቆም!!

​መርከቧ በቅጥራን ስትለሰን፣ ጥቁርና አስፈሪ መልክ ነበራት። በመጽሐፍ ቅዱሳዊና በቤተክርስቲያን ትርጓሜ፣ ይህች መርከብ የቤተክርስቲያን የቃልኪዳን የኢትዮጵያ የእመቤታችን ምሳሌ ናት። ውስጥና ውጭዋ በቅጥራን መለሰኑ የጸናች መሆኗን ያሳያል። ኖኅ በመቶ ዓመታት ውስጥ አንድም ቀን ተስፋ አልቆረጠም። ሰማዩ ሰማያዊ ሆኖ፣ ምድሪቱ ደረቅ ሆና ሳለ፣ እርሱ ግን በመንፈሱ የውኃውን ድምፅ ይሰማ ነበር።

ወገኖቼ!

- ​ትዕግሥት ማለት ምን ማለት ነው? ትዕግሥት ማለት ዝም ብሎ መጠበቅ ሳይሆን፣ እየሠሩና እየተሰደቡ እየወደቁና እየተነሱ እየተነቀፉና ተስፋን እያፀኑ መጠበቅ ነው። ኖኅ መቶ ሃያ ዓመት ሙሉ በሰዎች ስድብና በፀሐይ ቃጠሎ ውስጥ የቆመው በመታዘዙ ነው።

- ​የእውነተኛ ብቸኝነት ዋጋ፦ እውነትን ይዞ ብቸኛ መሆን፣ ሐሰትን ይዞ ከሕዝብና ከአሕዛብ፡ ከመንግሥታትና ከአለቆች ጋር ከመሆን እንደሚበልጥ ኖኅ በተግባር አሳይቷል።

የዛሬው ጠያቂ ትምህርታችን የሚደመደመው ዓለም ዳግም በተወለደችበት፣ ፍርድና ምሕረት በተሳሳሙበት በዚያ አስፈሪና አስደሳች ምዕራፍ ነው። መቶ ሃያ ዓመታት የፈጀው ትዕግሥት አብቅቶ፣ ሰማይና ምድር የሚገናኙበት ቅጽበት ደረሰ።

​ሰማዩ በድንገት ጠቆረ። አየሩ በከባድ ጭጋግ ተዋጠ። ኖኅና ቤተሰቡ ወደ መርከቧ ገቡ። እንስሳቱ በየወገናቸው (ከንጹሐን፣ ከርኩሳን) እየሆኑ በታላቅ ሰልፍ ወደ መርከቧ ሲገቡ ዓለም በድንጋጤ ትመለከት ነበር።

​እዚህ ጋር ነው ትልቁ ምስጢር ያለው፦ ደጁን የዘጋው ኖኅ አልነበረም፤ እግዚአብሔር እንጂ። (ዘፍጥረት ፯፥፲፮)። ምሕረት አብቅቶ ፍርድ የሚጀምርበት፣ የንስሐ በር የተዘጋበት ያ አስፈሪ ዝምታ ሰፈነ። ከውጭ የቀሩት ሰዎች መሳለቃቸውን አቁመው፣ መርከቧን ማንኳኳት የጀመሩት ያኔ ነበር። ነገር ግን ጊዜው አልፏል። የዘገየ ጩኸት ሰሚ የለውም። ከእግራቸው መዳፍ የተነሳው የጥፋት ውሃ አፍንጫቸውን ሰነገው። ጩኸት ብቻ!!

​የሰማይ መስኮቶች ተከፈቱ፤ የጥልቁም ምንጮች ፈለቁ። ውኃው ከላይ ብቻ ሳይሆን ከታችም መፍለቅለቅ ጀመረ። ለአርባ ቀንና ለአርባ ሌሊት ምድር በውኃ ተጥለቀለቀች። ከፍተኛዎቹ ተራሮች እንኳ በውኃ ተሸፈኑ።

​በመርከቧ ውስጥ ግን ሰላም ነበር። መርከቧ በውኃው ላይ ስትናወጥ፣ በውስጧ ያሉት ነፍሳት ግን በመለኮታዊ ጥበቃ ሥር ነበሩ። መርከቧ የእውነተኛይቱ ተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ምሳሌ ነበረች—በውጭው ዓለም ጥፋትና ማዕበል ቢኖርም፣ በውስጧ በእምነት ጠብቀዋትና አክብረዋት በሚኖሩት ቅን የዋሀን ልብ ውስጥ ግን ሕይወትና ተስፋ አለ።

​ከመቶ አምሳ ቀናት በኋላ ውኃው ጎደለ። መርከቧ በአራራት ተራሮች ላይ አረፈች። ኖኅ መጀመሪያ ያልታመነው ቁራን፣ በኋላም ታማኝ ርግቧን ላከ። ርግቧ የወይራ ቅጠል ይዛ ስትመለስ፣ ምድር ዳግም ለሕይወት መዘጋጀቷ ታወቀ። ኖኅ ከመርከቧ ወጥቶ የመጀመሪያውን መሠዊያ ሠራ፤ መሥዋዕቱንም አቀረበ።

​እግዚአብሔርም ደስ አለው፤ በሰማይ ላይም ቀስተ ደመናን አኖረ። ይህ ቀስተ ደመና የትምክህት ሳይሆን የኪዳነ ምሕረት ምልክት ነበር። ዛሬም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ታላቅ የምህረት ዐይን ነው። በዚህም "ዳግመኛ ምድርን በውኃ አላጠፋም" የሚል የዘላለም ቃል ኪዳን ተገባ።

ከታሪኩ ምን እንማራለን!?

- መለኮታዊ ፍርኃትን፦ የእግዚአብሔር ትዕግሥት ረጅም ቢሆንም፣ ፍርዱ ግን የማይቀር መሆኑን ያሳያል።
- የመታዘዝ ዋጋ፦ ኖኅ በመታዘዙ ምክንያት ዓለምን ሁሉ ዳግም የሚያቆም የሰውን ልጆች ትውልድ የሚያስቀጥል የአዳም ሁለተኛ ምትክ የሰው ልጆች አባት ለመሆን በቃ።

- የኪዳን ኃይል፦ ሕይወት የሚቀጥለው በሰው ኃይል ሳይሆን፣ ከፈጣሪ ጋር በሚደረግ ቅዱስ ቃል ኪዳን ነው።

​የዛሬው ኖኅ ታሪክ ማጠቃለያ፦

ኖኅ መርከቧን ሲሠራ ብቻውን ነበር፤ በውኃው ላይ ሲንሳፈፍም ብቻውን ነበር። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር ስለነበረ፣ ዓለምን ሁሉ አሸነፈ። ትዕግሥትና መታዘዝ መጨረሻቸው በረከትና በእግዚአብሔር የተወደደ ሕይወት ነው።

የዕለቱ ትምህርት ጥያቄ፦

​ዓለም ሁሉ በአንድ የጥፋት አቅጣጫ እየፈሰሰ ባለበት፣ የሰዎች መሳለቂያና የዘመኑ ግፊት 'የምትሠራው መርከብና የምትጓዘው ጉዞ ከንቱ ነው' እያለህ ባለበት በዚህ ሰዓት፤ አንተ ግን ልክ እንደ ኖኅ ከሰዎች ጩኸት ይልቅ የፈጣሪህን 'ዝምታ' አምነህ፣ በደረቅ ሕይወትህ ላይ የተስፋ መርከብን መሥራትና ቃሉን ጠብቀህ ፍርዱን መቆየት ትችላለህን?

ኖኅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚታወቀው በሦስት ታላላቅ ባሕርያቱ ነው፦

፩) ​መታዘዝ፦ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ እንዳደረገ ተመስክሮለታል።

፪) ​ትዕግሥት፦ ለ፩፻፳ ዓመታት የሰዎችን ስድብ ችሎ መርከቧን ፈጽሟል።

፫) ​እምነት፦ የማይታየውን እንደታየ አድርጎ አምኖ ተራምዷል።

​የጥፋት ውኃው ሙሉ ትውልድን ከአድማስ ባሻገር ቢደመስሰውም፣ የኖኅ የመቶ ዓመት ጽናት ግን ለአዲስ ሕይወት በር ከፈተ። ዛሬም ድረስ በሰማይ ላይ የሚታየው ቀስተ ደመና ይመሰክራል፤ መታዘዝ በደረቅ ምድር ላይ ተስፋን ይዘራል። ሰምቶ ለመዳን፤ ድኖ ለመመስከር ያብቃን፤ ቸር ይግጠመን።

Post a Comment

0 Comments