በአፍሪካ የመጀመሪያው የኮሮናቫይረስ ሞት ግብጽ ውስጥ ተመዘገበ


የህክምና ባለሙያዎችና አምቡላንሶች


Image copyrightAFP
በኮሮናቫይረስ ተይዞ ግብጽ ውስጥ ህክምና ላይ የነበረው ጀርመናዊ ቱሪስት ህይወታቸው አለፈ፤ በዚህም አፍሪካ ውስጥ በበሽታው ምክንያት የሞቱ የመጀመሪያው ሰው ሆነዋል።
ከሳምንት በፊት ወደ ግብጽ ገብተው የነበሩት የ60 ዓመቱ አዛውንት ትኩሳት እንዳለባቸው ተናገረው ነበር።
ግለሰቡ በቀይ ባሕር የመዝናኛ ከተማዋ ሁርግሃዳ ወደሚገኝ ሆስፒታል ተወስደው ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ ነበር በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠው።
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው የግለሰቡ አተነፋፈስ በአደገኛ የኒሞንያ ህመም ታውኮ ነበር።
ታማሚው ወደ ለይቶ ማከሚያ እንዲገቡ ተጠይቀው ፈቃደኛ ሳይሆኑ ከቀሩ በኋላ ነው ህይወታቸው ያለፈው።
ቅዳሜ ዕለት የግብጽ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፤ በአንዲት የመዝናኛ መርከብ ላይ የተገኙ 45 አዳዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ጨምሮ በአገሪቱ 48 ህሙማን መገኘታቸውን አመልክቷል።
የመዝናኛ መርከቧ ለብቻዋ ተለይታ እንድትቆይ የተደረገ ሲሆን በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ደግሞ በአገሪቱ በስተሰሜን በሚገኝ ለይቶ የማከሚያ ማዕከል ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
በአፍሪካ እስካሁን በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 79 የደረሰ ሲሆን የመጀመሪያው ሞት ደግሞ ግብጽ ውስጥ ተመዝግቧል። በዘጠኝ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል፤ እነሱም
• ግብጽ - 48
• አልጄሪያ - 17
• ሴኔጋል - 4
• ደቡብ አፍሪካ - 3
• ሞሮኮ - 2
• ካሜሩን - 2
• ቱኒዚያ - 1
• ቶጎ - 1
• ናይጄሪያ - 1

Post a Comment

0 Comments