✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ትውልድ ድኅነት መድኃኒቱን በሚሰማባት።፣ በሚያጋኝበት ቤተክርስትያን የምዕራባውያን ጥፋት ዓይቶ ከስሕተታቸው አለመማር፣ ይባስ ብሎም ጥፋትና ሞቱን መድገም አደራን መብላት ነው!
“ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል፤ እናንተ ግን የወንበዴዎች ዋሻ አደረጋችሁት!” (ማቴ. 21፡13) የሚለው መለኮታዊ ግሥጼ ዛሬም በቤተ መቅደሱ ቅጥር ውስጥ በኃይል ያስተጋባል።
ይህ ቃል ትናንት በመቅደሱ ርግብ የሚሸጡትንና መክሊት የሚለውጡትን ብቻ ሳይኾን፣ ዛሬ በሃይማኖት ካባ ተሸፍነው ትውልዱን ለባዕድ ርዕዮተ-ዓለም አሳልፈው የሚሰጡትን “ዘመናዊ መንፈሳዊ ነጋዴዎች” የሚገርፍ እሳታዊ ጅራፍ ነው።
መቅደሱ የእውነት፣ የእምነትና የእሴት ቦታ መኾኑ ቀርቶ፣ በምዕራባውያን የገንዘብ ድጋፍና በዓለም አቀፍ ድርጅቶች አጀንዳ የሚመራ የርዕዮተ-ዓለም ገበያ እንዲኾን የፈቀዱ “ሆዳደር” ሊቃውንት በእውነት ፊት የሚቆሙበትና ውርደታቸው የሚገለጥበት ሰዓት ደርሷል።
እነዚህ አካላት የቤተክርስቲያንን አጥር በማፍረስና የቅዱሳን አባቶቻችንን አስተምህሮ በመበረዝ፣ መቅደሱን ለፖለቲካዊና ማኅበራዊ ሙከራዎች ማዕከል አድርገውታል።
ማንም ገንዘብ ይዞ የመጣ፣ በትውልዳችን፣ በቤተሰባችንና በማኅበረሰባችን ላይ “ጥናት አደርጋለሁ” እያለ እሴታችንን ለሚያጠፋ ነጋዴ በሩን ወለል አድርገው ከፍተውታል።
በ”ቅድመ-ጋብቻ ሥልጠና” ስም ወደ ቤተክርስቲያን ቅጥር ሰርገው የገቡት እንደ SRHR (ሥነ-ተዋልዶ ጤና፣ መብት) እና GBV (ጾታዊ ጥቃት)፣ መብብተና ነፃነት፣ ያሉ ቃላት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የቤተሰብ መዋቅርና የአባወራነትን ክብር፣ የቤተሰባችንን መዋቅር፣ የማኅበረሰባችንን ምሰሶና ማገር የሚንዱ መርዞች ናቸው።
እነዚህ ሥልጠናዎች በቤተክርስቲያን ስም ቢሰጡም፣ ይዘታቸው ግን የእግዚአብሔርን ቃል፣ ክርስትያናዊ ትውፊት ሳይኾን የግሎባሊስቶችን ትውልድ አጥፊ፣ ማኅበረሰብ አምካኝ የ”ጾታ ትርክት Gender Ideology” አጀንዳ የሚያስፈጽሙ ናቸው።
መለኮታዊው ጅራፍ እነዚህን መፈክሮች ቀዶና አቃጥሎ ሲጥላቸው፣ በውስጣቸው የታመቀው የሽንገላና የጥፋት መርዝ ለትውልዱ ግልጽ ኾኖ ይታያል።
የነጋዴዎቹ “መምህራን” ጠረጴዛዎች ሲገለበጡ፣ በእምነት ሽፋን የሚቸረቸሩት “የሴት ዲያቆን” እና “የሴቶች አመራር በቤክ” የሚሉ ሸቀጦች በቅዱሱ ስፍራ ቦታ እንደሌላቸው ይረጋገጣል።
ይህ በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የሚካሄድ ስውር የርዕዮተ-ዓለም ወረራ፣ ዓላማው የቤተሰብን መሠረት ማናጋትና ትውልዱን ካለማንነት ማስቀረት ነው።
አባወራነት ማለት የቤተሰብን ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላት ብቻ ሳይኾን፣ የመቅደሱንና የቤተሰቡን ቅጥር መጠበቅ ጭምር ነው። ዛሬ “በልጆቼ ትነግዳላችሁ!” የሚለው ቁጣ በዋነኝነት የሚያርፈው፣ ትውልዱን ለእንደዚህ ዓይነት የርኩሰት ንግድ አሳልፈው በሰጡና ዝምታን በመረጡ ጠባቂዎች ላይ ነው።
እውነተኛ አባወራ የቤተክርስቲያኑን ትውፊትና የቤተሰቡን ክብር ከርኩሰት የመጠበቅ መንፈሳዊ ግዴታ አለበት። መቅደሱ ከነጋዴዎችና ከወንበዴዎች ካልጸዳ፣ ትውልዱ የባዕድ አምልኮና የርዕዮተ-ዓለም ባሪያ መኾኑ አይቀሬ ነው። የግሎባሊስቶች አጀንዳ በቤተክርስቲያን መድረክ ላይ ሲደገስ፣ መድረክ ተዘርግቶለት ሲወደስ ዝምታን የመረጡ እረኞች ለትውልዱ መመክን ተባባሪዎች ናቸው። እያንዳንዱ አባወራ በመቅደሱ የሚነገዱትን ባዕድ አጀንዳዎች በመለየትና በማጋለጥ፣ ቤተሰቡንና ቤተክርስቲያኑን ከመመክን ትውልዱንም ከጥፋት ሊታደጋቸው ይገባል።
ትናንት ይህንን መሰል ጥፋት እያዩ ዝም ያሉ፣ “የሊቃውንቱን” ነጋዴነት ሲያውቁ ችላ ያሉ ምዕራባውያን በተለይም እንግሊዛውያን ትውልዳቸውን አጥተው፣ ማኅበረሰባቸው መክኖ ቀርተዋል።
ወንድምዓለም! ዛሬ የምናየው ሽኩቻ በሰዎች መካከል ብቻ ሳይኾን፣ በእውነትና በሐሰት፣ በትውፊትና በዘመናዊነት ስም በሚመጣ ጥፋት መካከል ያለ መንፈሳዊ ጦርነት ነው።
ቤተክርስቲያን የመንግሥተ ሰማያት ደጅ እንጂ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እንደፈለጉ የጽንሰሃሳብ (Ideology) ሸቀጣቸውን ማቅረቢያ መኾን የለባትም።
የቅዱሳን አባቶቻችን ደምና አጥንት የቆመችው ቤተክርስቲያን፣ ዛሬ በጥቂት የጥቅም ምርኮኞች እጅ መውደቋ የአባወራዎችን ቁጣና ንቃት ይጠይቃል፤ ግድም ይላል።
ይህ ኦርቶዶክሳዊውን ቤተሰብ እና ማኅበረሰብ ከውስጥ በሊቃውንቱ በሚሰጥ ከእሴቱ የተለየ ትርክት ራሱን በራሱ፣ ልጆቹንም በእጆቹ እንዲያጠፋ የተደረገበት ሸፍጥ ነው።
መቅደሱ ሲጸዳ ቤተሰብ ይጸናል፤ ቤተሰብ ሲጸና ደግሞ ትውልድ ይድናል። ስለዚህ፣ የአሁኑ ዘመን አባወራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ነቅተን መቆም፣ የባዕድ አጀንዳዎችን በመቅደሱ ቅጥር መቃወም እና ለልጆቻችን የማይበረዝ እምነትና ማንነትን ማውረስ አለብን!
ወንድሞቼ!
🚨 ትውልድ እያጣን ነው!
🚨 ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰባችን እየፈረሰ ነው!
🚨 ልጆቻችን እየተበተኑ ነው!
🚨 ትዳርን ታናናሾቻችን እየፈሩት እየጠሉትም ነው!
🚨 አልጫና ሆዳደር ትውልድ እያፈራን ነው!
🚨 የጠላቶቻችን መሳቂያና መሳለቂያ እየኾንን ነው!
🚨 ማኅበረሰባችንም እየመከነ ነው!
🚨 🚨🚨 ይህም ኾን ተብሎ “በራሳችን በተማሩቱ ሊቃውንቱ” እኔና አንተ አንቺም ባለንበት ጊዜና ዘመን፣ ዛሬ፣ አሁን እየኾነብን ነው!
0 Comments