የሥነ-ተዋልዶና ጾታ "መብት" እንድንጠፋ እንድንሞት

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ

"በሥነ-ተዋልዶ ጤናና መብት" በሴቶቻችን ላይ የሚፈጸመው ክህደት፤ የሚያመክናቸው ብቻ ሳይኾን ሰውነታቸውንም የሚያጠፋ ነው!

“ውሸት” በጀማ፣ በሥልጣን፣ በዝና፣ በገንዘብም መብዛትም “እውነት” አትኾንም! እነዚህ የሌሏት “እውነትም” እነርሱን ከማጣት “ሐሰት” አትኾንም!

የምትከታተሏቸው የማትገጾች አብዛኞቹ ስለዚህ ጉዳይ ለምን ማውራት፣ ማንሳትም ለምን አይፈልጉም?

እናንተ ስለማታጋሯቸው ወይንስ...?

ለምን?
ራሳችሁንም ኾነ እነርሱን ጠይቁ!

ነገ ማጣፊያው ያጥረናል!

ብዙዎቻችሁ የዋሃን ናችሁ! የባህል፣ የእሴት፣ የእውነት ጦርነቱ የሃሳብ ልዩነት ካለን ወንድም እህቶቻችን ጋር ይመስላችኋል፤ በእርግጥ ለጊዜው በገሃድም የሚታየው እንዲያ ነው።

🚨🚨🚨 ይኹን እንጂ ነገሩን ጠለቅ ብላችሁ ብታስተውሉት “በመልካም፣ አዛኝና ተቆርቋሪ” ስም ከመጣ ነገር ግን ልጆቻችንን ሊነጥቀን ከቋመጠ፣ ካፈጠጠ የሐሰት አባት ከጨለማውም መንፈስ ጋር ነው!

እርሱን ለመዋጋት የሚያስፈልገው ደግሞ በእምነት፣ በልበሙሉነት የደረጀ አስተዋይ ልብ እንጂ እውቀትም ጡንቻም አይደለም።

እነርሱ በጭራሽ አያስፈልጉም አላልኩም! ነገር ግን ጽድቅን መፈጸም የሚችለው ለእርሱ ለጽድቁ የጨከነ፣ የወሰነ በዚያም የሚመጣበትን መከራ ለመጨለጥ የቆረጠው ልብ ያለው ብቻ ስለኾነ እንጂ።

ይሄ “የተማረው፣ የተመራመረው” ባፍጢሙ የተደፋው፣ አስመሳይነትን የተካነበት፣ ከሞቀው የሚጣደው፣ ከሰውነት ይልቅ ጥቅምን የወደደው፣ ሰው ኾኖ ተፈጥሮ ሰው መኾን ያቃተው “ልሂቅና ሊቅ” ይህን ከቶ አይችለውም!

ይኹንና ብዙዎቻችን በእነርሱ እንታለላለን! አንድም እነርሱ ብዙኃኑ የሰጣቸውን ጆሮ፣ በልቡ ያዘጋጀላቸውን ቦታ ተጠቅመው ትውልዱ እነርሱን ካመነበት እንቅልፉ እንዳይነቃ ያስተኙታል።

እውነትን መሻት፣ ለዚያም ቁርጥ ሕሊናን መሥራት፣ መከራንም መጨለጥ ዐይተናል! ምንም እንኳ ዛሬ የዚህ አርአያ ሊኾኑ የሚገባቸው “ሊቃውንት” ከመንገዱ ላይ ባይታዩም!

ይኹን እንጂ በዚህ መንገድ አስቀድሞ አብነት የኾነን አባታችንንና የእርሱን ፈለግ የተከተሉ ቅዱሳኑን እንመስላቸዋለን፤ እንከተላቸዋለንም!

አዋቂ፣ አጨብጫቢ፣ “ከእኔ ወዲያ ጠማቂ” እብሪተኛ አይፈለግም! ስለ እውነት፣ ስለ ጽድቅ ያለን ጥማት፣ ረሃብ የአባታችንንም መንግሥቱን የመናፈቅ ጽኑ ጉጉት በቂ ነው!

“...አትፍሩ... ልባችሁ አይደንግጥ...” ተብለናል!

ይህ “ልሂቃኑና ሊቃውንቱ” ዝም ሲሉ፤ አልፎ ተርፎም ከተኩላ ተሻርከው የባለቤቱን በጎቹ አሳልፈው በሚሰጡትበት ወቅት እየተፈጸመ ነውና አስተውሉ።

እርሱም ዐዲስ ነገር አይደለም! ታሪክን፦የሰውን ልጅ አነዋወሩንና አሠራሩን፤ ብታጠኑት ይህ የተለመደ አካሄዱ ነው። “ማን በየትኛው ወገን ይሄዳል?” ዕያየነው ነው!

ዛሬ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደ UN Women, UNFPA, IPPF(PPF) እና MSI (Marie Stopes) ያሉ ድርጅቶችን በመጠቀም “የሥነ-ተዋልዶ ጤና እና መብት” (SRHR) የሚል ካባ የደረበ የጥፋት አጀንዳ በሀገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያሰራጩ ይገኛሉ።

ለዚህ ጽሑፍ ግን በተለይ ሰሞኑን በሺህ የሚቆጠሩ የኢትዮጵያውያንን ልጆች “ከሀያ አምስት ዓመት” በላይ ሲያጠና ቆይቶ፣ የፖሊሲ ምክረሃሳብ አዘጋጅቶ፣ አለቆቹ ሲመጡም በጓሮ በኩል ቡና እየጠጣ ሲመክር የነበረው ያንግ ላይቭስ “ማስረጃን መሠረት ያደረገ ጥናት” ላይ ትኩረቴን አደርጋለሁ።




በዚህ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” እንግሊዛዊ አሉላ ፓንክረስት የሚመራ ተቋም የረጅም ጊዜ “ጥናቶች” ውስጥ የአንድን ምህጻረ ቃል ድብልቅልቆሽ (Inconsistency) ታያላችሁ።

እርሱም ይህ ድብልቅልቆሽ (inconsistency) ለምን እንደተፈጠረ ትኩረት መስጠት ሳያስፈልግ አይቀርም። ምክንያቱም እርሱም ከኋላ ያለውን ሸፍጥ ይገልጣልና።

ምህጻረ ቃላቱ SRH እና SRHR ሲኾኑ በአሉላ ፓንክረስት ያንግ ላይቭስ ወጥነት ባለው መልኩ አይጠቀሱም።

የመጀመሪያው SRH(Sexual Reproductive Health) የሚለው በተለይ ከኢትዮጵያ ለሚወጡት ጥናታዊ ጽሑፎች፣ የፖሊሲ ምክረሃሳቦችና የማትገጽ ዜናዎች ሲውል፤ ሁለተኛው ግን ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኾኑት በተለይ ይጠቀሙበታል።

ይህ አጀንዳ በውጭው ዓለም “ነፃነት” ቢባልም የጥፋት መንኮራኩር መኾኑ ታውቋል፤ በሀገራችንም የቤተሰብን ምሰሶ የሚነቅል፣ እናትነትን የሚያረክስ እና ትውልድን የሚያመክን የክህደት መረብ እየኾነ ነው።

እነዚህ ተቋማት ለታዳጊ ወጣቶች “ከጋብቻ በፊት ከወሲብ መታቀብ” (Abstinence) የሚለውን የሞራል እሴት እንደ ኋላቀርነት ይቆጥሩታል።

ይልቁንም ወጣቶች ገና በለጋነታቸው የወሊድ መቆጣጠሪያ እንዲጠቀሙ በማበረታታት፣ ወሲብን ያለ ኃላፊነት እንዲፈጽሙ ይገፋፋሉ።

እዚህ ላይ ነው ትልቁ ክህደት የሚፈጸመው፤ “የሥነ-ተዋልዶ የጤና አገልግሎት/ትምህርት የማግኘት መብት” የሚለው ሴቶችን ከፈጣሪ ተፈጥሮአዊ ጸጋቸው የሚነጥል መሣሪያ ነው።

ይህንንም ደግሞ በትምህርት ካሪኩለም፣ በሴቶች ማኅበራትና በጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ እንዲሠራ ይጠቁማል።

ያንግ ላይቭስ በኢትዮጵያ ሪፖርቶቹ ላይ SRH (Sexual and Reproductive Health) የሚለውን ምህጻረ ቃል ይጠቀማል። “ጤና” የሚለው ቃል ለማኅበረሰባችን መግቢያ ጭንብል ነው። በዚህ ስም፦

👉ገና ለጋ የሆኑ ታዳጊዎች “ጊዜሽን ጠብቂ” በሚል ማባበያ የወሊድ መከላከያዎችን እንደ ከረሜላ እንዲጠቀሙ ይደረጋል።

👉 እናቶች በጤና ጣቢያዎች ግዴታ እስኪመስል ድረስ የወሊድ መከላከያ በመጠቀም የሚወልዱበትን ጊዜ እንዲያዘገዩት፣ እንዲያርቁትና ኋላም መክነው እንዲቀሩ ይበረታታሉ።

👉 “ላልተፈለገ እርግዝና” ውርጃ (Abortion) እንደ “መፍትሔ” ይቀርባል። ለትምህርት ወይም ለሥራ “እንቅፋት” ነው ከተባለ፣ ማኅፀንን የመቃብር ሥፍራ ማድረግ እንደ ሥልጣኔ ይቆጠራል።

ይህ የሀገር ክህደት ነው! ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በሚገባ የሚያውቁት የምዕራባውያን እውነታ የሚያሳየው፣ ይህ “ማቀድ” የሚባለው በመድኃኒት ማኅበረሰቡን ዘር-አልባ አድርጎ ማስቀሩን ነው።

ዛሬ አውሮፓ ተተኪ ትውልድ አጥታ ስትጨነቅ፣ ያንኑ የመካንነት መርዝ “ጤና” በሚል ስም ወደ እኛ ማምጣት የትውልድ ግድያ ካልሆነ ምን ሊሆን ይችላል?

ያንግ ላይቭስ በሌሎች ሀገራት ለሚያደርገው ጥናት SRHR የሚለውን ምህጻረ ቃል ይጠቀማል። በዚያች “R” (Right - መብት) የምትለዋ ፊደል ውስጥ ትልቁ የሰይጣን ወጥመድ ተደብቋል። ይህ “መብት” የተባለው አጀንዳ ትውልዱን ከሰውነት ባሕርይው የሚያስወጣ ነው፦

👉 ትውልዱ ጾታውን (Gender) ራሱ የመምረጥና የመወሰን ሴት ወይም ወንድ፣ ወይም ሁለቱንም፣ ወይም ከሁለቱ ውጭ (Non-binary/LGBTQI+) የመኾን “መብት” እንዳለው ይሰብካል።

👉 የወሲብ ምርጫውን (Sexual Orientation) ከማን ጋር ወሲብ መፈጸም እንደሚችል (ከወንድ፣ ከሴት፣ ከሁለቱም፣ ከሁለቱም ውጪ) የመምረጥ፣ “ነፃነት” ይሰጣል።

👉 ይህ አጀንዳ በኢትዮጵያ ሪፖርቶች ላይ “R” ተብሎ ባይገለጽም፣ በተግባር ግን አባወራውን “አንባገነን” በማለትና ሴቶችን “በገዛ ሰውነታችሁ ላይ የመወሰን መብት አላችሁ” በማለት በስውር እየተተገበረ ይገኛል። ይህ “መብት” ግን የመጨረሻው የትውልዱ የቁም ሞትና ጥፋት የይኾናል!

ይህ ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ሰውን ከተፈጥሮውና ከፈጣሪው ለመለየት የመጣ የጠላት ሥራ ነው። ጠላት ሔዋንን “ከእግዚአብሔር በላይ አውቅልሻለሁ” እንዳላት ሁሉ፣ ዛሬም ያንግ ላይቭስና የብሪታንያ ፖሊሲ አውጪዎች ለልጆቻችን “ከአባታችሁ በላይ እናውቅላችኋለን” እያሏቸው ነው።

የአሉላ ፓንክረስቱ ያንግ ላይቭስ ባቀረበው “ጥናትና” ባቀበለው “የፖሊሲ ምክረሃሳብ” ላይ አባትን እንደ “መብት ገፋፊ”፣ ቤተሰብን እንደ “እስር ቤት” በመሳል ልጆቻችንን ከጥበቃችን ነጥለው ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለም አሳልፈው ይሰጣሉ።

ልብ በል! ጠላት ልጆቻችንን በእጁ አያጠፋቸውም፤ ይልቁንስ እነርሱ ራሳቸው ራሳቸውን፣ ጾታቸውንና ዘራቸውን የሚያጠፉበትን “መብት” በእጃቸው ይሰጣቸዋል እንጂ!


Post a Comment

0 Comments