በበጎች የተመራው ያንበሳ መንጋ


  ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

አንበሶች ለዘመናት በኖሩበት፣ በሚታወቁበት፣ በሚከበሩበት፣ በሀገራቸው ሊቃውንት በጎች ታሪካቸውን ለልጆቻቸው አስተምረውላቸዋል፤ ነገር ግን...

ከብዙ ዘመናት በፊት በአንድ ሰፊና ለምለም ሳር ባለበት የአንበሶች ግዛት እንዲህ ኾነ። በዚያ ግርማቸው እጅግ የሚያስፈራ፣ ግሳታቸው ከሩቅ የሚሰማ፣ ዝናቸው በሌሎችም ሳርማ ሜዳዎች ሁሉ የገነነ የአንበሶች መንጋ ነበር።

በአንድ ወቅት ታላላቆቹን አንበሶች የሚያጠቃ ክፉ በሽታ ገብቶ ወንዶቹንም ሴቶቹንም አጠፋቸው። የአንበሶቹም ደቦሎች ወላጅ አልባ ኾነው ተቅበዘበዙ።

በዚያን ጊዜ የጀግኖቹ አንበሶች በበሽታ ማለቅ ሰርግና ምላሽ የኾነላቸው ተኩላዎች የግዛቱን እንሰሶች ይሰበስቡና “ጌቶቻችን አልቀዋል፤ ኾኖም ግን ገና በእንቦቀቅላነት ጥለውብን ለሄዱት በርካታ ደቦሎቻቸውና ከእነርሱም ትንሽ ከፍ ለሚሉትም ታላላቆቻቸው የአያት ቅድምአያቶቻቸውን ታሪክ እየነገረ የሚያስተምር ታማኝ ያስፈልጋቸዋል” አሉ።

እንሰሳቱም በጉዳዩ ተስማምተው የሊቃውንት ጥቆማ ተደረገ። ተኩላዎቹ በግን መረጡ፣ እንሰሳቱም “እውነትም እንደ በግ፣ የዋህ፣ ታማኝ፣ ቅን፣ ትኁት፣ መልካም፣ ጨዋ፣ ደግ..... የት ይገኛል” ሲሉ የተኩላዎችን ምርጫ በጩኸትና በጭብጨባ አጸደቁ።

ትምህርቱም በስፋትና በጥልቀት ለደቦሎቹ በያሉበት ይሰጥ ዘንድ፤ ግዛቱን ሲያስተዳድሩ የነበሩት አንበሶች እንዴት ዓይነት ባሕርይ እንደነበራቸው አበጥረውና አብጠርጥረው የሚያውቁት ሊቃውንት በጎች ታጥቀው ተነሱ።

“ይህንን በማንም ሳይደፈር የኖረን ግዛት እኛ አንበሶች ለሌሎች አሳልፈን መስጠት የለብንምና ልጆቻችንን የጀግንነት ታሪካቸውን እየነገርን ልናሳድጋቸው ይገባል” ብለው አስተማሩ።

(የበጉ “እኛ አንበሶች” እያለ ማስተማሩ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ተሹሞ “እኛ ሴቶች...” በማለት የሚበላበት ሆዱን እንጂ አእምሮውን ተጠቅሞ የማይናገረውን ሹመኛ ወንድ ያስታውሷል)

የኾነው ኾኖ ደቦሎቹ ይህንን ትምህርት ከማሳደጊያቸው(ከKG) ጀምሮ እስከ ትላልቅ ቦታዎች(University) ድረስ ተማሩ። በዚያም በርካታ የአያት ቅድም አያቶቻቸውን ታሪክ የሚያውቁ ደቦሎች በማዕረግ ጭምር ተመረቁ፤

ከፍተኛ ነጥብ ያመጡትም ያንኑ በሊቃውንቱ በጎች የተነገራቸውን የአያት ቅድም አያቶቻቸውን ታሪክ ሊያስተምሩ እዛው እንዲቀሩ ተደረጉ።

ይኹን እንጂ ደቦሎቹ በዚህ ሁሉ የማዕረግ ትምህርት በአካላቸው ከደቦልነት ወደ ሙሉ አንበሳነት እያደጉ ቢመጡም፤ ነገር ግን የሚያስፈራው ግርማ አልነበራቸውም፤ ከዚያ በተጨማሪም ከአያት ቅድም አያቶቻቸው ጊዜ ይልቅ በግዛቱ ኢፍትሐዊነት የሚነግሥ ኾነ።

ጅቦች በርካታውን የግዛቱን ነዋሪ እንሰሳት “ለምን ዓየኸኝ/ዓየሽኝ” እያሉ አላፊ አግዳሚውን ሁሉ የሚተናኮሉ፣ የሚዘነጥሉ ኾነ፤ ከመሸም ለመንቀሳቀስ አስቸገረ፤

እሜት ቀበሮም የበጎችን የዋህነት ተጠቅማ ከተኩላዎች መዳፍ አታላ የምትከታቸው፣ እርሷም ከተኩላው ጋር የምታወራርዳቸው ኾነች።

ሊቃውንቱ በጎች የተፈሪዎቹን፣ የጀግኖቹን፣ የጀብደኞቹን የግዛቱን ነገሥታት አንበሶች ታሪክ ላንቃቸው እስኪሰነጠቅ ጮኸው አስተማሩ፤

ነገር ግን ያለ ወላጅ ከቀሩት ደቦሎች መካከል አንድም ለጽድቅ፣ ለፍትሕ የጨከነ፤ ጨክኖም ተፈጥሮአዊ ጸጋውን ተጠቅሞ የሚፈጽምበትን፣ ፍትሕ የሚያሰፍንበትን ጀግና አንበሳ ሊያወጣ አለመቻሉ ጥያቄ ኾነባቸው።

ደቦሎቹ “አያውቁም” እንዳይባል ሊቃውንቱ የታሪክ አዋቂ በጎች ያስተማሯቸውን የአያት ቅድም አያቶቻቸውን ታሪክ በማዕረግ ተመርቀውበታል፤

“እና ምን ጎደለ፣ ምን አጎደልንባቸው?” የምሁራኑ በጎች በምሁር ጭንቅላታቸው ሊመልሱት፣ ከአእምሯቸው በላይ የኾነና፣ መልሱንም እስካሁን ያልደረሱበት ጥያቄያቸው ነው!

በዚያ መንደር ከነበረኝ ጥቂት የምናብ ቆይታ በኋላ ወደ እናንተ እንደምመለስ ያወቁት፣ የተጨነቁት ሊቃውንት በጎች ከሌሎቹ እንሰሳት ተደብቀው ለእነዚህ ሦስቱ ጥያቄዎቻቸው መልስ እንድትሰጧቸው ልከውኛል።

ልትረዷቸው ትችላላችሁ?

1 የእኛ የሊቃውንቱ በጎች ድክመት(ስሕተት) ምንድን ነው?

2 እኛን በጎችን ለመምህርነት ጠቁሞ መምረጥ ማስመረጥ፣ ተሰሚነት እንድናገኝ መድረክ የማመቻቸት የተኩላዎቹስ ዓላማው ምን ነበር? ሸፍጥ ሊኾን ይችላልን?

3 ግዛቱ ወደ ነበረበት ባለግርማ የአንበሶች መንደር እንዲመለስስ ምን መደረግ አለበት ትላላችሁ?

መልሱን እየጠበቁ ነው፤ ቶሎ በሉ!

(ይህ በተረት መልክ የቀረበላችሁ፤ ትናንት ከአባወራው ልሂቃን ጋር የተወያየንበት ጭብጥ ነው)

Post a Comment

0 Comments