✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
“በመብትና ነፃነት” ሰበብ ያልተወለዱትን የልጆቻችን ለቅሶ፣ የንጹሐኑንስ እንባ ማን ያብሳል!
በዐለማችን ላይ ዛሬ ከሚሰሙት ድምፆች ሁሉ እጅግ መሪርና ልብ ሰባሪው ድምፅ፣ ገና ዓለምን ባላዩ፣ ብርሃን ባልቀመሱ ነገር ግን በሞት ጥላ ስር ባሉ ንጹሐን ፅንሶች የሚሰማ የዝምታ ጩኸት ነው።
ይህ ጩኸት በቤተ-መቅደሱ የሰው ልጅ ያውም የእናት ማኅጸን ውስጥ ኾኖ፣ ወደ እናቱ ልብ የሚላክ የመጨረሻው የልመና መልእክት ነው፦ “እናቴ ሆይ! እወድሻለሁ፤ ነገ ለሀገር ለምድር የሚተርፍ ጥሩ ልጅ እኾንልሻለሁ፤ እባክሽን አትጣይኝ! ለእነዚያ በመርዝና በመቀስ በጣጥሰው ለሚያስወርዱኝም አሳልፈሽ አትስጪኝ!”
ዛሬ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፣ “የሥነ-ተዋልዶ ጤና”፣ “የሴቶች መብት” እና “የሰውነት ነፃነት” በሚሉ አንጸባራቂ ቃላት ተሸፍኖ ትውልድን የሚያመክን መርዛማ አስተሳሰብ በምድራችን ላይ እየተረጨ ይገኛል።
ይህ መርዝ ዘርን የሚተካውን፣ ተስፋን የሚቀጥለውንና የፈጣሪ በረከት የኾነውን የሰው ልጅ ፅንስ እንደ “አላስፈላጊ ክስተት” ወይም እንደ “ጤና ጠንቅ” አድርጎ እንዲታይ አድርጎታል።
ዘመናዊው ዓለም የሰው ልጅን ሕሊና ለማደንዘዝ፣ በተለይም ማርክሳውያን ነባሩን እሴት ለመናድ የተጠቀሙበት ትልቁ መሣሪያ የቃላት ማጭበርበር ነው።
“መብት” የሚለው መልካም ቃል ተጠቅመው አንዲት እናት የገዛ ልጇን ሕይወት እንድትቀጥፍ ፈቃድ የሚሰጥ የሞት ደብዳቤ እንዲኾን ተደርጓል።
“ነፃነቱም” ከፈጣሪና ከተፈጥሮ ሕግ ወጥቶ የራስን ዘር እስከ ማጥፋት፣ ማኅበረሰብንም እስከማምከን የሚያደርስ እብደት ኾኗል።
እነዚህ መርዛማ ፍሬዎች፦
🚨 ሕይወት የሰጪው የፈጣሪ እንጂ የሰው ልጅ የግል ንብረት አይደለችም። ይህንን አደራ መበላት ከበረከት ምንጭ መለየትና የፈጣሪን ሉዓላዊነት መዳፈር ነው።
🚨 ተፈጥሮ በእናትና በልጅ መካከል ያስቀመጠችውን የማይበጠስ የፍቅርና የጥበቃ የእንክብካቤም ገመድ በመበጠስ፣ እናት ለልጇ መጠጊያ መኾኗ ቀርቶ ሥጋት የምትኾንበትን የተገለበጠ ዓለም ይፈጥራል።
🚨 ይህ አስተሳሰብ አካላዊ ምክነት ብቻ ሳይኾን፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ምክነትንም ያስከትላል። ሕይወትን የማይቀበል፣ ለተቀሰውና ክቡር ለኾነው የሰው ነፍስ ክብር የሌለው ትውልድ ለሀገር፣ ለታሪክና ለወደፊት ተስፋ የሚቆምበት መነሻ ምክንያትም አይኖረውም።
ዛሬ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በዘመናዊው የሕክምና መሣሪያዎች፣ በሴቶች “መብትና ነፃነት” ሽፋን በሚካሄዱ ሕጋዊ ግድያዎች(ውርጃዎች) ሕይወታቸውን ያጣሉ። እነዚህ ገና ያልተወለዱ የነገው የሀገር መሪዎች፣ የቤተሰብ ኃላፊዎችና የዓለም ጨው ብርሃንም የሚኾነ ነፍሳት ደማቸውና እንባቸው ወደ ሰማይ ይጮኻል።
🚨 ይህንን እንባ ማን ያብሳል?
👉 የቤተሰቡ መሪ፣ የትውልዱ ጠባቂ፣ የኾነው አባወራ ለሕይወት ዘብ ካልቆመ?
👉 ማኅበረሰቡ ይህንን “የሥነ-ተዋልዶ ጤናና መብት” የሚባል ጭንብል የለበሰ መርዝ ካላጋለጠ?
👉 እናትነት ለሰው ልጅ የተሰጠ ታላቅ ክብርና የሕይወት ምንጭ መኾኑን ዳግም ካላስተማርን?
ይህ የማምከን ሴራ በትውልዳችን ላይ የሚያስከትለው ጥፋት ከጦርነትና ከቸነፈር፣ ከበሽታና ከተፈጥሮም አደጋ የከፋ ነው።
ምክንያቱም የኋለኞቹ በሌላ ወገን የሚፈጸሙ ጥፋቶች ሲኾኑ፣ ይህ ግን በገዛ እጃችን፣ የገዛ ተስፋችንን፣ ልጆቻችንን፣ ትውልዳችንን እንድንቀብር ያደርገናልና።
ስለዚህ፣ የእነዚህን ንጹሐን ልጆች የዝምታ ጩኸት እንስማ። ዛሬ ማስትሬትና ዶክትሬት ይዘው፣ ከምዕራባውያን ጋር ግብር ተሻርከው፣ ግብር በማይከፍሉ “የግብረሰናይ ሱቆቻቸው” በከፈቷቸው የሕጻናት “ቄራዎች” የሚፈጸመውን ሴቶቻችን የሚለማመዱትን ውርጃ ማስቆም ይገባናል።
እናትነት የሕይወት አፀድ፣ ማኅጸኗም የትውልድ ምንጭ እንዲኾን እንጂ የሞት ሜዳ፣ የሕጻናት መቃብር እንዳይኾን፣ መብትና ነፃነትም ለሕይወት እንጂ ለጥፋት እንዳይውል በጋራ ልንቆም ይገባል።
0 Comments