ትውፊት ሲባል ዝም ብሎ ያለፈ ታሪክ ሳይኾን፣ የቀደሙት አባቶቻችንና እናቶቻችን በጥብቅ ያምኑባቸውና ይኖሩባቸው የነበሩ፣ ዛሬም በውስጣችን ሕያው ኾነው የሚቀጥሉ እሴቶች ማለት ነው።
አንድም ትውፊት በትላንትናው መቃብር ላይ የቆመ የደረቀ ሐውልት አይደለም፤ ይልቁንስ ከአባቶቻችን ልብ ወደ እኛ ደም ስር የፈሰሰ ሕያው እውነት እንጂ ነው።
ይህ እውነት ትውልዱ ራሱን የሚያይበት መስታወት፣ የነፍሱንም ስብራት የሚጠግንበት፣ ማኅበራዊ አንድነቱንም የሚያጸናበት መመሪያ ነው።
ማንኛውም ትውልድ ማንነቱን የሚበይነውና “እኔ ማን ነኝ?” ለሚለው ጥልቅ ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ካለፈው ዘመን በወረሳቸውና ዛሬም በውስጡ በሚያስተጋቡት እሴቶች አማካኝነት ነው።
እነዚህ እሴቶች ዝም ብለው የሚወሩ ተረቶች ሳይኾኑ፣ እንደ ዘር በውስጣችን ተቀብረው ዛሬ ለምናፈራው ማንነት ማዳበሪያ፣ ማነጫ፣ ማበልጸጊያ የሚኾኑ የሕይወት መርሖች ናቸው።
ትውልዱ እነዚህን እሴቶች ሳያውቅና ሳይረዳቸው ቢቀር፣ ማንም እንደ ነፋስ የሚነዳውና የራሱ መቆሚያ የሌለው ባይተዋር፣ ለባርነት የተሰጠ፣ ከእሴቱ ውጪ ቢማርም ባርነቱን የሚያጠናክርበት ይኾናል።
እሴቱን ለይቶ ያወቀ ትውልድ ልቡን በእውነት ላይ ያንጻል። የቀደሙት አባቶቻችን የኖሩበትን የክብር፣ የታማኝነትና የጀግንነት የቅድስናም መንፈስ ጠብቆ መያዝ ማለት የድሮውን ልብስ መልበስ ሳይኾን፣ የድሮውን ጽናትና ጥበብ ለዛሬው ኑሮ ስንቅ ማድረግ ማለት ነው።
ይህንን እውነት ትውልዱ እንደሚታነጽበት አምኖ ሲኖርበት ሰውነቱ የሚታወቅ የሚረዳለት ሲኾን ከዚያ በተቃራኒው ሲሄድ ደግሞ ሰውነቱ ባዳ፣ ባዕድ ኾኖበት የሚጠፋበት ይኾናል።
አንድም ይህንን እውነት ትውልዱ ይታነጽበት ዘንድ ሊቃውንቱ አምነውና አውቀው፣ እንዲኖርበት ግድ ብለው ሲሰጡት፣ ሲኖሩትም ሰውነቱ የሚታወቅ የሚረዳለት፣ የሚድንለትም ይኾናል።
🚨🚨🚨 አለበለዚያ ግን ከዚህ ትውፊት ያልኾነ፣ ከባዕዳን ያመነዘረ፣ በባዕዳን ሸፍጥ የተዳቀለ ባፍጢም ተደፍተው በተገዙበት ምንደኝነታቸው የመረዙትን ቢግቱት ግን፤ አባቶቹን ፍጹም የማይመስል ነገር ግን አስመሳይ፣ አድርባይ ልባልባ ትውልድ ይገኛል፤ በዚያም ሰውነቱ ይጠፋል ይመክናልም!
እሴት ማለት እንደ ጨለማ ግር የምንሰኝበት ዓለም ውስጥ ከአያት ቅድማያቶቻችን በተቀበልነው አቅጣጫ ጠቋሚ፤ ወደብ ምዕራፋችንን የምናስስበት ነው።
ትውልዱ ይህንን “ሕያው እምነት” አውቆ ሲኖርበትና ሲጠቀምበት ብቻ ነው ከተራና ልማዳዊ ባህላዊነት ድርቀት ወጥቶ ወደ ትውፊታዊነት ሕይወት የሚሸጋገረው።
ማንነት የሚገነባው ካለፈው በምንረከበው ጽናትና ዛሬ ላይ በሚገኘው ንቃት መገናኛ ላይ በመኾኑ፤ እሴቶቻችንን መኖር ማለት አባቶቻችንን በኑሮ መምሰል ብቻ ሳይኾን፣ እኛም ለሚመጣው ትውልድ የሚተላለፍ ረብ ያለው እሴት፣ “ሕያው እምነት” ኾነን መገኘት ነው።
እሴቶቻችንን በተግባር መተርጎም ማለት የሰውነታችንን ትርጉሙን፣ የሰውነት ብያኔዉን፣ የልባችንን ልኩን፣ የተልዕኳችንን ጽድቁን ማግኘት ማለት ነው።
እንደ አባወራነታችን ለትውልድ የምናቀብለው “ሕያው እምነት” ቅድስናን፣ ራስነትንና ኃላፊነትን እንደ ጌጥ መለጠፍ በእነርሱም መለጠጥ ሳይኾን፣ እንደ እስትንፋሳችን አብሮን እንዲኖር ማድረግ ትልቁ ተግባር ነው።
ትውልዱ የራሱን እሴት ሲንቅና የሌላውን ሲመኝ፣ ራሱን አጥቶ፣ ማንነቱ ጠፍቶ፣ ባዳን ተጠግቶ፣ የሌላው ጥላ፣ ተከታይና ባርያ ኾኖ ይጠፋል።
ስለዚህ የአባቶቻችንን እምነት በልባችን አኑረን፣ በዘመናችን ዐውድ ውስጥ በተግባር ስንገልጠው፣ ትውፊቱ በእውነት “ሕያው” ይኾናል።
ይህ ሲኾን ነው አባወራነት፦አባትነት፣ ባልነት፣ ወንድነትና ራስነት፤ ከተራ ስምነት፣ ከመጠሪያ ቅጽልነት፣ ከጉራ መቸርቸሪያነት ወጥቶ ወደ ሕያው ተግባርነት የሚለወጠው የሚገለጠውም።
ትውልዱ እሴቱን አውቆ ሲኖርበት፣ ጥፋትና ሞቱን ወደ ጽድቅና ሕይወቱ ይቀይራል፤ በዚያም ወደ ተፈጠረለት ልዕልና ከፍታም ይሻገራል!
ይህ አባወራዊ መንገድ ነው! ዛሬ ያሉት ሊቃውንት በዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ስም ወደ እንከፍ ምስኪንነት፣ ስልብ ጃንደርባነት፣ ፍዝ አልጫነት ሊቀይሩብን ከጠላት ጋር የሚዶልቱት!
አባቶቻችን ከኖሩበት፣ አያት ቅድማያቶቻችን ከሚታወቁበት ትውፊት፣ እሴት የተለየ መንገድ ሲነግሯችሁ ተጠንቀቁ!
“ወንድነት ምስኪንነት ነው፣ ባልነት መስዕዋትነት ነው፣ መሪነት አገልጋይነት ነው…” የሚል ትርክት በየመገናኛ ብዙኃኑ፣ በዩቲዩብና መድረኩ በአስመሳይ አድርባዮች ሲቀጣጠል ጠርጥሩ!
ይህንን የሚነግሯችሁ እነርሱ ማንም ቢኾኑ በተለይ ደግሞ በኑሮ ያይደለ፣ በንባብ የደለበ፣ በፈተና ያልለዘበ ሕይወት አልባ ደረቅ እውቀት የተሸከሙ ሲኾኑ፤
ለምን?
እነርሱ ሸፍጣቸውን ከታሪክም ከቅዱሳት መጻሕፍትም ምሳሌንና ኃይለቃልን እየመዘዙ፣ ንግግራቸውን እያጣፈጡ፣ እውነቱን ከሐሰቱ የሚያምታቱበት፣ የሚያጠናክሩበት፤ ለሕይወት የማይገልጡት፣ ለጥፋት ያሰለፉት እውቀቱ አላቸውና! ለመሃይሙ ይህ አይቻለውም!
የትውልዳችንን ልብ ከአስመሳይ አድርባይነት፣ ከእናት ጡት ነካሽ ባንዳነት፣ ከስልብ ጃንደርባነት፣ ከ”ሙክት” ወኔቢስነት፣ ከቅልብ ሆዳደርነት ለይተን ወደ አባወራነቱ ልዕልና(Excellence) እናነሳዋለን!
ይህ በትውልዱ ዘንድ የተናፈቀው፣ የሚናፈቀው፣ የሚጠበቀው ባለ ግርማ ሞገሱ አባት የአባወራውም ድምጽ ነው! ተራ ጩኸት አይደለም፤ ነገር ግን ልጆቹን፣ ትውልዱን ከተጫነባቸው አዚም የሚለይ የትንሳኤው ንዝረት እንጂ!💪
0 Comments