ትውልዱን ከእውነቱ፣ ከእምነቱና ከእሴቱ ነጥለው ልባልባ በማድረግ ለጥፋትና ለሞት ሲጠብቁት፣ በአያት ቅድመ አያቶቹ ትውፊት ዳግም በክብር ይነሳል!
አሁን የምንገኝበት ጊዜና ዘመን በትውልዱ ላይ የሚደረገው ዘመቻ ከጦር መሣሪያ የከፋው ማንነትን የሚኮንነው መሣሪያ ነው።
ትውልዱን ከገዛ እውነቱ፣ ከጥንት እምነቱና ካሳደጉት እሴቶቹ ነጥሎ “ልባልባ” የማድረግ ስውር ደባ እየተፈጸመበት ይገኛል። በዚህ መንገድ ልባልባ የኾነው ትውልድ ደግሞ ይጠፋ ዘንድ ጦር አይሰበቅበትም ሰውነቱን የሚያጠፋበት፣ ማኅበረሰቡን የሚያመክንበት ልባልባነቱን ሰጥተውታልና!
በምሁራን ነን ባይ አድርባዮች ዘንድ የሚሰበከው አስተምህሮ ትውልዱን ባዶ የማድረግ የምንደኞች ስልት ነው። አድርባይነት በነገሠበት ሥፍራ፣ “መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውብ” የኾነውን መፈጸም፣ ለመፈጸምም መጀገኑ፣ ይህም ተገቢና ልክ የኾነ የክብርም መኾኑ ቀርቶ “በጥቅም በራስ ወዳድነት” ይተካል።
አስመሳይ አድርባዩም በተለይም ሆዳደር ሊቃውንቱም ታሪክን በማዛባት ትውልዱ እሴቱን እንዲጠላ፣ በዚያም ለባርነት የተመቸ፣ በአጉል መንፈሳዊነት ግን የታጀረ እንከፍ ምስኪን፣ ስልብ፣ አልጫ፣ ጃንደርባ እንዲኾን ይሠለጥናል።
ይህ ሥልጠና ስብከት ተብሎ በዐውደምህረት፣ መጽሐፍ ተብሎ በአዟሪ ደረት ይሸጣል። ትውልዱም ጠላት እንደፈለገው፣ ሆዳደሩም ሊቃውንት እንደደለለው ይኾናል።
ምን ቢማርና ማስትሬትና ዶክትሬት ቢይዝ ጭንቅላቱ በከንቱ ዕውቀት የነፈሰ፣ መመላለሱ በአጉል መንፈሳዊነት የታጀረ፣ ሆዱ ለጊዜያዊ ጥቅም ያደረ፣ ጽድቁን የሚፈጽምበት ወኔ- ልቡ ግን የጠፋ ትውልድ እንዲፈጠር ይደረጋል።
ልባልባ ትውልድ ታይታና ይኹንታን ብቻ የሚፈልግ ቀበጥ፣ ቀላጭ፣ እንደ ትቢያም በናኝ፣ አቋም የለሽ፦ ለሀገሩ፣ ለክብሩ፣ ለማንነቱ የማይቆም የአልጮች (Demoralized) ስብስብ ነው።
ይህ ስልታዊ ጥፋት ደግሞ የሚመራው እውነትን (ጽድቅን) የሚያስቀድመውን ትውፊታዊ መመሪያ ጥለው፣ በራስወዳድነት በጠፉ አድርባይ ሊቃውንት ነው።
ይህ አድርባይነት ትውልዱን ከጥንታዊውና ከታላቁ የኢትዮጵያዊ እሴት ነጥሎታል። ሥነ-ምግባራቸው የተመሰከረላቸው፣ ግርማሞገሳቸው የሚያስፈራ፣ ዓለምን በኃያለኛነታቸውና በጽናታቸው ያስደመሙት የአባቶቻችን ማንነት ዛሬ የለም! ማንም የሚንቀን፣ የሚደፍረን ጥላቢስ ኾነናል! በእብሪት ግን ታጅረናል!
ይህንን ትውልድ ማኅበረሰቡንም በትውፊት በእሴቱ ላይ መሥርቶ፣ አጽንቶ ማነጽ ታሪክን ከሚያውቁት ከሊቃውንቱ ወዲያ የማን ኃላፊነትና ሚና ነበር?
ይኹን እንጂ ከአያት ቅድማያቶቹ፣ ንግሥናን ከቅስና ሳይጋጭባቸው አስተባብረው ከያዙቱ “የተሻለ መንፈሳዊ ነኝ” ሲል የታበየው በሶሻሊስት ማርክሳዊ መርዝ ተመርዞ፣ በራስጠልነት የታጀረው፣ አንድም ለጠላት “በስባሪ ሳንቲም” የተቀጠረው “ምሁር” ወገኔን አጠፋው!
ያኔ ኢትዮጵያውያን በክብርና በጽድቅ የታወቁት በሆዳቸው ብቻ እንደ እንሰሳ፣ በአእምሮአቸው ብቻ እንደ “መላእክት” “ሀገራችን በሰማይ ነው” እያሉ በመታበይ ሳይኾን በልባቸው (በእሴታቸው) ይመሩ ስለነበር ነው።
በዓለም የናኘው ዝናቸው፣ ባሕርን የተሻገረ ግርማቸው፣ በስደተኞች የተወደደ ሞገሳቸው የተገነባው “ማንነቴን አለቅም፣ ለጥቅም አልደራደርም” በሚል ጠንካራ ስብዕና ላይ ነበር።
ዛሬ ግን እነዚህን ታላላቅ እሴቶች በትውልዱ ልብ ውስጥ እንዳይሰርጉ የሚያደርጉት በተለይም አጉል የኾነ መንፈሳዊነትን ከእሴትና ትውፊቱ ነጥለው በረቀቀ ዘዴ የትውልዴን ወኔ የሰለቡ፣ ጥቅማቸውን ያስቀደሙና ይህንንም በመጽሐፍና በመድረክ ያሰራጩ፣ ለውጭ ኃይሎች ያደሩ “ሆዳደር” ሊቃውንት ናቸው።
(ታሪካዊ መንፈሳዊ ተብለው የተሸጡልን መጻሕፍትና ደራሲዎቻቸውን እንዲሁም ስብከቶች ትውልዱን እንዴት ከአያት ቅድማያቶቹ እሴት ለይተው ልባልባ እንዳደረጉት፣ በዚያም የጀግንነትና የክብር ትጥቁን እንዴት ኮንነው እንዳስጣሉት ገምግሙ።
ጌታ በፈቅድና ብንኖር ደግሞ እነዚሁ አይነኬ፣ አይወቀሴ፣ አይከሰሴ ተደርገው በሚታዩ የቤተክርስትያናችን “ምሁራን” እና ተቋማት የተሰራጩትን ትውልድ የተሰለበባቸውን ተውሳኮች (Demoralizing Agents) “መንፈሳዊ የታሪክ” መጻሕፍት እንገመግማለን!)
ዐዲስ ትውልድ ይነሳል!
ትውልዱን ልባልባ፦ስሜታዊ፣ ጥቅመኛና ማንነቱን ያጣ፣ ኢትዮጵያዊነቱም መንፈሳዊነቱም ትናንት እነርሱ ሲመጡ የተጀመረ ይመስል ከትውፊቱ ቆርጠውት ለባርንት፣ ጥፋትና ለሞት ያዘጋጁት እነዚህ አድርባዮች፣ በትውልዱ ላይ የገነቡት የውሸት ማማ የሚፈርስበት ጊዜ ደርሷል።
ልባም ትውልድ የሚፈጠረው የትውልዱ አባቶች አባወራዎች ቤታቸውና ቤተመቅደሳቸውን በአያት ቅድማያቶቻቸው ትውፊት ላይ ሲተክሉ፣ በዚያም ጸንተው ሲቆሙ ነው።
ይህ ንቅናቄ ዓላማው ትውልዱን ወደ ቀደመው የአያት ቅድመ አያቶቹ የጀግንነት፣ የጽድቅና የክብር ትውፊት መመለስ ነው። ልባም ትውልድ ማለት በጭንቅላቱ (በእውቀት) እና በሆዱ (በፍላጎት) መካከል የሰውነቱ ሚዛን ልቡ ያለው፣ ለእውነት የሚሞት እንጂ በእውነት የሚነግድ ሸቃላ ያልኾነ ትውልድ ነው።
ይህ ትውልድ ሲነሳ፣ እነዚያ የቤተክርስቲያንንና የሀገርን ክብር የሸጡ አድርባይ ሊቃውንት በታሪክ ፊት ተዋርደው ይወድቃሉ። እነርሱ በርካታ ደቀመዛሙርትን አፍርተው ባቋቋሙት የአልጮች ማኅበር በርካታ ዘራቸውን የማይተኩ፣ መተካትም የማችሉና የማይፈልጉ ወኔ ቢስ ስልብ ጃንደርባ ትውልዶችን ካፈሩ ቆይተዋል።
እነርሱም ስለ እውነት፣ ስለ ጽድቅ፣ ስለ ክብር፣ ስለ ጀግንነት አይገዳቸውም። ይልቁንስ ባፍጢም የተደፉ ሆዳደር አስመሳይና አድርባይ፣ የእናት ጡት ነካሽ “ሊቃውንቱ” እንዳስተማሯቸው በአጉል መንፈሳዊነት” ታጅረው፣ በታጋቱት አልጫነት ታውረው፣ በጸደቀላቸው ባርነትና ጥፋቱ ይመክናሉ እንጂ።
በመኾኑም፣ የአሁኑ ዘመን አባወራዎች ኃላፊነት በራሳቸው ላይ ሠልጥነው ሲያበቁ ትውልዱን ከአስመሳይ አድርባዮቹ መዳፍ ነጥቆ ማውጣት ይኾናል።
ልጆቻችን ስለ ሆሜር ምስክርነት፣ ስለ ሄሮዶተስ አድናቆትና ስለ ክሩሴድ ዘመኑ “Prester John” ኃያልነት፣ ታቦት ይዘው ስለዘመቱት የአድዋ አንበሶች ግርማ ጀብደኝነት በቅደም ተከተል ሊነገራቸው ይነገራቸዋል።
“የቤተክርስትያን አካል ነን፣ ኢትዮጵያዊም ወገን ነን” ብለው ለልጆቻችን አልጫነትን መንፈሳዊነት፣ ጃንደርብነትንም ጽድቅ አድርገው ከሚግቷቸው ለይተን እናሳድጋቸዋለን።
በሆዳደሩ ቅጥረኛው “ሊቃውንት” የተኮነነውን የአባቶቻቸውን ታሪክ ጽድቁን ይፈጽሙ ዘንድ የሚጨከኑበትን ልብ ያንጽላቸው ዘንድ እናስተምራቸዋለን።
ይህ ታሪክ ተራ ተረት ሳይኾን፦ መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውብ የኾነውን ይፈጽሙ ዘንድ፣ አንድም ይፈጽሙበት ዘንድ የተሰጣቸውግ ጀግንነት፣ ማንነት።፣ ክብርም የሚያነቃቃ መለከት፣ ቀስቃሽም ነጋሪት ነው።
አድርባዮች በሚቆፍሩት የጥፋት ጉድጓድ ፋንታ፣ እኛ የጀግንነትን፣ የክብርን፣ የቅድስናን ኢትዮጵያዊ መሠረት እንጥላለን። ይህ ልባም ትውልድ ሲነሳ በእርግጥም በአስመሳይ አድርባዩ፣ ባንዳ የእናት ጡት ነካሹ መቃብር ላይ ይቆማል!
ያኔ መቅደሱ ከነጋዴዎች ይጸዳል፣ ቤተሰብም በጥንታዊው የአባወራዊው፣ አባታዊው ሥርዓት ይገነባል። የትውልድ ሽያጭ ይበቃ ዘንድ፣ እውነተኛው ተፈሪው፣ ተከባሪው፣ ተወዳጁ የኢትዮጵያዊነት ልብ ዳግም ሊመለስ ይገባል!
በእርግጥ ይህ ዜና የሆዳደሩን፣ የአልጫውንም (ወኔው የተሰለበውን Demoralized የኾነውን) ፊት እንዲያጠቁር፣ ዐይኑንም እንዲያቀላ ይገባናል! ግን ምንም ማድረግ አይቻልም! ትውልዱን ከአስመሳይ አድርባዩ ተናጥቆ ወደ ክብሩ መመለስ የእኛ የአባወራዎቹ ድርሻ ኾኗል! 💪
0 Comments