✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
አንድ ታሪክ ሲጻፍ ለትውልዱ እንዲተላለፍ ወደተፈለገው ጭብጥ አድልቶ ይጻፋል። ትውልድን በማነጽ ሀገርን ለመገንባት የሚያስቡት ልባሞች የጀግንነቱን፣ ትውልዱን ሰልበው ለባርነት የሚያግዙት አድርባዮች ስሐተቱን ያደምቁታል!
ታሪክ መረጃ ብቻ ሳይኾን መቅረጫ እሴትም ነው። ይኹን እንጂ ይህንን ታሪክ የትውልዱ ልብ የሚታነጽበት እሴት የሚያደርጉት ታሪካዊ ክስተቱን (ሐቁን) ከትርጉሙ፣ ትርጉሙን ከዘመኑ ዐውድ ጋር አስማምተው እሴት የሚያወጡለት ሊቃውንት፣ ሽማግሌዎች፣ አርበኛ አባወራዎች ናቸው።
የትውልድን ልብ በጠንካራ ስብዕና በማነጽ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የሚያልሙ ልባሞች የጀግንነቱን፣ የመስዋዕትነቱንና የሉዓላዊነቱን መንፈስ ያደምቁታል።
በአንጻሩ ደግሞ ትውልዱን ሰልበው ለባርነትና ለከንቱነት የሚያመቻቹ የጠላት ተቀጣሪዎች፣ አድርባዮች፣ ምንደኞች የጀግኖቹን ድካምና ውድቀት ፈልገው በማጉላት፣ አጉልተው በማስኮነን የውርደት ትርክትን ይግቱታል።
ይህንን ስልታዊ የታሪክ ጥቃት ትውልዱን በተለይም ወንዱን ከተፈጥሮአዊው ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ ከተሰጠው መክሊቱ፦ ወኔው፣ ጀግንነቱ፣ ድፍረቱ ጥንካሬው፤ መስለብ እንለዋለን።
ኾኖም ግን ይህንን የሚያደርጉት ያልተማሩ መሃይም አይደሉም፣ ጠላትም የቀጠራቸው ታሪኩን አበጥረው፣ ሲያውቁ “በዘመናችን የሞራል መነጽር ለምን ልክ አልኾነም” የሚል ግብዝነትን አንባቢው ውስጥ አስርገው፣ ጀግኖቹን አስኮንነው የትውልዱን ወኔ-ልቡን እንዲሰልቡለት ነው።
ባለታሪኩ የሀገር የጦር መሪ ይኾናልና፤ ከስሕተቱ መርጠው “በመንፈሳዊ መነጥር” ዐይተው፣ የሠራውን “ስሕተት” የሚኮንን ጻድቅ ፈልገው፣ ሁለቱን በማገናኘት ጀግናው ለሀገሩ ከከፈለው መስዋዕትነት ይልቅ “ኩነኔውን” አግዝፈው ለትውልዱ ይጽፉለታል።
አንድን ኃያል መሪ በግል ድክመቱና በሥነ-ምግባር ጉድለቱ ብቻ አጥብቦ በመተርጎም፣ ለሀገሩና ለህልውናው የከፈለውን ታላቅ ዋጋ ማኮሰስ ትውልዱ ከእርሱ ሊማር የሚገባውን የክብር፣ የልዕልና፣ የመስዋዕትነት፣ የጀግንነት ትምህርት ንቆ፣ ጠልቶ፣ ተጠይፎ እንዲቀር፤ “ልባልባ” የማድረግ ሂደት ነው።
በዚህ ላይ ደግሞ እንዲህ ያሉት ጸሐፊያንም ኾኑ እነሱን የሚያበረታቱ ተቋማት “መንፈሳዊ ነን” ብለው በእውቀታቸው የሚመጻደቁ ከኾነ፤ እነርሱን ተከትሎ ጽሑፍ ትርክታቸውን፣ የቃል ስብከታቸውን ይዞ በአጉል መንፈሳዊነት ታጅሮ፦ ጀግንነትን፣ ተዋጊነትን፣ ኃይለኝነትን፣ ጀብደኝነትን፣ መስዋዕትነትን፤ በጽድቅ ስም የሚጠየፍ ለባርነት የተመቸ፣ ስልብ ጃንደርባ ይኾናል።
ስልብነቱ ሥነ-ልቦናዊ ቢኾንሜ በዚያው ተወስኖ አይቀርም። ለመኖር ባልጓጓበት፣ ለሕይወት ባልሮጠበት፣ ልጆችን ወልዶ ተስፋ ባላደረገበት፦ ምክንያቱም ለዚያ ኑሮ የሚከፈለውን ውድ ዋጋ በናቀበት ሃሳቡ፤ ቢያገባም ለማስረገዝ ለማያስችለው መካንነት አእምሮው አሳልፎ ይሰጠዋል።
ወንድሞቼ! በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ፍጹም የኾነ ጀግና የለም። ከብሉይ ኪዳን አባቶች ከአብርሃምና ከዳዊት ጀምሮ እስከ ጥንታዊያኑ ነገሥታቶቻችን ድረስ፣ ሁሉም የሰው ልጅ ድካም ነበረባቸው።
ነገር ግን ታሪክና እምነት ቅዱሳንና ጀግኖች ብሎ የሚዘክራቸው በድካማቸው ሳይኾን፣ በንስሐቸውና ለወገናቸው ተዋግተው ባሳዩት የጀግንነት ጀብድ ነው።
ቤተክርስቲያን አብርሃምንና ዳዊትን በስማቸው ታቦት ቀርጻ የምታከብረው ድካማቸውን ቆጥራ ሳይኾን በእምነታቸውና በጀግንነታቸው ነው።
ከታሪክ ድርሳናት ውስጥ የሀገር፣ የጦር መሪዎች ከሠሩት የሕይወት ዋጋ ከከፈሉለት፣ በዓለም መድረክም ከታወቁበት ጀግንነታቸው እየነጠሉ፤ ድካማቸውን ብቻ እየመረጡ ማሳየት ግን ትውልዱ “ጀግንነት የሚባል ነገር የለም” ብሎ ተስፋ እንዲቆርጥ በዚያም ራሱን፣ ቤተሰቡን፣ ማኅበረሰቡን፣ ቤተክርስትያኑንና ሀገሩን የሚከላከልበት ወኔ አጥቶ “ስልብ፣ ቅልብ፣ ሙክት፣” አገልጋይ፣ ጃንደርባ ብቻ እንዲኾን ያደርገዋል።
ይህ ትርክት ደግሞ “መንፈሳዊ ነን” ከሚሉ ተቋማትና ግለሰቦች ሲመጣ የሚገኘው ፍሬ አልጫ፣ ልባልባ፣ እንከፍ ምስኪን የኾነ ለባርነት የተመቸ፣ በመስዋዕትነት የቀበለውን ሀገር “ያለምንም ደም መፍሰስ” አሳልፎ የሚሰጥ አድርባይ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳ ሲኾን፤ “በመንፈሳዊነቱም” አስመሳይ የኾነ፣ ሃይማኖተኛነቱ ታውቆለት በእብሪት የቀበጠ ቀላጭ ትውልድ ብቻ ነው።
አሁን የተጋረጠብን የትውልድ አደጋ ይህን የመሰለው ነው። ይህም ትውልድን የመስለብ ሸፍጥ ደግሞ ኾን ተብሎ ባፍጢም በተደፉቱ የቤተክርስትያኗ የዘመናችን የታሪክ ጸሐፊዎች ተፈጽሟል።
ለገዳማውያን የሚጻፍ ድርሳንና ለሕዝብ የሚጻፍ የታሪክ መጽሐፍ ለየቅል ናቸው። ገዳማዊው መካሪና ገሳጭ ነውና ያየውን ስሕተት ነቅሶ፣ ሳይፈራ ጠቅሶ፣ ወቅሶና ገስጾም ይናገራል፤
የሀገር መሪው፣ ጦረኛ ተዋጊው ደግሞ የሀገር ጠባቂ፣ መከታ፣ ጋሻ ነው፤ የእኔ የሚለውን ሕዝብ፣ ሀገር፣ እምነት የሚያጠፋ ጠላት ሲመጣ ክብሩን ላለማስደፈር፣ ሕዝቡን ላለማስበርበር፣ ንብረቱን ላለማዘረፍ ሲል ሕይወቱን አሳላፎ እስኪሰጥ ድረስ መስዋዕት ይኾናል።
የቤተመንግሥቱን ጀግንነት አሳንሶ የቤተ-መቅደሱን ብቻ “የኃያላን” አድርጎ ማቅረብ፣ ሕዝቡን ሊያጠፋው በጨከነበት፣ ጦር ሰብቆ በቀረበው ጠላቱ ላይ ከመዝመት ይልቅ ወደ ጸሎትና ለቅሶ ብቻ እንዲያደላ ያደርገዋል።
ይህም ትርክት ተቀባይንት አግኝቶ በትውልዱ ልብ ሲዘቅት፦ በስጋውም በመንፈሱም ጠላትን የሚረታበት ትጥቁን፣ አምላኩ የሰጠውን ስንቁን ሠልጥኖበት አይሎ ከመገኘት ይልቅ፤ ዘወትር ጠዋትና ማታ “በመንፈሳዊ ነኝ” ብሂል የሚያዝን፣ የሚያላዝን የሚነፋረቅም አባቶቹን የማይመስል አልጫን ያፈራል።
ይህም ኩነቱ ለጠላትና የወጥመዱን መረብ በመንፈሳዊነት ሰበብ ለዘረጉት ሰርግና ምላሽ ነው። ትውልዱ የተሰጠው “ጣፋጭ መርዝ” በመንፈሳዊነት ጨልጦ ከተጠናወተው ስካር የተነሳ ምን ቢማር ማስትሬትና ዶክትሬትም ቢሠራ ለባርነት በወዶ ፈቃደኝነት እጁን የሰጠ አድርጎታል።
ጠላት ሲመጣ የሚመከተው በሰይፍና በጦር ስልት እንጂ በጸሎት ብቻ አይደለም። ይህም ራሱ እውነትን ለሚመረምራት፣ እውነትን ለሚሻት ከእነዚያው ግሥናን ከቅስና አልፎ ተርፍም ከቅድስና አስተባብረው ከያዙት መሪዎች ታሪክ ውስጥ የጦር ልምምዳቸውና ዘመቻቸው ምን እንደሚመስል በማጥናት ይገኛል።
ወንድሞቼ ስሙኝማ ልንገራችሁ! ለልጆቻችሁ ታሪክን ስታስተምሩ ትውልዱን እንደ አንበሳ ደቦል የሚያሳድግ፣ ግርማ ሞገሱን የሚዘክር፣ ይህንንም የሚሄድበትን ፈለግ በሚስል ልባምነት ይኹን።
ለሀገሩ ኩራትና ክብር፣ ወደ ሙሉ ሰውነት የሚያወጣውን ጠንካራ ስብዕናም የሚሰጠውን የጀግንነት ትርክት እየነገራችሁ በተለይ በይበልጥም እየኖራችሁ ቅረጿቸው።
ድካምን ብቻ የሚቆጥር፣ በአጉል መንፈሳዊነት ተመጻድቆ፣ የአባቶቹን ገድል የሚኮንን የሆዳደር አንደበት ትውልዳችሁን አስመሳይ አድርባይ አድርጎ እንዳይሰልበው ተጠንቀቁ!
እውነተኛ የታሪክ ፋይዳ የሚገኘው ትውልዱ ከቀደምት ጀግኖቹ ጋር በመንፈስ ተስማምቶ ለሀገሩ ሉዓላዊነት እንዲቆም ሲያደርገው ብቻ ነው።
አንተ አንበሳው! ደቦል-ልጆችህን ለማሳደግ የአንበሳን ታሪክ ባንተ በአንበሳው ድምፅ መተረክ፣ በእግርህም እየሄድክ ፈለግህን መተው የግድ ነው!
የታሪክ ጸሐፊ ያውም የባዕዳኑ ያልኾነ ያንተው ወገን የሀገር፣ የድንበር፣ የእምነት ጠባቂ የኾኑትን፤ በዚህም የታወቁትን፣ የገነኑትን ጥቃቅን ስሕተታቸውን እየፈለገ፣ ገድላቸውን እያኮሰሰና አልፎ ተርፎም “በሃይማኖት አባቶች” እያስኮነነ ሲጽፍ ለምን ብለህ ጠይቅ?
አልጨረስኩም!
እውነተኛ የታሪክ ድርሳን ቀዳሚ ዓላማው ማንነትን መገንባትና የሀገርን የጀግንነት አውታር ለትውልድ ማስተላለፍ ነው።
እንዲህ ዓይነቱ አጻጻፍ የነገሥታቱንና የጀግኖቹን ተግባር የሚመዝነው ለሀገር ህልውናና ለሕዝብ አንድነት በፈጸሙት ታላቅ ገድል ላይ በመመሥረት ሲኾን፣ መሪዎች ሰው በመሆናቸው ሊፈጽሟቸው የሚችሏቸውን ሰብአዊ ድካሞች ከታላቁ የጀግንነት ሥራቸው በላይ አጉልቶ በማውጣት የታሪኩን ፋይዳ አያደበዝዙም።
አንባቢው እንዲህ ያለውን የታሪክ ድርሳን ሲያነብ “የጀግኖች ዘር ነኝ” የሚል ኩራትና ለሀገሩ የመቆም ወኔ እንዲሰማው በማድረግ ትውልዱን እንደ አንበሳ ደቦል በጽኑ መሠረት ላይ እያነጸ ያሳድገዋል።
በአንጻሩ የሞራል ክሰሳ አጉል መንፈሳዊነትኔ እንደ ፍርድ ቤት በመጠቀም የጀግናውን ግርማ የሚቀንጥስና ትውልዱን የሚሰልብ አደገኛ አካሄድ ነው።
የዚህ ዓይነቱ አጻጻፍ ትኩረት የመሪው የጦር ሜዳ ጀግንነት ወይም ዲፕሎማሲያዊ ጥበብ ሳይኾን፣ በግል ሕይወቱ ውስጥ የሚታዩ ጥቃቅን ስህተቶችን መለቃቀም ላይ ያተኩራል።
ጀግናውን እንደ ተራ ኃጢአተኛ ብቻ እንዲታይ ማድረጉ፣ ትውልዱ ስለ አባቶቹ የሚሰማው ክስና ውርደት ብቻ እንዲኾን በማድረግ ለሀገር ፍቅርና ለክብር ግድ የሌለው ተጠራጣሪና ልባልባ በማድረግ፣ አስመሳይና አድርባይ ትውልድ ይፈጥራል።
0 Comments