አሮጌው ዐለም ሲሞት በዐዲሱ ይተካል፤ የአጋንንትም ይኾናል!

✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

የሰው ልጅ የመጣበት፣ ሰውነቱን የበየነበት፣ ይህም የተመሰከረለት ነባር ሥርዓት ሲፈርስ ተፈጥሮአቸው የሰው፣ ግብራችው ግን የአጋንንት የኾኑ ሰዎች ይቀራሉ!

ርዕሱ ግራምሺ በፋሺስት ጣልያን እስር ቤት ኾኖ ሳለ Prison Notebooks በሚለው መጽሐፉ አስፍሮታል ተብሎ የሚታመነው ኃይለቃል ነው።

"The old world is dying, and the new world struggles to be born: now is the time of monsters."

አንቶኒዮ ግራምሺ “አሮጌው ዓለም እየሞተ ነው፣ ዐዲሱም ለመወለድ እየታገለ ነው” ሲል፦

👉 ማርክሳዊ ሶሻሊስት አብዮቱን፣

👉 ባህላዊ አመጹን፣

👉 እሴታዊ ለውጡን እንደ አንድ ታሪካዊ አስፈላጊነትና ወደ ነፃነት የሚደረግ ግስጋሴ አካል አድርጎት ሊኾን ይችላል።

ነገር ግን በታሪክ መነጽር የሩቁን አቅርበን ስንመለከተው በተግባር የታየው እውነት የሰው ልጅ “ሰውነቱን የበየነበት” ነባር ሥርዓት ሲፈርስ፣ በቦታው በመብትና በነፃነት ስም የሚተካው ዐዲስ ሰብአዊነት ሳይኾን ተፈጥሮአቸው የሰው፣ ግብራቸው ግን የአጋንንት የኾኑ ሰዎች መፈልፈል መብዛትም ነው።

ይህ ሽግግር የሰው ልጅ ለዘመናት የገነባቸውን፣ እንደ ሃይማኖት፣ ቤተሰብና ትውፊታዊ አባወራነት ያሉ የሞራል መሠረቶች፣ የማኅበረሰብ ምሰሶዎች፤ በማርክሳውያን “አሮጌ” ተብለው እንዲናቁ፣ እንዲጠሉና ትውልዱም እንዲጠየፋቸው በማድረግ፣ ማህበረሰቡን ያለ መሪና ጠባቂ፣ ያለ አጥርና ቅጥር ለጥፋት ለጠላትም አሳልፎ መስጠት ነው።

የሰው ልጅ ማንነቱ የሚረጋገጠውና ትርጉም የሚሰጠው በገነባው ጠንካራ፣ የማይካድና የማይደፈር ስብዕና ነው። እርሱም ከቆመበት ፅኑ መሠረት ላይ የሚበቅል፣ የሚያፈራ የትናንት ዘር የዛሬ ፍሬ ነው።

ይህ መሠረት ደግሞ የመጣበትን ማንነት የሚያውቅበት፣ ኃላፊነቱን የሚረዳበትና ለፈጣሪውና ለቤተሰቡ ያለውን ግዴታ የሚወጣበት ነባር እሴት ነው።

ግራምሺና መሰል ርዕዮተ-ዓለም አቀንቃኞች፣ የእኛም ሀገር ግራ ዘመምተኞች ይህንን ሥርዓት “የበላይነት መሣሪያ” አድርገው በመፈረጅ ሊያፈርሱት ሲነሱ፣ በምትኩ የፈጠሩት ዓለም ግን የሰውን ልጅ ወደ ዕቃ- ቁሳቁስነት ዝቅ ያደረገ ነው።

ካርል ማርክስ በግጥሞቹና በጽሁፎቹ ዓለምን የመደምሰስና የመበቀል ስሜት ሲያሳውቅ እንደነበረው ሁሉ፣ ይህንን “አሮጌ” የተባለ ሥርዓት ለመናድ የተነሱት አብዮቶችም ውጤታቸው እንደ ስታሊን፣ ሌኒንና ማኦ፣ እንደ ሀገራችንም መንግሥቱ ያሉ ጨካኝ መሪዎች መፈጠር ኾነ።

እነዚህ ኃይሎች ለብዙኃን ነፃነትና እኩልነት በሚል ሰበብ የንጹሐንን ደም እንደ ጎርፍ አፈሰሱ፣ በመቶ ሚሊዮኖች አለቁ፤ ይህም የሰው ልጅ የተፈጥሮ ክብሩን ጥሎ ወደ አጋንንታዊ ግብር የወረደበት የጥፋት ምዕራፍ ኾነ።

ምንም እንኳ ይህ በፖለቲካው መስክ የታየ እልቂት ቢኾንም ዛሬ ደግሞ በባህላዊና በማህበራዊ ህይወት ውስጥ እጅግ በከፋ መልኩ ቀጥሏል።

የሴቶች መብትና ነፃነት በሚል ሽፋን፣ እ.ኤ.አ. ከ1973 ጀምሮ በዓለም ላይ የታየው የውርጃ መስፋፋት የሰው ልጅ ከምንም በላይ ቅዱስ አድርጎ የሚመለከተውን የሕይወት እሴት ምን ያህል አርክሶ ለልባልባነት እንደተዳረገ ማሳያ ነው።

አንዲት እናት በገዛ ማህፀኗ ውስጥ ያለውን ምንም የማያውቅ፣ ንጹሕና ቅዱስ የኾነ፣ የአባቱና የአምላኩ መልክ የተሳለበትን ሕፃን በመርዝ በጣጥሳ በመቀስ ቆራርጣ የምትገድልበት መንገድ “ከበዝባዡ፣ ጨቋኙና በዳዩ አባወራዊ ሥርዓት የምትላቀቅበት ዐዲስ የመብትና የነፃነት መንገድ” ተባለ። በዚያም በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሕጻናት ነፍስ ተጨናገፈ!

በተጨማሪም ቤተሰብ እንደ ተቋም የሚፈርስበትና የልጆቹ የቤተሰቡ አናጺ፣ ጠባቂ አባወራውና ሥርዓቱ እንደ ጨቋኝ መዋቅር የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ደረስን።

🚨 ይህ “ዐዲሱ ዓለም ለመወለድ ሲታገል የሚከፈለው መስዋዕትነት ነው” ቢለንም ግራምሺ፤ እኛ ግን የሰው ልጅን የሚያድስ ሳይኾን፣ ሰብአዊነትን አጥፍቶ በቦታው ልብአልባነትን የሚተካ አጋንንታዊ ሂደት መኾኑን እንረዳለን።

“አሮጌ” የተባለው ሥርዓት ሲፈርስ በሚቀረው “ልባልባነት” ሰውነት ይጠፋበታል፣ ማኅበረሰብ ይመክንበታል፣ ሀገር ይፈርስበታል።

ጥልቅና ስር የሰደዱ እሴቶች በውጫዊና ጊዜያዊ ስሜቶች ሲተኩ፣ ሰው የሕይወትን ትርጉም ከፈጣሪውና ከቤተሰቡ ሳይኾን ከፖለቲካዊ ትርክቶችና ከግለኝነት ፍላጎቶች መፈለግ ይጀምራል።

ይህ ደግሞ When all that says ‘it is good’ has been debunked, what says ‘I want’ remains,” C.S. Lewis’s The Abolition of Man ያስታውሰናል።

በዚያም ግብሩ ከአጋንንት የማይለይ፣ ለንጹሐን ደምና ለትውልድ መጥፋት የማይራራ ትውልድ እንዲፈጠር፣ ይህንም ደግሞ በመብትና ነፃነት ስም ለሚፈጽመው ልብአልባ ትውልድ መገኘት ምክንያት ኾኗል።

ስለዚህ ነባር እሴቶችን መጠበቅ ማለት አሮጌ አስተሳሰብን መያዝ ሳይኾን፣ የሰውን ልጅ “ሰው” አድርገው ያቆዩትን፣ ሰውነቱን የበየኑትን የሞራል አጥሮች እንዳይፈርሱ መከላከል ነው።

እነዚህ አጥሮች በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ሰበብ በተለይ በልሂቃኑ ይበልጡንም በሊቃውንቱ ተንደው የሚመጣው “ዐዲስ ዓለም” የአጋንንት እንጂ የሰዎች፣ ያውም በእግዚአብሄር አርአያና ምሳሌ ለተፈጠሩቱ፣ በዐዲስም ኪዳን ለታደሱቱ መኖሪያ መናኃሪያ ሊኾን አይችልም!

Post a Comment

0 Comments