አንዳንድ በመንግስታት የሚለቀቁ የሞባይል መተግበርያዎች (Apps) የሚፈጥሩት ስጋት!

 
✍ ኤልያስ መሠረት 

ነዳጅ ለመቅዳት፣ ክፍያዎችን ለመፈፀም፣ አገልግሎት ለማግኘት... ወዘተ እየተባለ ህዝቡ በአስገዳጅነት አንዳንድ የሞባይል መተግበርያዎችን እና የዲጂታል መንገዶችን እንዲጠቀም የሚያስገድዱ አሰራሮችን በቅርቡ እያየን ነው። 

ነገር ግን ከሌሎች ሀገራት ልምድ እንደምንረዳው አንዳንድ መተግበርያዎች (የሞባይል አፖች) ዜጎችን ለመከታተል እና መረጃዎችን ለመመንተፍ በአንዳንድ መንግስታት ይውላሉ። በሶርያ፣ ሩስያ፣ ቤላሩስ፣ በአሜሪካ፣ በእስራኤል፣ በእንግሊዝ እና ቻይና በስፋት ጥቅም ላይ ውለዋል። 

ይህን ችግር እነ ኤድዋርድ ስኖውደን እና ጁሊየን አሳንጅ ቀድመው ያጋለጡ ነበር፣ በዚህም ምክንያት ብዙ ችግር ደርሶባቸዋል። 

ታድያ ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ምን አሳሰበኝ? 
ለምሳሌ በቅርቡ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው Tele Birr በምስሉ ላይ እንደሚታየው የተጠቃሚዎችን ስልክ ፎቶ እና ቪድዮ፣ አድራሻ፣ የግል መረጃ፣ የፋይናንስ መረጃ፣ ሴቭ የተደረጉ ስልኮች ቁጥር፣ የስልኩን መለያ እና ሌሎች መረጃዎች ማየት እንደሚችል ጉግል ፕሌይ ያሳያል (እቀባ/restriction ካልተደረገበት ማለት ነው)። ምን ያህሉ የመተግበርያው ተጠቃሚ እቀባ እንዳደረገ መገመት ይቻላል። 

አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንዳስረዳኝ Tele Birr እነዚህን ሁሉ መረጃዎች የሚያገኝ ከሆነ የግል መረጃ አያያዝ ጥሰት ነው። 

"ይህ የ Tele Birr መተግበርያ እንደሚጠይቀው ሌሎች እንደ CBE Birr፣ Apollo ያሉ መተግበርያዎች አይጠይቁም። ጉግል ፕሌይ ይህ የ Tele Birr መተግበርያ እንደ ስልክ ማይክራፎን፣ ካሜራ፣ ወዘተ እንደሚያገኝ ይናገራል፣ ይህ አሳሳቢ ነው" ይላል ባለሙያው አብነት ተፈራ። 

አብነት አክሎም "እነዚህ የክፍያ ስርዓቶች እንደ ተጨማሪ የክፍያ አማራጭ ማለትም በጥሬ ገንዘብ፣ ኤቲም፣ POS ሳይሆን የግዴታ (mandatory) መደረጋቸው እና በዚህ መልኩ ብቻ ተጠቀሙ መባሉ የበለጠ የችግሩ ተጋላጭ እንድንሆን ሊያደርገን የሚችል ስጋት አለኝ" ብሏል። 

"መረጃዎችን ከግለሰብ ፈቃድ ውጭ ከመመንተፍ ጋር በተያያዘ ይህን ችግር ከማስፋትም በላይ የመንግስት የሚስጥር ደህንነት ተቋሟች ከግለሰብ ፈቃድ እና እውቅና ውጭ የግል ስልክ ላይ ያሉ ሙሉ መረጃዎችን እንዲያገኙ በር መክፈቱ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል" ብሎ አስተያየቱን ሰጥቶኛል። 

የ Tele Birr መተግበርያ ይህን ድርጊት እየፈፀመ ነው ለማለት ማስረጃ እስካሁን የለም፣ መረጃውን ምን እንደሚያደርግበት ግን ራሱ ተቋሙ ያውቀዋል። 

ለማንኛው ቢያንስ ቢያንስ ስልኮቻችን ለተለያዩ መተግበርያዎች የ App Permission እንዳያገኙ በማድረግ ሊደርሱ የሚችሉ ችግሮችን በመጠኑም ቢሆን መከላከል ይቻላል ብዬ አስባለሁ። መጠንቀቁ አይከፋም።

Post a Comment

0 Comments