ስውሩ አፈር | "፯ ቁጥር" ሰው የመሆን ምስጢር መፍቻ

 
"ሰባት ቍጥር እና ጥንተ ተፈጥሮ"

✍ ቲና በቀለ | ኢትዮጵያ አውታር 

ሰው ራሱ 7 ቁጥር ነው፡፡ ጥንታውያን የኢትዮጵያ ተመራማሪና ተፈላሳፊ ሊቃውንት፣ የጥናትና የምርምር ማዕቀፋቸው የሚያተኩረው ሰው ላይ ነበር፡፡ አንድን መንጋ ንብ ለመያዝ እያንዳንዱ ሠራተኛ ንብ ላይ መልፋት ሳይኾን አዋጪው ብልሀት፣ አውራውን መያዝ ነው የሚለው ንጽጽር፣ ሰው ከተሠራ ሌላውን ማለትም መንፈሳዊውንና ዓለማዊውን ነገር ኹሉ ሰው ራሱ ይሠረዋል፤ ከሚል መነሻነት እንደኾነ ብዙ ምሁራን ይስማማሉ፡፡ ‹ያልተገነባ ጭንቅላት የተገነባ ከተማን ያፈርሳል!›› እንዲሉ ባልተሠራ ሰው መኃል ሕንጻ ቢገነባ፤ ባቢሎን ቢሠራ፣ መንገድ ቢጥመለመል፣ ሀገር በሚመኝዋት ልክ ካርታ ላይ ብትሣል… የተሳለችበትን የካርታ ወረቀት ኾና ትቀራለች፡፡ ሕግ ቢረቀቅ፣ ለኅትመት የዋለውን ወረቀት ያክል ዋጋ እንኳን ሳይኖረው የአቧራ መደበቻ ኾኖ ይቀራል… ወዘተ. ወዘተ. በሚል መነሻነት የሰው ልጅ ግንባታ ላይ ለፍተዋል፡፡ በመልካም ሥነ-ምግባር የተገነባ ሰው፣ እንኳንስ የተገነባ ሀገር አግኝቶ ይቅርና እንደ ሕዝበ እስራኤል የተበታተነች ሀገር ቢያስረክቡትም መልሶ መገንባት ይችላል፡፡
‹‹እስመ ኁልቈ ፯ቱ በኀበ ዕብራውያን ፍጹም ውእቱ፡፡›› ሰው ማለት በዕብራውያን ዘንድ ሰባት/ሳብእ ፍጹም ቁጥር ማለት ነው፡፡›› እንዲል መጽሐፈ አቡሻኽር። ሰው፣ ሰው የሚሆነው የሰባቱ ድምር ውጤት ማለትም አራቱ ባሕርያተ ሥጋና ሦስቱ ባሕርያተ ነፍስ ያሉበት ሲኾን ነው፡፡

ሰው ባሕርያተ ሥጋው ሲያሰንፈው ባሕርያተ ነፍሱ ያነቃዋል፡፡ በሥጋው ይተኛል፤ በነፍሱ ደግሞ ይነቃል፡፡ ሥጋው ዕረፍትን ሲይሻ ነፍሱ ትጋትን ታለብሰዋለች፤ ታጎናጽፈዋለችም፡፡ በዚህ ምክንያት ተቃራኒ ነገሮች ሲፈራረቁበት የሚኖር ፍጡር ኾኖ እናገኘዋል፡፡ ለዚህ ነው እስስታዊ ፀባይ ያላቸውን ሰዎች “አንዴ ሰው አንዴ አፈር ያደርገዋል” የምንላቸው፡፡ ይህ ወደ ተለዋዋጭ የሰዎችን ጠባይ ለመግለጥ የምንጠቀምበት አባባል ነውና የሰውን ልጅ ከግብራቱ መካከል አንዱ የኾነውን ጠባዩን ያሳየናል፡፡ አንድን ሰው “እንዴት እንደዚህ ይለኛል!? እንዴት እንደዚህ ያደርጋል!?” የምንለው ይኖራል፡፡ ሊያሸማግለን የሚሞክር ሰው ደግሞ፥ ‹መቼስ ሰው አይደል!? ሰው እኮ ደካማ ነው፤ ሥጋ ለባሽ ነው፡፡›› ይለናል፡፡ሥጋ ለባሽ ነው ሲለን፣ ሥጋ የለበሰው ምንድነው? ስንል ነፍስ የሚል መልስ ይሰጠናል፡፡ ለዚህ ነው ሰው ነፍስና ሥጋ ነው፡፡ ሥጋው አራት ባሕርያት ሲኖሩት ነፍሱ ደግሞ ሦስት ባሕርያት ይዘው በድምሩ ሰባቱ ባሕርያት ናቸው ሰው ያደረጉት፡፡ በመኾኑም ሰው ሰባት ቍጥር ነው፤ ፍጹም ሰባት ነው የሚለውን የዕብራውያኑን አባባል መሠረት አድርጎ መጽሐፈ አቡሻኽር የተነተነው፡፡

የ "7" ቁጥር ነገር እጅግ በጣም የሚያስደንቅ። በጥቅሉ አለም የተፈጠረችው በቁጥር ነው። እግዚአብሔር ሰማይና ምድር ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐረፈ። ሰባተኛዋን ቀን ባረካት፤ ቀደሳትም፤ ሊፈጥረው ከጀመረው ሥራ ሁሉ በእርስዋ ዐርፎአልና።

እስካሁን በዓለም ላይ ከ900 አመት በላይ የኖሩ ሰዎች 7 ብቻ ናቸው።

1.አዳም 930 አመት
2.ሴት 912 አመት
3.ሄኖስ 905 አመት
4.ቃይናን 910 አመት
5.ያሬድ 962 አመት
6.ማቱሳላ 969 አመት
7.ኖኅ 950 አመት

አዳም የተፈጠረው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ተብሎ ይታመናል። የአፈር ዝርያዎች በራሱ 7 ናቸው። ከሰባቱ አዳም የተፈጠረው " ስውሩ አፈር" በተባለው ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይገኛል። አፈሩ ከተገኘ ፍቱን መድሀኒት ነው ይባላል።

እግዚአብሔር አዳምን ፈጠረ፣ አዳም ሴትን ወለደ የኖረበት ዘመን 930 ዓመት ሆነ ሞተም።

ሴትም ሄኖስን ወለደ፣ የኖረበት ዘመን 912 ዓመት ሆነ ሞተም።

ሄኖስም ቃይናንን ወለደ፣ የኖረበት ዘመን ሁሉ 905 ዓመት ሆነ ሞተም።

ቃይናንም መላልኤልን ወለደ፣ የኖረበት ዘመን 910 ዓመት ሆነ ሞተም። ልጁ መላልኤልም ያሬድን ከወለደ በኋላ 895 ዓመት ሆነ ሞተም። መላልኤል 900 ዓመት አልሞላውም።

ያሬድም ሄኖክን ወለደ፣ የኖረበት ዘመን ሁሉ 962 ዓመት ሆነ ሞተም። ሄኖክ በምድር ላይ የኖረበት ዘመን 365 ዓመት ሲሆን ከዛ በኋላ በበጎ ሥራው እግዚአብሔር ሰውሮታል። ሄኖክ በራሱ ከአዳም ጀምሮ 7ኛ ትውልድ ነው። በገነትም ሰባቱን ሰማያት አይቷል።

1. ጽርሐ አርያም
2. መንበረ መንግስት
3. ማይ-ውዱድ
4. ኢየሩሳሌም-ሰማያዊት
5. ኢዮር
6. ራማ
7. ኤረር የሚባሉትን።

ሄኖክ ከመሰወሩ በፊት ማቱሳላን ወለደ፣ ማቱሳላም ላሜሕን ወለደ። የኖረበት ዘመን 960 ዓመት ሆነ ሞተም።

ላሜሕም ኖኅ'ን ወለደ ላሜሕ የኖረበት ዘመን 747 ዓመት ሆነ፤ሞተም።

#ኖኅም 3 ልጆችን ወለደ፤ እነርሱም ሴም፥ካምና ያፌት ናቸው። በኖኅ ዘመን በሰዎች ክፋት ምድር በማየ አይኅ ተደመሰሰች። ከ40 ቀን በኋላ ምድር ደረቀች። ኖኅ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አቀረበ፤ እግዚአብሔርም ለኖኅ ቃል ኪዳን ሰጠው። ኖኅም ከጥፋት ውኃ በኋላ 350 ዓመት ኖረ። በጠቅላላ የኖረበት ዘመን 950 ዓመት ሆነ ሞተም።

እናም እስካሁን በምድራችን የ7ቱን ሰዎች ያህል ከ900 ዓመት በላይ የኖረ የለም ወደፊትም አይኖርም።

ለምን❓ለእናንተ የምተወው የቤት ስራ ይሆናል❓

ይህ ብቻም አይደለም የ"7" ቁጥር ምስጢራት"❗

ሰባት ቁጥር ጥልቅ ምሳሌና ትርጓሜ አለው። በዕብራውያን ዘንድ ሰባት ቁጥር፦

ፍጹም ቁጥር ነው። እግዚአብሔር ከሰኞ እስከ ዕሁድ ያሉትን ቀናት በሰባት ቁጥሮች ወስኗል። (መ.ምሳሌ 24፥16)

- እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነጻ ወጥተው በሲና በረሃ ሲጓዙ ይመሩት የነበረው በሰባት ደመና ነበር። (ዘዳ 13፥21)

- እስራኤላውያን ኢያሪኮን ለሰባት ተከታታይ ቀናቶች እንዲዞሯት፣ በሰባተኛው ቀን ደግሞ ሰባት ጊዜ እንዲዞሯት ታዘው ነበር። (ኢያሱ 6፥15)

- ጴጥሮስ ወንድሙን ይቅር እንዲለው የታዘዘው እስከ ሰባ ሰባት ጊዜ እንጂ ሰባት ጊዜ ብቻ አልነበረም። (ማቴዎስ 18፥21, 22)

- ሌላው የሰባት ቁጥር ምሳሌዎች በጥቂቱ እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

ሰባቱ አባቶች❗

1. ሰማያዊ አባታችን እግዚአብሔር
2. የነፍስ አባት
3. ወላጅ አባት
4. የክርስትና አባት
5. የጡት አባት
6. የቆብ አባት
7. የቀለም አባት

ሰባቱ ዲያቆናት❗

1. ቅዱስ እስጢፋኖስ
2. ቅዱስ ፊልጶስ
3. ቅዱስ ጵሮክሮስ
4. ቅዱስ ጢሞና
5. ቅዱስ ኒቃሮና
6. ቅዱስ ጳርሜና
7. ቅዱስ ኒቆላዎስ

ሰባት የጌታ ቃላት(እኔ ነኝ)❗

1. የሕይወት እንጅራ እኔ ነኝ
2. የዓለም ብርሃን እኔ ነኝ
3. እኔ የበጎች በር ነኝ
4. መልካም እረኛ እኔ ነኝ
5. ትነሣዔና ሕይወት እኔ ነኝ
6. እኔ መንገድና ሕይወት ነኝ
7. እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ

ሰባቱ_ሰማያት❗

1. ጽርሐ አርያም
2. መንበረ መንግሥት
3. ሰማይ ውዱድ
4. ኢየሩሳሌም ሰማያዊት
5. ኢዮር
6. ራማ
7. ኤረር

#ሰባቱ_ሊቃነ_መላእክት❗

1. ቅዱስ ሚካኤል
2. ቅዱስ ገብርኤል
3. ቅዱስ ሩፋኤል
4. ቅዱስ ራጉኤል
5. ቅዱስ ዑራኤል
6. ቅዱስ ፋኑኤል
7. ቅዱስ ሳቁኤል

ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት❗

1. የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን
2. የሰርምኔስ ቤተ ክርስቲያን
3. የጴርጋሞን ቤተ ክርስቲያን
4. የትያጥሮስ ቤተ ክርስቲያን
5. የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን
6. የፊልድልፍልያ ቤተ ክርስቲያን
7. የሎዶቅያ ቤተ ክርስቲያን

ሰባቱ ተዐምራት❗

ጌታ የሰው ልጆችን ለማዳን በመስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ የተፈጸሙ ተዐምራት፦

1. ፀሐይ ጨልሟል
2. ጨረቃ ደም ሆነ
3. ከዋክብት ረገፉ
4. ዐለቶች ተሠነጠቁ
5. መቃብራት ተከፈቱ
6. ሙታን ተነሡ
7. የቤተ መቅደስም መጋረጃ

ሰባቱ የመስቀሉ ቃላት❗

1. አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ
2. አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው
3. ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትሆናለህ
4. እነሆ ልጅሸ እናትህ እነሆት
5. ተጠማሁ
6. ተፈጸመ
7. አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እስጥሃለሁ

ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተክርስቲያን❗

1. ምሥጢረ ጥምቀት
2. ምሥጢረ ሜሮን
3. ምሥጢረ ቁርባን
4. ምሥጢረ ክህነት
5. ምሥጢረ ተክሊል
6. ምሥጢረ ንስሐ
7. ምሥጢረ ቀንዲል

ሰባቱ ዐበይት አጽዋማት❗

1. ዐቢይ ጾም
2. የሐዋርያት ጾም
3. የፍልሰታ ጾም
4. ጾመ ነቢያት
5. ጾመ ገሀድ
6. ጾመ ነነዌ
7. ጾመ ድኅነት

 ሰባቱ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠሉ ነገሮች❗

1. ትዕቢተኛ ዓይን ምሳ ( 16፥6-19)
2. ሃሰተኛ ምላስ
3. ንፁህን ደም የምታፈስ እጅ
4. ክፉ ሃሳብን የምታፈልቅ ልብ
5. ለክፋት የምትፈጥን እጅ
6. የሐሰት ምስክርነት
7. በወንድሞች መካከል ጠብን የምታፈራ ምላስ

ሰባቱ ፀሎት ጊዜያት❗

1. ነግህ የጠዋት ጸሎት
2. ሠለስት (የ3 ሰዓት ጸሎት)
3. ቀትር (የ6 ሰዓት ጸሎት)
4. ተሰአቱ (የ9 ሰዓት ጸሎት)
5. ሰርክ (የ11 ሰዓት ጸሎት)
6. ነዋም (የምኝታ ጸሎት)
7. መንፈቀ ሌሊት (የሌሊት ጸሎት)

"ለጠቢብ አሀቲ ቃል ትበቁእ"!
"ለጥበበኛ ሰው አንድ ቃል ትበቃዋለች"!

Post a Comment

0 Comments