✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ምን ሊቅና ሊቀሊቃውንት ቢኾኑ ባልሠለጠኑበት ሰውነት ጽድቁን ከመፈጸም በአስመሳይነቱ ካባ ባፍጢም ተደፍተው ባድርባይነት ማደሩ ያይላል።
በየመድረኩ የምናያቸው “ምሁራን” እና “የሃይማኖት መሪዎች” ውድቀታቸው የመነጨው ከእውቀት ማነስ ሳይኾን፣ ከሰውነት ሥልጠና ማጣት ነው።
ልብ በእውነት፣ በእምነትና በእሴት ካልሠለጠነ፤ ጨጓራ እስኪላጥ፣ ኩላሊት እስኪፈርጥ፣ አጥንት እስኪጎብጥ፣ ቢጾሙ፣ አእምሮ እስኪሰነጠቅ ማስትሬትና ዶክትሬት ቢጭኑ ትርፉ “አስመሳይነት” በአስመሳይነቱም በአድርባይነት ማደር ብቻ ነው።
ጽድቅ ማለት ራስን በመርህ ላይ ማሠልጠን ነው። ሥልጠና የሌለው ሰውነት ግን እንደ ገለባ ለነፋስ፣ እንደ መረንም ለባርያ ፈንጋይ የተመቸ ነው።
በምዕራባውያን ዶላርና ትረካ የተነደፉት እነዚያ “ሆዳደር” ምሁራን፣ በየዩኒቨርሲቲውና በየተቋማቱ ተቀምጠው የትውልድ ማምከኛ ፖሊሲዎችን (እንደ SRHR) ሲያስፈጽሙ የምናየው ለዚህ ነው።
ሰውነታቸው በሐቅና በጽናት ስላልሠለጠነ፣ ቤተሰባቸውንና እምነታቸውን፣ እናታቸውንና ሀገራቸውን ለማይረባ ጥቅም ለውጠው አሳልፈውም ይሰጣሉ።
ጽድቁን እንደ ካባ ይደርቡታል እንጂ፣ በውስጣቸው የሚኖረው ግን ከጠላት ጋር ያበሩበት አስመሳይ አድርባይነታቸው ነው።
የአባወራ ቻናልና ገጽ የሚጮኸው ለዚህ ነው። ትውልዱ፣ በተለይም ወንዱ፣ ሊሠራው ካለው “ጽድቅ” በፊት በገዛ ራሱ ላይ እንዲሠለጥን ግድ ይላል።
በፈተና ቀን የሚከዳ፣ በጥቅም ጊዜ የሚሸጥ፣ በምቾትም የሚለውጥ ሕብረት ያልሠለጠነው ለጽድቅ የሚለብሰው የ”አስመሳይ” ካባ ነው።
በገጻችን በልምምዳችን ግድ የምንለው ግን እንደ ድንጋይ የጸና፣ ለሆዱ የማይገዛ፣ ለጠላት ሸፍጥ የማይመች የትውልድ ምሰሶ፣ የሀገር ዋልታና ማገር የሠለጠነው አባወራ ነው።
ስለዚህም ነው ብዙዎች “እስቲ አብረን እንሥራ” ለማለት የሚፈሩት፣ ቃለመጠየቆችን የማይደፍሩት፣ የመጡትም የሚሰጉት አልጫ፣ ቀላጭነታቸውን፣ አስመሳይ ሸቃላነታቸውን የሚገልጥ የሚያጋልጥ እውነት ስለኾነ!
በገዛ ራሱ ላይ ያልሠለጠነ፣ ሆዱንና ስሜቱን ያላሸነፈ ወንድ፤ በውጭው ዓለም ላለው ተኩላ (ለNGOዎቹ ደባ) ሲሳይ መሆኑ አይቀርም።
ራሱ ላይ ያልሠለጠነ አባት ልጆቹ በተኩላውና በሆዳደሩ ለእነርሱ በታሰበ “መብትና ነፃነት” ተቀርጥፈው ሲበሉ በ”ዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት” ስም የተጋተውን ምስኪንነት እያጸደቀ እጂን አጣጥፎ ይቀመጣል።
ራሱ ላይ ያልሠለጠነ፣ ልቦናው በእውነት፣ እምነትና እሴቱ ያልታሸ ወንድ፣ በባዕዳን ትረካ ተሸንፎ አባቱን “ጨቋኝ”፣ እናቱን “ተበዳይ” አድርጎ መሳል፣ ራሱንም መጥላት ይጀምራል።
ለአባወራ ቻናል ተከታዮች ሥልጠና ማለት ጂም ሄዶ ጡንቻ ማሳበጥ ብቻ አይደለም። እውነተኛው ሥልጠና፦
ሥልጠናም ስንል በስሜቶቻችን፣ በብልቶቻችን ላይ እኛ የመጨረሻው፣ ዋነኛውና ብቸኛው የበላይ አዛዥና ናዛዥ መኾን መቻል ማለት ነው።
ሰውነት ስለፈለገ፣ ስጋ ስለጠየቀ፣ ስሜት የልብን በር ስላንኳኳ፣ ፍላጎትም ስለተንጫጫ አይደለም። “ሰጥ በል” ብለን የምናዘው፣ የምናሳርፈውና የምናርፍ በዚያም ወደ ጽድቁ የምናልፍ በሰውነታችን ላይም ብቸኛው ልዕለ ኃያል እኛ መኾናችንን ማስረገጥ ነው!
ባልሠለጠኑበት ሰውነት ምን ቢማሩ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ቢኾኑ በዚያው ባልሠለጠኑበት መውደቁ፣ አልፎ ተርፎም ለጠላት በባንዳነት ማደሩ አይቀርም!
በሰውነት ለመሠልጠን ልብ በእውነት፣ እምነትና እሴቱ መታደስ፣ መታነጽ፣ መወቀርም አለበት። ትልቁ ጦርነት ያለው የራሳችንን ልብ ከጠላትና ሆዳደሮች ጽንሰሃሳብ አርቆና ጠብቆ ማቆየቱ ላይ ነው።
አለበለዚያ ግን የሰበሰቡት ሀብት፣ የደረሱበት የትኛውም እውቀት፣ የወጡበትም የሥልጣን እርከን እንኳን ጽድቅ ሊሠራበት የክፋት መሣሪያ መኾኑ ሳይታወቅ ይኾናል!
ወንድምዓለም! ጀግን!💪
0 Comments