“ጨጓራ ላጡ ኩላሊት አፍርጡ” ሳይኾን ሠልጥኑባቸው!

ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ጠላት የላካቸው ምንደኞች አልያም ጉስቁልና “የጸደቀላቸው” ምስኪኖች ትውልዱ በራሱ ላይ ሠልጥኖ፣ በልጽጎና አይሎ ጽድቅ የሚፈጽምበትን ሳይኾን አቅመቢስ፣ ጎስቋላና አልጫ ኾኖ በባርነት የሚያድርበትን ልምምድ አጽድቀው ይግታሉ!

💪 ይህ የአባራው ንቅናቄ ድምጽ ነው!

🎯 ትውልዱን፤ ከትውልዱም ወንዱን ወደ አባቶቹ ግርማ፣ ወደ አባወራነት ማማ ለመመለስ የተናጠ፣ ከምንደኞች መዳፍ፣ ከጠላትም መንጋጋ ለመናጠቅ የሰጠ!

🎯 ባልጫነት ለመሰንበትና ለመክረም ለሚፈልጉ፣ የአባቶቻቸውን ክብርና እሴት ንቀው፣ ጠልተውና ተጠይፈው በማርክሳውያን የብሶትና የአቅመቢስነት ትርክት ለተወዘቱት በጭራሽ አይኾንም! ይመራል!

በእርግጥ “ጨጓራ ላጡ ኩላሊት አፍርጡ” ብለው በአደባባይ የሚያስተምሩ፣ ያስተማሩም ባይኖሩም ነገር ግን የሚታይ፣ የሚሰማና የሚመሰከር ኑሮአቸውና የንግግራቸው መልእክት በዚያ ሐረግ የሚቋጭ ነው።

ብዙዎች ሕይወትን በተለይም ክርስትናን ከመጣበት ዐውዱና እሴቱ፣ አባቶቻችን ከሄዱበትና ከተገለጡበት ከሚታወቁበትም ለይተው ደንበኛ የባሮች “የውርደት ማዕረግ”፣ የግዞታቸው ሕይወት፣ የምንደኞችም ወግ፣ አድርገውታል።

አስታውሳለሁ በአንድ ወቅት (ከዛሬ አስራ እምርት ዓመት በፊት) በአራዳ ጊዮርጊስ ስለ ምስጢራት የሚያስተምሩን መምህር ባህታዊ አይደሉም፣ ዓለማዊ፣ ወጣትም ናቸው፤ ነገር ግን ሰውነታቸው አልቆ፣ ነጠላ ማጣፊያ ትከሻቸው ወድቆ “ምን ኾነው ነው?” ስል “እጅግ መንፈሳዊ ጧሚ ጦሎተኛ ናቸው፣ እህል አይበሉ እንቅልፍ አይተኙ፣ ታድለው፣ ....” የተባልኩትን አልረሳውም።

ትውልዱ ቢችል ቢጎሳቆል፣ እየበላ መጎሳቆል ባይችል እንኳ በተጎሳቆሉት ቢቀና “መንፈሳዊ በረከት” የሚገኝ ሳይኾን የሚታፈስ ይመስለዋል።

ህም!

በራስ ላይ፦ በስሜቶቻችንና በሃሳቦቻችን፣ በብልቶቻችንም ላይ መሠልጠን ሳይኾን በራሳችን ላይ እንሠለጥንበት ዘንድ በተሰጠን መሣሪያ ራስን ማጥፋት፣ ማጎሳቆልና ማድቀቅ “መንፈሳዊነት፣ አምልኮ” ብለንም የሄድንበት “የእውቀት” ነገር ግን የእብሪት መንገድ፣ በዚያ የእብሪት መንገድም ታጅረን የወደቅንበት የአዘቅቱ ጥልቀት አይለካም!

ጽድቅ እንሠራበት ዘንድ በተሰጠን ጡንቻችንም ኾነ ስሜቶቻችን፣ ፍላጎቶቻችን፣ ሃሳቦቻችንና ብልቶቻችን መሠልጠን የእኛ ፋንታ ነው።

ካላወቅንበት ደግሞ አባቶቻችን፦

👉 ቤተ-መንግሥትንና ቤተ-ክህነትን፣

👉 ዓለማዊ አስተዳደርና መንፈሳዊ እረኝነትን፣

👉 በልዕልና መንገሥንና በትኅትና መታዘዝን እንዴት አስተባብረው እንደኖሩ መመርመር!

በተረፈ ግን፦

🎯 ሰውነታችን አልቆ፣

🎯 ጉልበታችን ደቆ፣

🎯 ወኔያችን ላሽቆ፤

🎯 ጨጓራችን ተልጦ፣

🎯 ኩላሊታችን ፈርጦ፣

🎯 ጉበታችን አብጦ፣

🎯 ትከሻችን ጎብጦ፣

🎯 ራሳችን ተመልጦ፣

🎯 ጥርሳችን ገጦ፣

🎯 አጥንታችን ፈጦ፣

🎯 ስኳራችን ተሟጦ፣

🎯 ደማችን ተመጦ፣

ይህም ሁሉ ኾኖ እንኳ ዛሬም በስሜቶቻችንና በሃሳባችን የምንሰቃይ ሲኾን ኪሳራው እጥፍ ድርብ ይኾናል!

ወንድምዓለም! “ጨጓራ ላጡ ኩላሊት አፍርጡ” ሳይኾን ሠልጥኑባቸው፣ ሠልጥናችሁ ስታበቁም አበልጽጓቸው፣ አበልጽጋችሁ ስታበቁም፣ አይላችሁባቸውም ስታበቁ በዚያም ጽድቅ ሥሩባቸው ተባለ እንጂ!

ጾመው፣ ከስተው፣ መንምነው ትውልድን፣ ቤተክርስትያንን፣ ሀገርን ለጠላት ባንዳ ኾነው የሚሸጡ፣ ከእረኝነቱ ይልቅ ምንደኝነቱ የሚበልጥባቸው እኮ ራሳቸው ላይ ይሠለጥኑበት ዘንድ የተሰጣቸው መሣሪያ የዳለጠ፣ ጽድቅን የማይፈጽም፣ (”እስፓናቶ የኾነ” እንዲሉ መካኒኮች) የይስሙላ ልማዳዊ ስለኾነ እንጂ ነው።

እነርሱም ትውልድ አቅመቢስ፣ ጎስቋላና አልጫ ኾኖ በባርነት የሚያድርበትን ልምምዳቸውን አጽድቀው ይግታሉ! ጠላት የላካቸው ምንደኞች አልያም ጉስቁልና “የጸደቀላቸው” ከአባቶቻቸው እሴትና ትውፊታቸው የተለዩ ትውልዱ በራሱ ላይ ሠልጥኖ፣ በልጽጎና አይሎ ጽድቁን የሚፈጽምበትን ሳይኾን አቅመቢስ፣ ጎስቋላና አልጫ፣ አላዛኝና ነፍራቃ ኾኖ በባርነት የሚያድርበትን ልምምድ አጽድቀው ይግታሉ!

ወንድምዓለም!

💪 ይህ የአባወራው ንቅናቄ ድምጽ ነው!

🎯 ትውልዱን፤ ከትውልዱም ወንዱን ወደ አባቶቹ ግርማ፣ ወደ አባወራነትም ማማ ለመመለስ የተነቀነቀ፣ ከምንደኞች መዳፍ፣ ከጠላትም መንጋጋ ለመናጠቅ የቀነቀነ!

🎯 ባልጫነት ለመሰንበትና ለመክረም ለሚፈልጉ፣ የአባቶቻቸውን ክብርና እሴት ንቀው፣ ጠልተውና ተጠይፈው በማርክሳውያን የብሶትና የአቅመቢስነት ትርክት ለተወዘቱት በጭራሽ የማይኾን!

👉 ሲመር ሲጎመዝዝህም ይህን አስታውስ!

በእርግጥ “ጨጓራ ላጡ ኩላሊት አፍርጡ” ብለው በአደባባይ የሚያስተምሩ፣ ያስተማሩም ባይኖሩም ነገር ግን የሚታይ፣ የሚሰማ፣ የሚመሰከእም ኑሮአቸውና የንግግራቸው መልእክት በዚያ ሐረግ የሚቋጭ ነው።

“እገሌ ሞተ!”

“እንዴት ሞተ?”

“እርሱኮ መንፈሳዊ፣ ታራሚ፣ ጧሚ፣ ጦሎተኛ.. ነው፤ እህል አይበላ፣ እንደ ሰዉ ይህንና ያ አያምረው፣ ለነፍሱ የሚኖር፣ ሰውነቱ አልቆ፣ ጨጓራው ተልጦ፣ ኩላሊቱ ፈርጦ፣ ጉበቱ አብጦ፣ ስኳሩ ተሟጦ... የሚኖረው እኮ ለሰው ነው፣ ለራሱ አይኖር...”

እንዲህ ብለው፣ እንዲህም እያሉ ትውልዴን አቅመቢስ ጎስቋላነት፣ ደካማ ልፍስፍስነት፣ እንከፍ ምስኪንነት ክርስትና መንፈሳዊነት እንደኾነም ይግቱታል!

ወንድሞቼ! በተሰጣችሁ ጸጋ፣ በወንድነት መክሊቱ፣ በብልቶቻችሁና በስሜቶቻችሁ፣ በፍላጎቶቻችሁና በሃሳቦቻችሁም ሠልጥኑባቸው፤ ትሠለጥኑበት የተሰጣችሁንም መሣሪያ፣ ግብ ሳይኾን መንገድ፣ አድራሽ፣ አንጋሽ አድርጉት እንጂ!

በልማድ ኩላሊት አፍርጠው፣ ጨጓራ ልጠው፣ ጉበት አሳብጠው፣ ስኳር አሟጠው ነገር ግን በስጋ አምሮቱ ተሸንፈው አስመሳይና አድርባይ ባንዳና የእናት ጡት ነካሽ፤ አልያም እንከፍ፣ ከረፈፍ እንደኾኑት፣ ኾነውም እንደወደቁት፣ መውደቃቸውንም ከመንፈሳዊነት አጽድቀው እንደጠፉት አትኹኑ!

አባታችሁን፣ አባቶቻችሁንም ምሰሉ!

በግርማና በልዕልናም ተመላለሱ!

በራሳችሁ ላይ ሠልጥናችሁ ጽድቁን ፈጽሙበት እንጂ “እንቅፋት” ብላችሁት በእብሪት ታጅራችሁ አትጥፉ!

ይህ የአባወራው ጥሪ፤ ድምጽም ነው!

Post a Comment

0 Comments