ትውልድ የሚታነጽበት ሀገር የምትገነባበት የወንድነት ልኩ አባወራነት

 

ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ትውልድ በጠንካራ ስብዕና ላይ ሲገነባ፣ የማኅበረሰቡ አንድነትና ውህደት ውልደትም ይጨምራል። አለበለዚያ ግን ብሶተኛ፣ ለቀስተኛ፣ ጎስቋላና መካን ይኾናል!

ማርክሳውያን (ግራዘመሞች) በተለይም ራሱ ካርል ማርክስ በጽሑፎቹ እንደገለጠው እግዜርን አይወደውም ነበርና፤ እርሱ የሠራውን ቅጥ፦ በሰማይ እንዳለው በምድርም የመሠረተውን ያስቀጠለውን ሥርዓት ኮንኖ ያፈርሰው ዘንድ ጽፏል።

አባትነትን፣ አባት መር ሥርዓትን፤ በዚያም ያለ ቅጡን፣ ሕጉን፣ ወጉን፣ እውነቱን፣ እምነቱን፣ እሴቱን፣ ምክሩን፣ ተግሳጹን፣ ቁጣዉን፣ ቅጣቱን፣ ጥበቃውን ከጭቆና ቆጥሮ፣ ፈርጆና ኮንኖ ማስተማር።

ይህ ነው ዛሬ፣ አሁን ባለንበት ጊዜና ዘመን ትውልዳችንን በሥልጣኔ ሰበብ ያጠፋብን እምነት፣ እውነት፣ እሴት ጠልነትን አስይዞ፤ “እኔን” አንጠልጥሎ “እኔን” ብቻ፣ “እኔ የምፈልገው፣ የእኔ እውነት” ለሚል ጥፉነት የዳረገብን፣ እኔነትንም ፖለቲካ ያደረገብን።

ማርክሳዊ አሰላሳዮች አባትነትን እና አባታዊ ሥርዓትን የሚተቹት፣ ሥርዓቱን ከንብረትና ከሥልጣን ክፍፍል ጋር ብቻ አያይዘው ይኹን እንጂ ያንን ንብረትና ሥልጣን የያዘው ግለሰብ አባት ነውና የትችቱ ኢላማ ኾኗል።

የአባት ቅጥ፣ ሕግና ወግ፦ ትውልድ እንዳይወድቅ ሀገር ተረካቢ በማጣት እንዳትደርቅ የሚይዘው ቋሚ ለጓሚ ዋልታና ማገር ነው።

ልጆቹን ለሚወደው፣ ብልጽግና ድኅነታቸውንም ለሚፈልገው አባት ተግሣጽና ቁጣው፦ ፍቅሩን የሚገልጽበት መንገዱ እንጂ ጭቆናው አይደለም።

ልጆች ሁልጊዜ “ተበድለናል፣ ተገፍተናል፣ ተረስተናል” እየተባሉ ካደጉ፣ አእምሯቸው የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ከመወሰን ይልቅ በሌሎች ላይ ጣት መቀሰርን ይለምዳል።

ልጁን “የተበዳይነት መንፈስ” (Victim Mentality) ውስጥ ይከታልና ከእንዲህ ዓይነቱ “ለጽድቅ ከሚጻፍ የብሶት ትርክት” ተለይ።

“አያቶችህ በብዙ ዓይነት ፈተና አልፈው እዚህ እንዳደረሱህ ስታውቅ፤ የድል አድራጊዎች የአሸናፊዎች ልጅ መኾንህን ስትረዳ የብሶት መንፈስ ካንተ ይርቃል።

በብዙ መከራዎች፣ መገፋቶችና መድሎዎችም ውስጥ እያለፍክ እንኳ እነርሱን እያነሳህ የምታዝን፣ የምታላዝን፣ የምትነፋረቅም ሳትኾን ማረፊያህን የምትወስንና ወደርሱም የምትገሰግስ ጀግና ትኾናለህ!

ማርክሳዊ ትረካዎች ባህልንና እምነትን “የጭቆና መሣሪያ” አድርገው ስለሚስሏቸው፣ ትውልዱ ከማንነቱ ጋር እንዲጣላ ያደርጉታል።

አባወራው ግን ከአባቶቹ በተቀበለው እሴት፣ የሰማይ አባቱን ባመነበት እምነት ባህልን ልጁን በእውነት ላይ መስርቶ ሥር ሰዶ ያሳድገዋል!

ታሪክን ሲነግረው “ፍጹም ነው” ብሎ ሳይኾን ስህተት ቢኖር እንኳ፣ ያ ስህተት ለበቀልና ለጥላቻ ሳይኾን ለጥንቃቄና ለዕርቅ፣ ለምክርና ለተግሳጽ መሠረት መኾኑን ያስገነዝባል።

ብሶት ለተጋተው ትውልድ ሀገሩን፣ እምነቱን፣ እሴቱን እንደ “ወኅኒ ቤት” ነው የሚያያቸው። እሴትና እውነትን የተማረ፣ እምነትንም የጨበጠ ትውልድ ግን ሀገሩን እንደ “ርስት”፣ ማንነቱንም እንደ “ውርስ” ያያቸዋል ይጠብቃቸዋልም።

አባወራው ለልጆቹ የጀግኖችን ድል፣ የአርበኞችን ተጋድሎ፣ የሽማግሌዎችን ጥበብ፣ የሊቃውንቱን እውቀት፣ የመሃይምናንን እምነት፣ የገበሬውን ጥረት መተረክ አለበት።

ይህ ትረካ ነው ሀገርን የሚሠራው፤ እንጂ ብሶትን እየፈለጉ፣ እያራገቡ ማቀጣጠል ለጊዜው ጥቅም ቢያመጣም ለኋላው ግን ትውልድን ሳያጠፋ፣ ሀገርንም ሳያቃጥል አይቀርም!


Post a Comment

0 Comments