✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ወንድነትን ከሶ፣ አርባወራነትን አኮስሶ ወኔቢስነትን፣ ቀላጭነትንና ጃንደርባነትን የሚያበረታታው ያልጮች ክርስትና በፍጹም ኢትዮጵያዊ አይደለም!
ዛሬ በሃይማኖት ስም የሚነገደው “ዝምታ ጥበብ ነው”፣ “ምንም ማድረግ አይቻልም”፣ “ግራህን ሲመታህ ቀኝህን ስጥ”፣ “እርሱ ያመጣውን እርሱ ይመልሰው እንጂ” ...የሚሉ አልጫዊ “ስብከቶች” የጥንቷንና የባለታሪኳን ኢትዮጵያ መንፈስ የሚወክሉ አይደሉም።
ይህ ዐዲሱ “ክርስትና” ወንድን ልጅ ስልብና አድርባይ የሚያደርግ፣ ለባርነትም የሚያመቻች የጠላት መርዝ፣ የሆዳደሮች መዘዝ ነው ነው።
በዚህ ማለትም ባልጮች ክርስትና ምዕራባውያንም ተጎድተውበታል። በእርግጥ ትውልዱን አልጫ (Demoralize) የሚያደርገው “ዘመናዊው” ስብከቱም፣ መዝሙሩም፣ የመርሐግብራት ዝግጅቱም፣ ምንጩ በአብዛኛው ታይታና ቅብጠት ቅልጠትንም የጋበዘ ባዕድ እንጂ በፍጹም ኢትዮጵያዊ ትውፊት የለውም!
የዓለም ታሪክ ጸሐፊዎች እነ ሆሜርና ሄሮዶተስ ኢትዮጵያውያንን ሲገልጡ በእነርሱም የምትጠራ ኢትዮጵያን ሲስሉ ምን ብለው እንደገለጧቸው እስቲ ጠይቁ፤ ግብረ-ገብ፣ ኩሩ፣ ጠንካራ፣ ኃይለኛና የእምነት ሰዎች እንደኾኑ መስክረዋል።
እነዚያ ጥንታውያን ሕዝቦች ለእምነታቸውና ለርስታቸው የሚቀኑ፣ የማይፈሩ፣ የማይደፈሩ፣ የጠንካራ እምነትና ስብዕና ባለቤት ነበሩ እንጂ እንደ ዛሬው ዘመን “ሊቃውንት” ለሆዳቸው የሚያድሩ፣ ትውልዱንም የሚሸጡ አልነበሩም።
ኢትዮጵያዊነትና ክርስትና ሲገናኙም ቀድሞም ግብረ-ገብና የጠንካራ ስብዕና ባለቤት የነበረው ትውልድ በዐዲሱ ኪዳን ይኸው ምግባሩ የሚያጸናለት ኾነ፣ “አርበኝነቱም” ጽድቅ ኾኖ ተገለጠ እንጂ “አልጫነት” አልተወለደም!
በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በገድላቱ፣ በምንባባቱ ውስጥ የምንሰማቸውና የምናነባቸው አባቶቻችን ከመናፍስትና ከወራሪ ኃይላት ጋር የሚዋጉ፣ ቆራጥ፣ ኃይለኛና አሸናፊዎች ነበሩ እንጂ አላዛኝና ነፍራቃዎች አልነበሩም!
አባቶቻችን በጸሎታቸው መናፍስትን ሲያርዱ፣ በተግባራቸው ደግሞ ግፍንና ክፋትን የተፋለሙ ጀግኖች ነበሩ። የእነርሱ ክርስትና ወንድነትን የሚያጸና፣ ልብን የሚያጨክንና ለጽድቅ የሚያቆም በተፈጥሮአዊ ጸጋ ላይ ሠልጥኖ የበለጸገ እንጂ ወኔን የሚሰልብ ለጃንደርባነት የሚዳርግ፣ ከሆዳደርነት ባፍጢም የሚጥልም አልነበረም።
ዛሬ የሚታየውን እንከፍ፣ ፍዝ፣ ደካማ፣ ጎስቋላ፣ አቅመ-ቢስ፣ ሰበበኛ፣ አስመሳይ፣ አድርባይ፣ አልጫ ትውልድ የሰጠን “ክርስትና” ግን ከእነዚህ አባቶች የተወረሰ አይደለም።
ይህ “ክርስትና”፦
አስመሳይና አድርባይ፦ እውነትን ለጥቅም፣ ትውልዱን በምንዳ የሚሸጥ፤
ሆዳደርና ቀላጭ፦ ታይታና ይኹንታ፣ ቅልጠትና ቅብጠት የሚሻ፤
ስልብና ጃንደርባ፦ ወንድነቱን ቀብሮ መሪነቱን ንቆ፣ ምሪትና ስምሪት ከሚስቱ የሚጠብቅ፣ መውለድ መብዛት የማይፈልግ በፈቃዱ ስልብ ዘር-አልባ የኾነ ነው።
ይህ ዓይነቱ ስብዕና በፍጹም ኢትዮጵያዊ አይደለም! እንዲያውም ኢትዮጵያዊውን ወንድ ከታሪኩ፣ ከተፈጥሮውና ከፈጣሪው ጋር ለመለየት፣ ለማጣላትና ለማጥፋትም የታቀደ “የአስተሳሰብ ነቀርሳ” እንጂ ነው።
እኛ አባወራዎቹ የምንከተለው ክርስትና የአርበኞችና የጽኑዓን አባቶችን ክርስትና ነው። ወንድነትን የሚባርክ፣ ቤተሰብንና ርስትን ለመጠበቅ የሚያስጨክን፣ ለጽድቅ ፍጻሜ ደፋር፣ ጠንካራና ሥልጡን የሚያደርግ እምነት ነው።
ዛሬ በየአደባባዩ በለስላሳና ዘገምተኛ አነጋገር፣ ተደማጭነት አገኘን፣ ተቀባይነትም በዛልን እያሉ “ወንድነትን” የሚያቃልሉ፣ ወንድነትን በተለይም አባወራነትን የሚኮንን ፕሮጀክት የሚያበረታቱ ሊቃውንት ትውልዱን ለባርነት እያዘጋጁት እንደኾነ ልናስተውል ይገባል።
ታናሼ! ኢትዮጵያዊነትህና ክርስትናህ፣ ክርስትናህና ተፈጥሮህ በፍጹም እርስ በርስ የሚጋጩ አይደሉም። ይልቁንስ አንዱ ለአንዱ መሠረትና ምሰሶ፣ መሣሪያና ኃይል፣ ትጥቅና ስንቅ ናቸው እንጂ።
ልብአድርግ!💪
“አልጫ” እንድትሆን የሚነግሩህ፣ በዜማና በጽሑፍ የሚግቱህ ሁሉ ክርስቶስን ሳይኾን ጣዖት የኾነባቸውን፦ የራሳቸውን ፍርሃት፣ “ሆዳደርነታቸውን” ነው የሚሰብኩህ። ወንድነትህን አጽና፤ አባወራነትህን አርበኝነትህንም ዐድስ!
በመንፈሳዊው ዓለም “በእነርሱማ አትምጡብኝ” እያልክ የማይነኩ፣ የማይወቀሱ፣ የማይከሰሱ ያደረግካቸውን ግለሰቦችና ተቋማት መርምር! እነርሱ እያሉ ምርታቸው-ትውልዱ “አልጫ” የኾነበትንም ነገር መርምር!
የአባቶቻችን ክርስትና በቃሉ የሚጸና የድል እንጂ የሽልጥልጥ፣ የውርደት፣ የውድቀት፣ የጉስቁልና፣ የብሶት፣ የሆዳደርነት፣ የአስመሳይነት፣ የአድርባይነትም አይደለም!
ይኹን እንጂ “ሊቃውንቱ” ትውልዱን፣ ከትውልዱም በተለይ ወንዱን፣ ከወንዱም ይበልጥ አባወራውን ከአባቶቹ መንገድ፣ ከአያቶቹም ፈለግ ለይተውት ለባርነት የሰጠ፣ የተመቸ፣ የተደላደለ ወዶገብ ባርያ እንዲኾን እያስተማሩት እንደኾነ፣ ለሚያስተምሩትም አሳልፈው እንደሰጡት ይታወቅ!
እኛ አባወራዎቹ ግን ለባርነት የተጠረገልን ያልጮች መንገድ አንሄድበትም፤ ልጆቻችንንም አንሰድበትም፣ ትውልድንም “ሂዱበት” ብለን አንመክርም!
ይህንን እንነግራቸዋለን እንጂ፦
......«ሐምሌ 22 ቀን 1928 ስምንት ወታደሮች በስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተንጠቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ «ተኩስ» በማለት ትእዛዝ ሲሰጥ ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውንና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደላቸው። .........
እርሳቸውም ይህንን ለተከታዮቻቸው ተናግረው ... ወደቁ፦
“አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተ-ክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው እንጂ በጎ ለመሥራት እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡
ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ፡፡ ነፃነታችሁ ከሚረክስ ሙታችሁ ስማችሁ ቢቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡ በፈጣሪዬ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን፡፡”
ለጽድቅ የጨከነ ድፍረት(ጥብዓት)፦
ከገዳዮቹም አንዱ “ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን?” ሲል ጠየቃቸው ፡፡ “ይህ የአንተ ሥራ ነው” ሲሉ ብፁዕነታቸው መለሱ ፡፡
0 Comments