በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ስም አለመተማመን በሴቷና በወንዱ መካከል ሲዘራ ቤተሰብ አይመሰረትም፤ የተመሠረተውም አይሰነብትም፤ ትውልድም ይጠፋል!
ዛሬ በሀገራችን “ማስረጃን መሠረት ያደረገ ጥናት” እና “የጾታ እኩልነት” በሚል ስም የሚረጩት ሚሊዮን ገንዘቦች አንድ ግልጽ ግብ አላቸው፦በወንዱና በሴቷ፣ በአባወራውና በቤት እመቤቷ መካከል የጥርጣሬን ግድግዳ መገንባት።
ይህ ስልታዊ “ማርክሳዊ ቀለበት” ወንድና ሴት እርስ በርስ እንደሚዋደዱ ባልና ሚስት ሳይሆን እንደ “ጨቋኝና ተጨቋኝ” እንዲተያዩ በማድረግ የቤተሰብ መሠረት ይናድ ዘንድ የሚገቡበት ወጥመድ ነው።
አንቶኒዮ ግራምሺ የኮሚኒስት አብዮትን እውን ለማድረግ ትልቁ እንቅፋት “ነባር እሴቶች፦ ሃይማኖትና ቤተሰብ” መኾናቸውን ተናግሯል።
እነዚህ ሳይፈራርሱ ሥርዓቱን መለወጥ አይቻልምም ይላል። ዛሬ ዶ/ር ሮሚና ኤስትራቲ በፕሮጀክት ድልድል በኩል፣ ዶ/ር አሉላ ፓንክረስት በያንግ ላይቭስ የሚያደርጉትም ይኽንኑ ነው።
ቀጥታ “ኮሚኒስት ነን” ብለው አይመጡም፤ ቢመጡም የሚቀበላቸው የለምና፤ ይልቁንም በቤተክርስቲያንና ቀመንግሥት መዋቅር ውስጥ ገብተው፣ የቅዱሳን አባቶችን፣ የባህላዊ እሴቶችን ትምህርት “ጾታዊ ጥቃትን ይደግፋል” በሚል ስም በመበረዝ፣ ትውልዱን ከነባር እሴቱ እንዲፋታ ያደርጉታል። ግራምሺ እንዳለው፣ ባህሉና እሴቱ የፈረሰበት ትውልድ ለባርነት የተመቸ “አልጫ” (Demoraluzed person) ይኾናል!
በዶክተር ሮሚና ኢስትራቲ የሚመራው ፕሮጀክት ድልድል (DLDL)፣ የማርክሳዊውን “የመደብ ትግል” ፍልስፍናን ወደ ትዳር ውስጥ ይዞ መጥቷል። “ጾታን መሠረት ያደረገ የቤት ውስጤ ጥቃት” በሚል ሽፋን፣ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ግንኙነት ከጨቋኝና ከተጨቋኝ የተለየ እስካይመስል ድረስ ስሎታል።
ወንዱን የምንጊዜም በዳይዋ እንጂ የልጆቿ አባት፣ መከታ አለኝታዋ አድርገው አይስሉትም። ከእርሱ ጋር መኖር ራስን ለጭቆና አሳልፎ መስጠት እስኪመስል።
በመልካም፣ ልክና ውብ መልኩ አይስሉላትምና፤ ትዳርን እንዳትጓጓለት፣ ወንዱን እንዳትተማመነው ያደርጓታል።
ሴቷን ትዳር በተባለው ተቋም ውስጥ ስለ ቤተሰብ ምሥረታ፦ በአንድነት ተዋዶ፣ ተዋሕዶና ተዋልዶ ከመኖር ይልቅ የመጠራጠርን፣ የመጠባበቅን፣ የመካሰስን፣ የመጠራጠርን፣ የመናናቅን፣ የመለያየትን መርዝ በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ሰበብ በጸረ-ጾታዊ ጥቃት ስምም ይግቷታል።
ይህንን ከልጅነቷ ጀምራ ከአስኳላ ትምህርት ቤት እስከ መንፈሳዊ ተቋማት “ስትማር”፣ የመገናኛ ብዙኃኑም ሲያጸኑላት፣ የማትገጾቹም ሲያራግቡላት የቆየችው ልጅ ወንድ ስታይ “ጃርት” ብትኾን፣ ከባልዋ ያልተስማማችበትን ሁሉ ከ”ጽታዊ ጥቃት” ብትተረጉም አይደንቅም።
መተማመን በጠፋበት፣ መጠራጠር በበዛበት ቤት ውስጥ ፍቅር አይኖርም፤ ፍቅር በሌለበት ደግሞ ቤተሰብ አይቆምም፤ ቤተሰብ ባልቆመበት ማኅበረሰብ አይገነባም፣ ማኅበረሰብ ባልተገነባበት ደግሞ ሀገር (ትውልድ) አይቀጥሉም!
ይህ አጀንዳ ዐዲስ አይደለም! ውጤቱም የታወቀ፣ የታየ፣ የተገለጠ ነው። በደቡብ ኮርያ፣ በጃፓንና በቻይና “የሴት መብት” በሚል ስም በወንድና በሴት መካከል የተዘራው ጥላቻ፣ ዛሬ ወጣቶች መፈላለግን (Dating) እና ጋብቻን እስከማቆም አድርሷቸዋል።
ወንዱ ሴቷን “በሴታቆርቋዦች (feminists) ተቋማት ጋር አብራ የምትከሰኝ፣ የምታሳድደኝ፣ አሳልፋም የምትሰጠኝ ጠላት ናት” ብሎ ሲፈራ፤
ሴቷ ደግሞ ወንዱን “ጨቋኝና አምባገነን” አድርጋ እንድታይ ተደርጋለች። ውጤቱ ምን ኾነ? ትውልድ ጠፋ! ዘር መከነ! ሀገር በሰው ድርቅ ተመታ!
ይህ ለማርክሳውያን “ያለ ምንም ደም መፍሰስ” ቤተሰብን ሀገርንም ያፈረሱበት አብዮታቸው ነውና ሰርግና ምላሻቸው ነው!
በዚሁ አንጻር እንዲሁ በእንግሊዛውያንም ኾነ! ዛሬ እንግሊዛውያን ቢባንኑም ከረፈደ ነው። ትዳር አልባ፣ ልጅ አልባና ዘር አልባ ኾነው ምድሪቱ የባዕዳን መጫወቻ ከሆነች በኋላ “ትውልዳችን ዘሩ፣ ሀገራችንም መልኳ ጠፋ” ብለው ይጮኻሉ፤ ደግሞም ከረፈደ ከመሸም የእውር ድንብራቸው ይራወጣሉ!
ይኹን እንጂ ያንኑ አልጫ(demoralize) ያደረጋቸውንና ያመከናቸውን መርዝ ዛሬ በሚሊዮን ፓውንድ በጀት ወደ እኛ ያመጡታል።
እርሱም “በማስረጃ በተደገፈ ጥናት” (evidence basede research) ለሴቷ እኩልነት፣ መብትና፣ ነፃነት እንዲኹም ጸረ-ጾታዊ ጥቃት ዘመቻ በሚሉ ካባዎች (camouflage) ትውልዳችንን እንደነርሱ ስልብ፣ ወኔቢስ፣ አልጫ፣ መካን አድርጎ ለማጥፋት መጥቷል!
የሚያሳዝነው ይህንን የማርክሳዊ ቀለበት ሴራ የሚያስፈጸሙት ባፍጢም የተደፉ የራሳችን “ዘመናዊና መንፈሳዊ” ትምህርት የቀሰሙ፣ አይነኬ፣ አይወቀሴና አይከሰሴ “ሊቃውንት” ናቸውና እጅግ ያሳፍራል!
በ”መመሪያ” ስም የሚዘጋጁት የትዳር ሥልጠናዎችና ደንቦች ወንዱን ሰልበው “አልጫ” የሚያደርጉ፣ የሚስቱ፣ ቤተሰቡ፣ የማኅበረሰቡ፣ የትውልዱ መከታ አለኝታ፣ አርአያ የኾነውን አባወራ የሚሰብሩ ናቸው።
ግራምሺ እንዳሰላው ተቋማትን ከውስጥ በመቆጣጠር ትውልዳቸውን በጽድቅ ሊያሠለጥኑና ሊያበለጽጉ የሚገባቸውን ተቋማት፦ ቤተክርስቲያንንም መንግሥትንም፤ የራሳቸው የጥፋት መሣሪያ እያደረጓቸው ነው።
ይህ ተራ ስጋት አይደለም፤ በሌሎች ዘንድ ሲኾን ያየነው፣ በቂ መረጃ ኖሮን፣ አሳማኝ ማስረጃዎችንም የሰበሰብንበት፦ነባር እሴቶችህን በማፍረስ ትውልድህን ለማለጭ (Demoralization) የመጡ ነጣቂዎችና የተባባሪ ሆዳደር ምንደኞቻቸውም ሥራ ነው።
ወንዶቻችንን ከተፈጠሩለት፣ ከተለዩለት፣ ከተጠሩለት፦ ወንድነት መክሊቱ፣ አባወራዊ ሚናውና ከሚፈጽሙበት ጽድቅ፣ ከሚያሰፍኑበትም ፍትህ እንዲርቁ፣ እንዲለዩ በጥላቻና ክስ ከተሰለቡ፤
ሴቶቻችንም በእኩልነት፣ መብትና ነጻነት ሰበብ የተሰጣቸውን ጸጋና ሚና እንዲጠየፉ፣ እንዲጠሉትና እንዳይገለጡበት ተደርገው፤ በተሠራላቸው ሥርዓት ለአባወራው ተገዝቶ፣ ታዞና አግዞ መኖርን “ከጭቆና” ተቀብለው፣ በጥርጣሬና ስጋት ተሞልተው፣ ከዚያ ይልቅ በወንዱ “ጫማ” ለመስተካከል የሚጣደፉ ከኾነ፤
🌟 ቤተሰብ ለመመስረት የሚደፍር ወጣት እናጣለን! ሁለቱም በየወገናቸው ለታይታና ይኹንታ በፉክክር ለማያሳርፍ ኑሮ የሚሮጡ እንጂ ትውልድን አምጥተው፣ ማንነታቸውን አስቀርተዎ፣ አሻራቸውን አኑረው፣ ዘራቸውን አብዝተው፣ እሴታቸውን አቀብለው መኖር የሚፈልጉ አይኾኑም!
በዚያም ትውልድ ይጠፋል! ሀገርም ቤተክርስትያንም መኖራቸው ያበቃላቸዋል!
ወንድሞቼ “ይህ በእኛ አይኾንም” አትበሉ! ትናንት እጅግ ሀገር ወዳድ፣ አርበኛ፣ ባለ ታሪክ የነበረው የደቡብ ኮርያ፣ የጃፓንም ሕዝብ እንዲሁ “ይህ ሁሉ ሚሊዮን ሕዝብ አለን፤ አይኾንብንም!” እያለ ከራርሞ፤ አሁን ግን ጥፋት ሙስናውን በቁጭት ይጨልጣልና!
0 Comments