✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ ፈተና “ባዶ ኪስ መኾን” አይደለም፤ ትልቁ ፈተና ባዶ ኪስ ይዞ ጠንካራ ስብዕናን ጠብቆ ከአስመሳይነት ርቆ መቆም ነው!
ብዙዎች የገንዘብ አቅማቸው ሲቀንስ፣ የማንነት መሸርሸር ይገጥማቸዋል። በኪሳቸው ያለው ብር ሲቀንስ፣ በሌሎች ዘንድ ያላቸውም ተቀባይነት ሲሸረሸር፣ በፊታቸው ላይ የሚለብሱት “ጭምብል” ግን እየጨመረ ይሄዳል።
ለምን? ምክንያቱም እውነተኛ ማንነታቸው የተገነባው በገንዘብ ላይ እንጂ በጠንካራ፣ የማይናቅና የማይደፈር ስብዕና ላይ ስላልኾነ ነው።
ገንዘብ ሲኖር መሪ መኾን፣ ተወዳጅ መኾን ቀላል ነው። እውነተኛው መሪነት ግን አንድም ሳንቲም በሌለበት ወቅት የሚታይ የመንፈስ ጥንካሬ፣ የዓላማ ጽናትና የልበሙሉነት ስሜት ነው።
“የለኝም” ብሎ በሐቀኝነት መናገርና ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ ማንነትን አለመሸጥ የጀግንነት “ጥርብ” ነው። አስመሳይነት የደካሞች መጠለያ ሲኾን፣ እውነት ግን የቆፍጣና እና ቆራጦች ጋሻ ናት።
ቁም! ራስክን ፈትሽ!
ልበ ሙሉነት የሚመነጨው ከባንክ ደብተር፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ፣ ከንብረት ብዛት ሳይኾን በውስጥህ በተገነባው ለጽድቅ የኾነ ማንነት ነው። ቆፍጣና ሰው ሁኔታዎች ሲቀያየሩ አቋሙን የማይቀይር ጽኑዕ ዐለት ነው።
👉 በሰው ፊት “ሞገስ ተቀባይነት ለማግኘት” ብለህ በአስመሳይነት በአድርባይነትም ውስጥ አትዘፈቅ።
👉 የራስህን እውነት ይዘህ በኩራት፣ በልበሙሉነት፣ በግርማ ሞገስ መራመድ፣ መገማሸርም አባወራዊ ቆራጥነት ነው!
አባወራነት ማለት ቤተሰብንና ራስን በገንዘብ ብቻ ማስተዳደር አይደለም፤ በአርዓያነት መምራትም ጭምር እንጂ ነው።
የገንዘብ አቅምህ ሲወድቅ ቤተሰብህ ካንተ የሚጠብቀው ተስፋን፣ ጽናትንና የማይናወጥ ማንነትህን ነው።
በዚያ ሰዓት የምታሳየው አስመሳይነት ልጆችህንና ተከታዮችህን ውሸት አድርባይነትንና ባንዳነትን ያስተምራቸዋል።
ቆፍጣና መሪ ግን “ዛሬ የለኝም፣ ነገ ግን አገኘዋለሁ፣ ባይገኝም ባለን እንጸናለን” ብሎ የሚያምንና የሚያሳምን ለዚያም የሚለፋ ነው።
ሰው መኾን የሚለካው በኪስህ ባለው ገንዘብ ብዛት ሳይኾን፣ በችግርህ ወቅት በምትጠብቀው እውነትህ፣ ቃልህ፣ ማንነትህ ነው!
ዛሬ ላይ ራስህን ጠይቅ፡ የገንዘብ አቅሜ ሲቀንስ “አስመሳይነቴ” ይጨምራል ወይስ “እውነተኛነቴን ጠብቄ እቆያለሁ”?የኋላ ታሪክህንም መውዝን! እንደ ብረት የጠነከረ ማንነት ለመገንባት ዛሬውኑ ጭምብልህን አውልቀህ በእውነት ላይ ቁም!
እውነተኛ አባወራነት በቁሳቁስ ሳይሆን በባህሪ ይገነባል!
ልብ በል፡ ባዶ ኪስህን፣ ማጣትህን ለመሸፈን የምትለብሰው ውሸት አስመሳይነት፣ ከባዶ ኪስህ በላይ ማንነትህን ያደኸየዋል፤ ሰውነትህን ያጠፋዋል!
ልበ ሙሉነትህ በኪስህ ባለ ብር አልያም በሰዎች ዘንድ ባለህ ተቀባይነት ላይ የተመሰረተ ከኾነ አንተ የእነርሱ ባሪያ ነህ እንጂ በነፃነት በአባወራነት ልዕልና ለጽድቅ አትገኝም!
አሁን ባለንበት ጊዜና ዘመን የገንዘብ የመግዛት አቅም በወደቀበት፤ የአስመሳይነት ግን ከሊቅ እስከ ደቂቁ ድረስ እጅግ አሻቅቧል! አሳሳቢ ደረጃ ላይም ደርሷል!
ራስህን ለይ!
0 Comments