✍ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር
ያ የጣልኩት አሮጌ ልብስ በመንገድ ዳር እንደ ባዶ ቅርፊት ተኝቷል። ለተመልካቾቹ ያ ጨርቅ ተራ አቧራ የጠገበ ቁራጭ ሊመስላቸው ይችላል፤ ለእኔ ግን ያ የቆየው ማንነቴ ሬሳ ነበር። በመንገድ ዳር የቀሩት ሰዎች ያንን ልብስ ሲመለከቱ በውስጣቸው የሚቀሰቀሰው የነፍስ ጥያቄ ጥልቅ ነው፦ "አንድ ሰው ለዓመታት የተላመደውንና መኖሪያው የሆነውን ጥላ እንዴት በአንድ ቅጽበት ጥሎ ሊሄድ ይችላል?" የሚል።
ያ ልብስ ለእኔ መከታዬ ነበር። ብርድ ሲመጣ የምጠለልበት፣ ሰዎች ሳንቲም እንዲጥሉልኝ የምዘረጋው፣ የማንነቴ መገለጫ የሆነ የጭንቀት ካባ ነበር። በመንገድ ዳር የቀሩት ሰዎች ያንን ልብስ ሲያዩ፣ የራሳቸውን "አሮጌ ልብስ" ማሰብ ይጀምራሉ። እያንዳንዱ ሰው በልምድ፣ በሥልጣን፣ በሀብት ወይም በሐሰተኛ ዝና የተሸመነ አሮጌ ልብስ አለው። ያንን ልብስ ጥሎ ወደማይታወቅ ብርሃን መሄድ ደግሞ ትልቅ ድፍረትን ይጠይቃል።
ጥያቄው "ይሄ ረው! እንዴት አየ?" የሚለው ብቻ አይደለም፤ "ይሄ ሰው! እንዴት ሊጥል ቻለ?" የሚለውም ጭምር ነው። ብዙዎች ብርሃኑን ይናፍቃሉ፣ ነገር ግን ጨለማውን ለምደውታል። በመንገድ ዳር የቀሩት ሰዎች በአሮጌው ልብሳቸው ሙቀትና ምቾት ተታለዋል። መራቆትን ይፈራሉ። እኔ ግን እርቃኔን መቆሜን አላፈርኩም፤ ምክንያቱም ከብርሃኑ ጋር ስገናኝ የሚለብሰኝ አዲስ ማንነት እንዳለ በነፍሴ አውቄ ነበር።
ያ ልብስ በመንገድ ዳር መቅረቱ ለዓለም የሚናገረው አንድ እውነት አለ፦ "ከእውነት ጋር ለመገናኝት ካለፈው ታሪክህ ጋር መፋታት አለብህ።" ካለፈው ጋር እየኖርክ የወደፊቱን ማቀፍ አይቻልም። በመንገድ ዳር የቀሩት ሰዎች ያንን ባዶ ልብስ እያዩ "እኛስ የምንጥለው መቼ ይሆን?" ብለው ይጠይቃሉ። ነገር ግን ለመጣል መጀመሪያ ጩኸቱን ማወቅ ያስፈልጋል።
እኔ ያንን አሮጌ ካባ ጥዬ፣ በአዲሱ የብርሃን መጎናጸፊያ ተጠቅልዬ ወደ ፊት ገሰገስኩ።
እኔ ማለት ከራሱ አሮጌ ማንነት ተላቆ በአዲስ ተስፋ የተወለደው ነኝ።
0 Comments