የአርማጌዶን ጦርነት! ትርክት እና እውነት? አርማጌዶን ራእይ=16፣16

 ተስፋዬ ገቢሳ (ክንፈ ሚካኤል)    
                            
ስለ አለም መጨረሻ ከሚያስተምሩት ብዙዎች፡ አርማጌዶን፡ በመጨረሻው ዘመን የውጊያዎች ሁሉ ውጊያ የሚካሄድበት ቦታ ነው ይላሉ። 

ይህ የምጽዓተ ዓለም ትምህርት በአብዛኛው የሚቀነቀነው፡ በምጽሐረ ቃል D.P.P.Zism "  ወይም " Dispensational, Pre-Tribulation, Pre-Millenial, Zionism፡ በሚባሉት በተለይ በአሜሪካ በሚገኙት፡ የክርስቲያን ጽዮናውያን፡ አማኞች፡ እና በጴንጤቆስጣል  ፕሮቴስታንት ዘንድ ነው።  በአጭሩ እምነታቸውን፡ ዘርዘር አድርገን ስንመለተው የምናገኘው፡ የሚከተለውን ሐሳብ ነው።     

Dispensationalism፡ በአማርኛ " ሥፍረ ዘመናውያን" ይባላሉ። ይህም እግዚአብሔር አለምን ለማዳን በሰባት ዘመን ሰፍሮ አስቀምጧል። አሁን ያለነው ሰባተኛው ስፍረ ዘመን ላይ ነው፡ የሚል ነው። በዚህ በሰባተኛው ስፍረ ዘመን ላይ ከሚከናወነው፡ አለም አቀፍ ክስተት ውስጥ አንዱ ጎግ እና ማጎግ፡ እስራኤልን ለማጥፋት፡ በአርማጌዶን፡ ታላቅ፡ ጦርነት ይካሄዳል። ኢራን፡ቱርክ፡ራሺያ፡ቻይና፡ እስራኤልን ለማጥፋት ይነሳሉ፡ መሲሁ ይታደጋቸዋል የሚል ነው።                      

ይህ አስተምህሮ የሰው እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ አይደለም።                     
 
አርማጌዶን የተባለ የውጊያ ቦታ ወይም መካነ ድምሳሴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጭራሽ የለም።           
አርማጊዶን የሚባል ቦታ፡ በጥንት የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ጥናት ይሁን ታሪካዊ ጽሑፎች፡ የማይታወቅ ሲሆን፡ በጥንትም ይሁን በዘመናዊው፡ የመሬት ካርታ ላይ የሚታወቅ ቦታ አይደለም።                  

በጥንቱ የዕብራውያን ቋንቋ ሃር መጊዶን የሚለው ቃል ይህ ነው የሚባል ግልጽ ትርጉም የለውም። በጣም የቀረበ ተብሎ የተሰጠው ትርጉም የመጊዶ ተራራ ሲሆን፡ ይህን የሚገልጽ ተራራማ ቦታ ፈጽሞ አልተገኘም።                                  

መጊዶ የሚባል ሸለቋማ ሥፍራ፡ ለቀርሜሎስ ተራራ፡ በቅርበት የሚገኝ፡ ሲሆን፡ በ2ኛ ዜና=35፥22፣ መሣ= 5፣19-22፣ ዘካ=12፣11፣ 2ኛ ነገ=9፣27፣ እና 2ኛ ነገ=23፣29  የተገለጸ፣ ብዙ ጦርነት የተካሄደበት ፣ ሲሆን ንጉሥ ኢዮስያስ፡ የተሸነፈበትና፡የሞተበት፣ ጌድዮን ሚድያማውያንን ድል ያደረገበት፣ ኢዩም አካዝን የገደለበት፣ ሥፍራ፣እንደሆነ ተገልጿል።                                                 
በዚህ የተነሳ፡ አርማጌዶን በራእይ ዮሐንስ የጥፋት፡ የመቅሰፍት፡ የመአት፡ እና የአደጋ ተምሳሌት ሆኗል።  

አርማጌዶን የኃያሉ አምላክ በታላቁ ቀን ውጊያ፡ እስራኤልን፣ ከባዕድ ወራሪያን ለመታደግ፣ በመጊዶ ተራራ ላይ ይሆናል የሚለው ብሂል፡ ታሪካዊ አውዱን ያልተከተለ፡ በጥንታዊ አባቶችም፡ ሊቃውንት፡ የማይታወቅ፡ እሳቤ ነው።                                         

ከመጽሐፍ ቅዱስ አውዳዊ እሳቤ ስንነሳ፡ አርማጌዶን የሚለው አጠራር፡ ለሃር ሚግዶ ( ፍሬያማ ተራራ፥ ለሚባለው  ለጽዮን ተራራ፡ ( Mount Zion) የቀረበ ነው።

በዮሐንስ ራእይ መጽሐፍ የተወሰዱ ብዙ ምስላዊ ( Imagery): አገላለጽ፡ ከትንቢተ ኢዩኤል ጋር ተመሳሳይ ናቸው። 

ይህም እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከክፋት ኃይላት ጋር  የሚያደርጋቸው ውጊያዎች፡ ሁልጊዜም የሚወጡት ከጽዮን ተራራ፡ ነው። 
                                              
ተራራዎች መንፈሳዊ  ነገሮችን ለመግለጥ ብዙ ጊዜ ጥቅም ላይ ይውላሉ።                                                   
የተራራ ጫፍ፡ ለመንፈሳዊ ውጊያ ተመራጭ ተምሳሌታዊ ቦታ ሲሆን፡ የእግዚአብሔር ሕዝቦችም ታላላቅ ድልን የተቀዳጁበት ነው።                                          

አርማጌዶን የሚለው ቃል ብዙ በምሳሌያዊ ንግግሮች በተሞላው የራእይ ዮሐንስ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ፡ ሲሆን፡ ይህም ቀጥታ ቃል በቃል ከሚወሰድ ይልቅ፡ የበለጠ ተምሳሌታዊ ትርጉም ያለው ነው።  

በ2ኛው ክ/ዘመን የልዮን ግዛት ሊቀ ጳጳስ የነበረው፣ ቅዱስ ሔሬንየስ አርማጌዶን ማለት የሌቦች ተራራ ነው በማለት የተናገረ ሲሆን ይህም ሐሳዌ መሲህ የእግዚአብሔርን ክብር የሚሰርቅ መሆኑን የሚገልጽ ነው፡ በማለት ያብራራዋል።

በ6ኛው ክ/ዘመን፣ የዮሐንስ ራእይን አንድምታ የጻፈው የቂሳሪያው ሊቀ ጳጳስ እንድሪያስ አርማጌዶን ማለት መቁረጥ ወይም የተቆረጠ በማለት ተርጉሞታል።

በመጽሐፍ ቅዱስ የትም ቦታ የአርማጌዶን ውጊያ የሚል ክፍል የለውም።

አርማጌዶን በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ አንድ ጊዜ፡ በፈረሶች፡ በታንኮች፡ በሚሳይሎች፡ በኑክሊየር ቦንብ፡ በወታደሮች፡ በ21ኛው ክ/ዘመን፡የሚደረግ ታላቅ ውጊያ፡ አድርጎ ማየት፡ የመጽሐፉን ሐሳብ ያለመረዳትና፡ በ1ኛው ክ/ዘመን ለተጻፈላቸው፡ ሰዎች ተደራሽነቱን ዋጋ ማሳጣት ይሆናል።                                    

የአርማጌዶን ተምሳሌነቱ፡ በተመረጡት የእግዚአብሔር  አሸናፊ፡ ሕዝቦች  እና፡ የክርስቶስን መገለጥ በሚቃወሙ መካከል ( The Battle Between Good and Evil): ፡ በመካሄድ ላይ ያለውን የቅራኔ፡ እና የግጭት ቦታን የሚገልጽ ነው።                            

ይህም ውጊያ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚካሄድ፡ መንፈሳዊ ጦርነት እንጂ፡ በሰው ሠራሽ መሣሪያ በሚሳኤል፡ በጀት እና በኑክሊየር ቦንብ የሚደረግ አይደለም።                 

ብዙዎች በዘመናችን፡ በተነሱ፡ ሐሰተኛ መምህራን የነቢያት መጻሕፍትን በመተርጎም ሊቅ ነን (Dooms Day Prophecy Pundit): በሚሉ፡ ነገር ግን፡ የዮሐንስ ራእይ እና የትንቢት መጻሕፍትን ሐሳብ፡ መቼት፡ በዘመናችን ከሚሆኑ ክስተቶች ጋር በማያያዝ፡ የዋህ ክርስቲያኖችን፡ አለም በዚህ ቀን ትጠፋለች፡ ሐሳዌ መሲህ በዚህ ተገለጠ፡ በዚህ ታየ፡ በማለት፡ ያወዛግቡበታል። 

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ሐሳዌ መሲህ (የክርስቶስ ተቃዋሚ)፥ ያልነበረበት ዘመን የለም። በፊትም ነበር፡ አሁንም፡ አለ፡ ለወደፊት፡ ወደ ጥልቁ ባህር እስኪጣል ድረስ ሰዎችን በማሳት ይኖራል።                   
ቤተ ክርስቲያን በአርማጌዶን ተምሳሌት የተነገረችው፡ የክፋት እና የበጎ ኃይላት ፍልሚያ የሚያደርጉባት ቦታ ስለሆነች ነው።                              

ብዙ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች፡ አንዳንድ መምህራንን፡ ጨምሮ፡ አርማጌዶን በሚባል ቦታ፡ ጎግ እና ማጎግ ተብለው የተሰየሙት፡ ራሺያ፡ ቱርክ፡ ቻይና፡ እና የአረብ ሐገራት፡ በጋራ ሆነው፡ እስራኤልን ሊወጉ ይመጣሉ። 

ቻይና 200 ሚሊዮን ፈረሰኞች ወታደሮች ይዛ፡ የኤፍራጥስ ወንዝን ስትሻገር ወንዙ ይደርቃል። አርማጌዶን፡ በሚባል ስፍራ ታላቅ ውጊያ ይሆናል፡ ጌታ ኢየሱስ ለእስራኤል ወግኖ፡ ጠላቶቻቸውን ሁሉ ያጠፋል፡ ምድሪቱ፡በሬሳ ትሞላለች፡ የጦር መሣሪያውን ማገዶ አድርገው ለሰባት አመት ይጠቀሙታል፡ በየመንገዱ የወደቁ አስክሬኖችን ወፎች ይበሉታል፡ የተቀረውን ለመቅበር፡ ለሰባት አመት ሰዎች ተቀጥረው ይቀብራሉ። 

ሐሳዌ መሲህም ይገደላል፡ ከዛም ጌታ ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለአንድ ሺህ አመት ይነግሳል በማለት፡ከዚህም ከዛም የተቀነጣጠቡ ጥቅሶችን ( Proof Texts)  ሙሉ፡ አውዱ፡ ሙሉ ታሪኩ፡ ከግምት ውስጥ ሳይገባ፡ በዘፈቀደ፡ ሲያስተምሩ ይታያል።                    

ይህ የሐሰት ትምህርት፡ በአማኞች፡ መንፈሳዊ፡ ማኅበራዊ፡ ፖለቲካዊ፡ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ ልቦናዊ ህይወት ላይ ስጋትን፡ እና አላስፈላጊ ፍርሀትን፡ አለመረጋጋትን የፈጠረ መሆኑ የታወቀ ነው።                                     
በተለይ አብዛኛው፡ የአሜሪካ ኤቫንጄሊካል ፕሮቴስታንት አማኞች፡ጌታ፡ኢየሱስ፡ በቅርቡ በስውር፡  ይመጣል። ድንገት፡ ተነጥቀን ( Caught up): ልንወሰድ: ወይም ደግሞ በዚህ ምድር ላይ በመቅረት ( Left Behind): ለሐሳዌ መሲህ ተላልፈን፡ በመሰጠት፡ ለሰባት አመት ፡ታላቅ መከራ: ይደርስብናል፡ ከዛም፡ በአርማጌዶን ጦርነት እንጠፋለን፡ በማለት በማያቋርጥ ድባቴ (  Depression): ውስጥ የሚኖሩት፡ በጣም ብዙ ናቸው።                                     

ስለ አርማጌዶን የተነገረበትን የምንባብ ክፍል፡ በጥንቃቄ፡ አውዱን፡ ጠብቀን ካነበብን፡ ውጊያው የሚደረገው፡  በራእይ=16፥13-14 ላይ ከተገለጹት፡ ከዘንዶው ( ሰይጣን)፡ከአውሬው (በሰይጣን ሥልጣን፡እና ኃይል የሚሰራው የአመጽ ሰው የተባለው፡ ሐሳዌ መሲህ)፥ እና ከሐሰተኛው፡ነቢይ ( የሐሳዌ መሲህ መንገድ ጠራጊ)፥ አፍ ከሚወጡት፡ ሶስት ጓጉንቸር፡ ከሚመስሉ ርኩሳን መናፍስት ጋር ነው እንጂ፡ እስራኤል፡ ከጎግ ማጎግ ጋር ጦርነት ታደርጋለች የሚል፡ ሐሳብ፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የለም።                    

ሶስቱ ጓጉንቸር የሚመስሉ፡ ርኩሳን መናፍስት እነማን ናቸው?                  

በሶስት ጓጉንቸር፡ የተመሰሉት፡ ርኩሳን መናፍስቶች፡ የምድር ነገሥታትን፡ በሐሰተኛ ተአምር እና ምልክቶች፡ አሰባስበው፡ በክርስቲያኖች፡ እና በጌታችን ኢየሱስ ላይ፡ የጥፋት ዘመቻ  (አርማጌዶን)፥ የሚታስከትቱ፡ የወደቁ፡ አጋንንት ናቸው።                    

በክርስቶስ የሚያምኑ፡ ክርስቲያኖች ይህንን፡ዕለት ተዕለት፡ ከክፋት ኃይላት ጋር ለሚደረገው፡ ግብግብ፡ ቁርጠኛ፡ተዋጊዎች፡ መሆን ያለብን ሲሆን፡ አሰላለፋችን፡ ከእግዚአብሔር ኃይላት ጋር መሆን አለበት።                           
ከአርማጌዶን ተምሳሌታዊ አገላለጽ የምንረዳው፡የክርስቶስ ቤተክርስቲያንን ለመቆጣጠር፡ በተነሳው፡ የክፋት ኃይላት ላይ የእግዚአብሔር፡ ቅጣት፡ አሳማሚ መሆኑን ነው።   
             
ይህ መንፈሳዊ ውጊያ የክፋት ኃይላት መሪ ከሆኑት በሐሳዌ መሲህ፡ በስይጣን እና፡ በክርስቲያኖችና በመሪያቸው በክርስቶስ ኢየሱስ መካከል የሚደረግ ሲሆን ፡ ጥንተ ጠላት ለአንዴና ለመጨረሻ የሚሸነፍበት፡ ውጊያውም የሚደመደምበት ነው።          

ይህንን የአርማጌዶን፣ ውጊያ የጎግ እና ማጎግ መንግሥታት በዘመናዊቱ እስራኤል ( በጽዮናውያን፣ መንግስት፣ ላይ የውጊያ ክተት የሚያውጁበት ነው ብሎ መተርጎም፡ የተገለጠ ስህተት ( Categorical Mistake)፣ ከመሆኑም ባሻገር፣ ባለ ራእዩ ቅዱስ ዮሐንስ ለጻፈላቸው ለ1ኛው፣ ክ/ዘመን፣እና  ከዛ በሁዋላ ለተነሱት፣ ለጥንት፣ ክርስቲያኖች ተደራሽነቱን ከግምት ውስጥ የማያስገባና፣ ሙሉ መልዕክቱን፣ የሚያዛባ ነው።

በተለይ በአሜሪካ ከ19ኛው ክ/ዘመን በሁዋላ በፕሮቴስታንት፣ ታላላቅ የመገናኛ፣ ብዙኅን፣ በሐሰተኛ ነቢያቶችና መምህራን፣ የዮሐንስ ራእይን፣ በዘመናችን ከሚከሰቱ ወቅታዊ ፖለቲካዊ፣ኢኮናሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ሥነ ምግባራዊ፣ እና ማኅበረሰባዊ፣ ችግሮች ጋር በማዛመድ፣ መጽሐፉ ያልተናገረውን፣ ሊናገረው ያላሰበውን፣ ከታሪካዊና፣ ባህላዊ አውዱ፣ በመውጣት፣ የአለም ፍጻሜ፣ በዚህ ቀን ይሆናል፣ የጌታ መምጫው፣ በዚህ ጊዜ ነው፣ እያሉ ሲያስፈራሩበት፣ ይስተዋላል።

የአርማጌዶን ውጊያ፣ ጥንተ ጠላታችን ከሆነው ከሰይጣን፣ ከሐሳዌ መሲሁ እና ሠራዊቶቻቸው ( ርኩሳን መናፍስት ) ጋር የምናደርገው፣ የጥፋት ኃይላት፣ የሚደመሰሱበት፣ የመጨረሻው፣ የመንፈሳዊ ውጊያ እንጂ፣ ምድራዊ እና በሥጋዊ ሐሳብ የተሞሉት፣ ሐገራት፣ ለኢኮኖሚያዊ የበላይነት፣ እና ለፖለቲካ ፍጆታ፣ በሰው ሰራሽ፣ አውዳሚ መሣሪያ፣ የሚያደርጉት ውጊያ አይደለም። 

በዘመናችን ያሉት ከአብርሃም በዘር፣ የማይዛመዱት፣ ራሳቸውን፣ የእስራኤል መንግስት የሚሉት፣ ከኢራንም፣ ይሁን ከራሺያ ጋር የሚያደርጉት ጦርነት፣ ከአርማጌዶን ውጊያ ጋር ምንም ግንኙነት፣ የሌለው፣ እና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር የሚያገኛኘው፣ እንደሌለ አውቀን፣ በክርስትናችን ጸንተን፣ ውጊያችን፣ ከሰይጣንና፣ ከክፋት መናፍስት፣ አሰራር ጋር መሆኑን 

አውቀን፣ በንስሐ ህይወት፣ በመመላለስ፣ በጊዜውም ባለ ጊዜውም ጸንተን፣እንገኝ።
ጎኛ ማጎግ እነማን ናቸው?

በዘመናችን ያሉት ሐገረ እስራኤል፣ የተመረጡት ሕዝቦች ናቸው ወይስ፣ በምዕራብ፣ አለም የተፈጠሩ፣ የሴራ ውጤቶች? 

ይቆየን፣ ይቀጥላል።

ማራናታ!  " ጌታ ሆይ በቶሎ ና "

Reference:- ምንጭ

-  ምጽአተ ክርስቶስ።  ገጽ= 278-279

-  የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት አንድምታና ትርጓሜ። ገጽ= 448-449

- The Apocalypse Conspiracy. P=135-146.

-  The Truth About Armageddon. P=135-143.

-  Sacra Pagina. Revelation. P= 167.

-   Antichrist, Armageddon, and the Mark of the Beast: Antichrist's Identity Revealed .P=81-83.

-  Your Bible Questions Answered. P= 241-242.

- Guiding to the Blessed End. Andrew of Caesarea  and His Apocalypse Commentary in the Ancient Church. P=267.

-  The Hope of the early Church. A Handbook of Patristic Eschatology.
-  Apocalypse. Early Church Fathers and the Early Church.     
           
-  Armageddon. What the Bible Really Says About the End. Prof. Bart Ehrman.   
         
-  The Antichrist. The Final Campaign Against the Savior. Fr. Vincent Miceli, S.J.

- Approaching Armageddon. Discover  Hope Beyond Earth's Final battle. Steve Wohlberg.

-  Exploding the Deception of Israel. Steve Wohlberg. P= 105-111                                     
-  The Didache. Faith, Hope and Life of the Earliest Christian Communities 50-70 A.D. Prof. Aaron Milavec.                                          



Post a Comment

0 Comments