አዋቂነት የማይታደገው ልባልባነት


✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ልብ ሰውነትን ይበይን ዘንድ በእውነት፣ እምነትና እሴት ሳይታነጽ ቀርቶ ልባልባ ከኾነ፤ ተምረው የሚደርሱበት ሊቅነት ሰውን ከልማቱ ይልቅ ለጥፋቱ አሳልፎ ይሰጠዋል!

ሰው ከመላእክትና ከእንሰሳት ተለይቶ “ሰው” የተባለው በአእምሮው ስፋት ብቻ ሳይኾን በልቡ ጥልቀትና በነፃ ፈቃዱ ነው። መላእክት በባሕርያቸው ለበጎ የተፈጠሩ፣ ክፋትን የማያውቁ ቅዱሳን(ቅዱሳኑ) ናቸው።

እንሰሳት ደግሞ በደመ-ነፍስ የሚመሩ፣ ከባሕርይ ሕጋቸው ዝንፍ የማይሉ ፍጥረታት ናቸው። ሰው ግን በሁለቱ መካከል ቆሞ፣ በተሰጠው “ልብ” አማካኝነት ነፃ ፈቃዱን ተጠቅሞ ሰውነቱን ይበይናል።

ልብ የሰውነት ማዕከል፦ የእውነት ማረፊያ፣ የእምነት ማደሪያና የእሴቶች መቀመጪያ ነው። ልብ በእነርሱ ካልታነጸ አእምሮን ማጥራት ስሜት ፍላጎትን መግራት አይችልም።

አእምሮም ምንም ያህል ቢሰላና ቢራቀቅ፣ ውጤቱ ማኅበረሰባዊ ውድመትና የዘር መጥፋት ብቻ ነው፤ እጅግም ስለት ይቀዳል አፎት እንዲሉ!

ዛሬ በየዩኒቨርሲቲውና በየተቋሙ የምናየው “አዋቂነት” ትውልዱን ከጥፋት ሊታደገው አልቻለም። ለምን? ምክንያቱም አእምሮው በትምህርት ተስሎ “ሊቅ” ቢባልም፣ ልቡ ግን በማርክሳዊና በቁሳዊ ፍልስፍናዎች፣ በጨቋኝና ተጠቋኝ ትርክቶች ስለመከነ ነው።

ልብ-አልባ ሊቅነት ሰውን ለክፋት የተሳለ መሣሪያ ያደርገዋል። አእምሮው በቴክኖሎጂና በሳይንስ፣ በሀብትና በቁስ ይራቀቃል፤ ልቡ ግን እውነት-አልባ፣ እምነት-አልባ፣ እሴት-አልባ ስለኾነ ያንኑ ዕውቀት የሠራ አካላቱን፣ የገዛ ወገኑን ለማምከን፣ ቤተሰቡን ለማፍረስና ተፈጥሮውን ለመካድ ይጠቀምበታል። ይህ “የተማረ ባርያ” እንጂ ነፃ ፈቃድ ኖሮት የተፈጠረ፣ እውቀቱንም ያንኑ ነጻነት ተጠቅሞ ጽድቅ የመረጠበት አይደለም።

የተሳለ አእምሮ ለጽድቅ እንዲያስብ፣ በእውነት፣ እምነትና እሴቱ በታነጸ ልብ መገራት አለበት። ልብ የሞራል ልጓም ነው፤ ልብ የሌለው አእምሮ ግን እንደ መሪ፣ ቃኚ አልባ መርከብ በማዕበል እየተነዳ ለማንኛውም የጥፋት አጀንዳ (propaganda) ይገዛል።

ማርክሳውያን ትውልዱን በመብትና ነፃነት ሰበብ ለማጥፋት የሚጠቀሙት እንደዚህ ያሉ “የተማሩ” ነገር ግን አያት ቅድማያቶቻቸው ከመጡበት እሴት የተለዩ ለጽድቅ መጨከን የማይችሉ ሆዳደሮችን ነው።

(የእኛን ሀገራቱን ሄደው እውቀት ቀስመው እንዲመጡ የተላኩቱን፣ ነገር ግን በመርዝ የተለወሰ እውቀት፣ በጥላቻ የተበረዘ ጥበብ ይዘው መጥተው የጥላቻ ነቀርሳን የተከሉብንን አስታውስ)

አእምሮአቸው የተሳለ፣ ማዕረጋቸው የረዘመ፣ ነገር ግን ልባልባ ኾኖ በጠፋበት የገዛ ራሳቸውንና የእነርሱ የኾነውን ሁሉ ጠልተውና ተጠይፈው እናታቸውንና ሀገራቸውን ለባዕድ ጠላት አሳልፈው የሚሰጡ ባንዳዎች እንዲኾኑ ያደርጓቸዋል። አእምሮው ያወቀ መስሎት ልቡ ሲመክን፣ ሰውነቱ “ሰው የመኾኑ ነገር” ይሞታል፣ ይጠፋል፤ የቀረውም ሥጋዊ ሲኾን አኗኗሩም ከእንሰሳት በታች ጭምር ይኾናል።

ወንድማምዓለም! ልጆችህን በዕውቀት ብቻ አታሳድጋቸው፤ ዕውቀት ያለ ልብ “አዋቂ ሰይጣን” ያደርጋቸዋል። ዛሬ ሀገሬን የራባትና የጠማት የናፈቃትም የተማረ ሰው ሳይኾን “ሰው” የኾነ ሰው ነው!

ልባቸውን በእምነትና በትውፊት እሴቶች ካላነጽከው፣ ነገ የደረሱበት ሊቅነት ወላጆቻቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ማንነታቸውን፣ ተፈጥሮአቸውን፣ ራሳቸውን የሚንቁበት፣ ቤተሰባቸውን የሚንዱበትና ማንነታቸውን የሚያጠፉበት መሣሪያ ይኾንባቸዋል።

አትርሱ አስታውሱ!

ሰውነት የሚበየነው በእውነት፣ እምነትና እሴት በታነጸ ልብ ውስጥ እንጂ በተጫነ ዕውቀት አይደለም! እምነትና እሴት ደግሞ በራስጠልነት በተመረዙት፣ ነቀርሳ በኾነብን በማንነት ፖለቲካ በተለከፉት እንደሚነገረው፤ ፍሬ አልባ አፈታሪክ፣ ገለባ የቃላት እጭቅ አይደሉም።

እነርሱ በተሻሩበት ልብ ይጠፋል፤ ልብ ሲጠፋ አእምሮ የቅብዘበዛል፤ በተቅበዘበዘው ነገር ግን በተሳለው አእምሮ ደግሞ መጀመሪያ ባልጫነት በወደቀው ሰውነት ማደሪያው ራሱን ትውልድንም ያጠፋል፤ ሰውነት ሲጠፋ ደግሞ ሀገርና ትውልድ አብሮ ይቀበራል!

ስለዚህ ታናሼ! ልብ-አልባ ሊቅነትን አትመኝ፤ (ሀገርን እያጠፉ ያሉትን ማስትሬትና ዶክትሬት የጫኑትን፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ተብለው ትውልድን ከመጣበት እሴቱ ነጥለውና ለይተው ለጠላት የሚሸጡትን አስተውል!)

ስለኾነምም አእምሮው ለጽድቅ በሠለጠነ ልቡ የሚገራ፣ ለጽድቅ የሚቆም፣ ለእውነት የሚጨክን፣ በዚያም መከራውን ለመጨለጥ የቆረጠ ሰውነት-ትውልድ ለማፍራት ትጋ እንጂ።

አዋቂነት ካልታደገው፣ ከማይታደገው፣ ሊታደገውም ከማይችለው ልብ-አልባነት ትውልዱን መጠበቅ ደግሞ የእኛ የአባወራዎቹ ድርሻ፣ ሚና፣ ግዴታ እና ኃላፊነትም ጭምር ነው።

Post a Comment

0 Comments