✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ተኩላ በዱር ያሉትን ያንበሳ ደቦሎች ከእሴት ማንነታቸው ለይቶ እንደ በግ ሊያኖራቸው እንደሚችል እርግጠኛ ነውና የተማሩ፣ ስለ አንበሳ ያጠኑና የተመሰከረላቸውን በጎችን ወደ ደቦሎቹ ይልካል፤ እነርሱም በአንበሳ ሰውነት በበግም ልብ ያድጋሉ!
(ከቀናት በፊት “በበጎች የተመራው ያንበሳ መንጋ” በሚል ከተጻፈው የቀጠለ)
ተኩላ አንበሶችን ድል ማድረግ የሚችለው በጉልበት ሳይኾን ማንነት ተፈጥሮአቸውን በመስለብ “በጥበብ” እንደኾነ ጠንቅቆ ያውቃል።
አንበሳን አንበሳ የሚያደርገው ጥርሱና ጥፍሩ ብቻ ሳይኾን፣ በውስጡ ያለው፣ አንበሳነቱ በተበየነበት ልቡ ጭምር በተለይም እንደኾነም ያውቃል።
ተኩላው ይህንን መንፈስ ለመስለብ የሚጠቀመው ስልት ደግሞ ስለ አንበሳ ተፈጥሮ በሚገባ ያጠኑ፣ የተመሰከረላቸውንና “የዱሩ ሊቃውንት” የተባሉ በየዋህነታቸው፣ በትኅኅተናቸው፣ በጨዋነታቸው፣ በቅንነታቸው... የተመሰከረላቸውን “የተማሩ በጎችን” ወደ አንበሳ ደቦሎች ይልካል።
እነዚህ በጎች በአንበሶቹ መካከል ተቀምጠው ስለ አንበሳ ግርማ ይተርካሉ፣ ስለ ጀግንነት ይፎክራሉ፣ ለነፃነት ይንጓደዳሉ፣ በልበሙሉነትም ይንጎራደዳሉ። ነገር ግን ትምህርታቸው ሁሉ ምን ያንበሳ ቢኾን እነርሱ ግን በጎች ናቸውና በበጎች ድምጸትና ቅላጼ ለደቦሎቹ ይደርሳቸዋል።
ደቦሎቹ እነዚህን በጎች እንደ መምህር አክብረው ሲሰሙ፣ ሲማሩ ቆይተው ምን ስለ አንበሳነታቸው ቢያውቁም ሳያስተውሉት ግን የመምህሮቻቸውን በጎች ልብ ይይዛሉ። እየሰሙ ያደጉት ድምጽ፣ እየተከተሉ ያደጉት መንጓደድ፣ “የልበሙሉነቱም” መንጎራደድ ሁሉ የበጎች ነበርና እነርሱም “በግነቱ” ይጸናባቸዋል።
ልባቸው በታነጸበት ማንነታቸውም እንዲሁ ይኾናል።
በጎቹ ስለ አንበሳ ተፈጥሮ፣ ስለ ጀግንነትና ስለ ታሪክ እጅግ የተራቀቀ ትንታኔ ይሰጣሉ። ነገር ግን ትምህርታቸው ደቦሎቹን አንበሳ ሊያደርግ አይችልም፤ ምክንያቱም አስተማሪዎቹ በጎች ናቸውና፦ ድምጻቸውና ድምጸቱ፣ ቅላጼውና ፍሰቱ፣ ዓይናቸውና አኳኋኑ ሁሉ ልባቸውን ወደ አንበሳነት ከማነጽ ይልቅ ወደ በግነት ያመጣዋል።
በውጤቱም በአንበሳ ሰውነት ውስጥ የበግ ልብ ይዘው የሚያድጉ፣ ለተፈጥሮአዊው ማንነታቸው ባይተዋር የኾኑ፣ ዐዲስ ያልጫ ልብ የተፈጠረላቸው፣ አንበሳ መሳይ በጎች፣ “አልጫ አንበሶች” ይኾናሉ።
ዛሬ በማኅበራዊ ሚዲያና በመገናኛ ብዙኃን የምናያቸው ብዙዎቹ “ምሁራን” ተብለው የሚቀርቡቱ የእነዚህ የተማሩ በጎች ምሳሌ ናቸው።
ስለ ሀገር ፍቅር፣ ስለ ድንበር መከበርና ስለ ጀግኖች አባቶች ታሪክ ለሰዓታት ሙሉ ሊሰብኩ ይችላሉ፤ በተግባር ግን፦ የገዛ ቤታቸውና ሰፈራቸው በጠላት ሲደፈር፣ ሚስትና ልጆቻቸው በባዕድ አስተሳሰብና በግፍ ሲገረፉ “ቢቻላችሁ ከሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” እያሉ በሽንገላ የሚሸሹ የፈሪዎች ስብስብ ናቸው።
ስለ ጥንካሬ፣ ኃይልና ሥልጣኔውም ሲያወሩ ካወቁት ካነበቡት እንጂ ከኖሩት፣ ከገነቡት፣ ከተገለጡበት፣ በተግባርም ከተመላለሱበት አይደለም።
ስለ አባወራነትና ስለ ኃላፊነት ብርቱ ምክር ይለግሳሉ፤ በተግባር ግን፦ በገዛ ቤታቸው ሥልጣን የሌላቸው፣ ለልጆቻቸው አርአያ መኾን ያልቻሉ፣ ልባቸው በስምምነትና በአድርባይነት የወደቀ ምስኪኖች ናቸው።
በኑሮአቸው የማይኖሩትን ጀግንነት በንግግር ያስተምራሉ፤ በሕይወታቸው ያልገነቡትን ስብዕና በጽሑፍና በዩቲዩብ ይሰብካሉ፤ እንዲሰብኩም መድረክ ይዘረጋላቸዋል።
ለምን?
ትውልዱ በእነዚህ አስመሳዮች፣ ደስ በሚል ትርክታቸው፣ የማይካድ የማይሞገት በኾነ ደረቅ ሐቅ ትምህርታቸው ተደልሎ በአእምሮው “ጀግና” ነገር ግን በልቡ “አልጫ” ኾኖ እንዲያድግ ነው ሸፍጡ።
ይህንንም ዓይነ ውሃቸው፣ ድምጻቸው፣ ድምጸታቸው፣ ቅላጼያቸው የሠራ አካላቸው ይህንኑ ይመሰክራል። ይኹን እንጂ የተናገሩት ደረቅ ሐቅ በመኾኑ ብዙዎችን ይስባል፤ የሚናገሩት ለስላሳና “ደስ የሚል” በመኾኑ ጆሮን ይይዛል፣ ወንድነትና አባወራነትን ሲኮንን በከረመው ማኅበረሰብ መካከል ላደገውም ልብን ይገዛል። ነገር ግን ደፋር፣ ጀግና፣ ጠንካራና ኃይለኛ ኾኖ ጽድቁን የሚፈጽምባቸውን ሳይኾን ምን ቢማር ሆዳደር አድርባዩን አልጫ ያፈራሉ።
ትውልዱ የአባቶቹን የመሰለ ወንድነት አባወራነት አይነገረውም፤ እንዲነገረው፣ አንዲሰማም አይፈለግም። ስለኾነም ሌላ ሲሰሙት ደስ የሚል፣ ሲገባም የሚለሰልስ እንጂ የማይቆረቁር ነገር ግን ጽድቁን ይፈጽሙበት ዘንድ የማያስችላቸውን ዐዲስ ማንነት፣ ወንድነት፣ አባወራነት በእነዚያ “ሊቃውንት በጎች” እንዲነገረው ይደረጋል።
እነዚህ “ምሁራን” ትውልዱን ከእሴቱና ከታሪኩ ለይተው በባዕድ አጀንዳ እንዲጠመቅ ያደርጉታል። Transforming Patriarchal Masculinities ይሉታል በእንግሊዘኛው ወደ አማርኛው ሲመልሱት ግን የተለያዩ ሸፍጡን የሚደብቁ ስሞችን ትርክትንም ይሰጡታል።
ትውልዱ ወንድ ከወንድም ጽድቁን መፈጸም የሚችል አባወራ እንዲኾን አይፈለግምና፤ እንለብሰው እንላበሰውም ዘንድ “ዐዲስ” ወንድነት አባወራነትም ተቀዶ እየተሰፋልን ይገኛል።
አስተውሉ!
አንበሳው ደቦል ድንበሩን ማስከበር፣ ቤተሰቡን መጠበቅና በራሱ መቆም ሲገባው፤ በእነዚህ በጎች የእውነት፣ እምነትና እሴት ትምህርቱ ጽድቁን የሚፈጽምበት፣ አንበሳነቱ የሚበየንበት ማንነቱ ጠፍቶ እንደ በግ ይኖራል።
ይህ ትውልዱን ከተገኘበት ጽኑ እሴት ለይቶ ለባርነት የማመቻቸት ስልታዊ ዘመቻ ነው። ተኩላው በቀጥታ መጥቶ የአንበሳውን ደቦሎች “በግ ኹኑ” ቢላቸው እንደማይሰሙት ያውቃል፤ ስለዚህ ሊቃውንቱን በጎች ወደ አንበሳው ደቦሎች ልኮ፦ የአንበሶቹን ማንነት በበጎች ያሰብካል።
አንበሳውም በበጎች መካከል እያደገ ሲሄድ፣ የገዛ ጥፍሩን እንደ ሸክም፣ ወኔውን ደግሞ እንደ ነውር፣ አንበሳነቱን ደግሞ እንደ እርግማን ቆጥሮ እንዲጠላውን፣ እንዲጠየፈውና እንዲጥለውም ይደረጋል።
ወንድምዓለም! ልጆችህ እውነትን፣ እምነትንና እሴትን ከማን ይማራሉ? የሚያስተምሯቸውስ የሚናገሩትን ይኖሩታል? ወይንስ ያንተን የአንበሳውን ደቦሎችህን በግ ለማድረግ የተላኩ “የተማሩ በጎች” ናቸው?
ንቃ! የአንበሳ ደቦል አንበሳ እንዲኾን የአንበሳ ልብ ካለው አባቱ ጋር መዋል አለበት። ከአልጫ ምሁራንና ከሆዳደር ሊቃውንት ትርክት ራስህንና ቤተሰብህን ነፃ አውጣ። ትውልዱ የአእምሮ ብቻ ሳይኾን የልብ ጀግና እንዲኾን፣ በተግባር፣ በንግግር የሚታይ የሚኖር የአባወራነት ግርማህን አሳየው!
በየስክሪኑ ላይ ጀግንነትን የሚተርኩትን ሳይኾን ጀግንነትን የሚኖሩትን ለይተህ እወቅ። አንበሳነት በበጎች አይነገርም፣ ጀግንነት በአልጮች አይሰበክም፣ ወንድነትም በምስኪናን አይተረክም፣ አባወራነትም በጃንደርቦች አይኖርም!
የቤትህ ደቦሎች የአንበሳን ግርማ ይዘው፣ ለቤተሰባቸውና ለሀገራቸው መከታ እንዲሆኑ ካስፈለገ፣ ከነዚህ “የተማሩ በጎች” ወጥመድ አውጣቸው።
የአንበሳን እውነት፣ እምነትና እሴት፤ ባሕርዩንና ዓላማውን የሚኖርበት አንበሳ ከነድክመቱ ሲተርከው እና፤ አንበሳነትን ያጠናው፣ ማስትሬትና ዶክትሬት የሠራበት ነገር ግን የማይኖርበት ሊቀ-ሊቃውንቱ በግ ሲተረተረው ውጤቱ ይለያያል፤ ፍጹምም ይቃረናል!
አንዳን ከምስኪንነት ያልተላቀቁ የዋሃን ግን፦
👉 ቆይ መልክቱ እውነት አይደለም?
👉 ቢያንስ ላልሰሙት ደቦሎች መድረስ የለበትም?
👉 መልእክቱ መልካም፣ ልክና ተገቢ ከኾነ...
👉 ምናለ በጎችም የአንበሳው እውነት፣ እምነትና እሴት እንዳይጠፋ የራሳቸውን ጠጠር ቢጥሉ? ወዘተርፈ ይላሉ!
ምን ይታያችኋል?
0 Comments