ከ”ምሁራን” ይልቅ ልባም ልጆችን እናፍራ!

ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

ኢትዮጵያን የቸገራት “የተማረ” ሰው አይደለም፤ “ልባም” ሰው እንጂ። ሀገራችን ማስትሬትና ዶክትሬት የጫኑ፣ በቤተ-ክህነቱም በኩል “ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት” የሚል ማዕረግ የተጎናጸፉ ሰዎች አልጎደሏትም። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ማዕረጎችና ድግሪዎች ሀገርን ከመፍረስ፣ ትውልድን ከመክሸፍና እሴትን ከመሸጥ ሊታደጓቸው አልቻሉ።

ለሀገራችን ውድቀትና ለትውልዱ መላላት፣ መሳሳት፣ መቅለጥና መሟሟት ዋና ተዋናዮቹ እነዚህ ባፍጢማቸው የተደፉ፣ ሆዳደርና አስመሳይ ሊቃውንት ናቸው። እነዚህ “አዋቂ” ነን ባዮች የያዙትን እውቀት ለጽድቅ ሳይሆን ለሆዳቸው፣ ለሃቅ ሳይኾን ለጥቅማቸው ገብረዋል።

በሕዝብ ፊት “ፍቅርና መንፈሳዊነት” ይሰብካሉ፤ በጓዳ ግን ለጠላት ትውልዱን ለመሸጥ ይስማማሉ፣ ነጣቂ ተኩላ በጎቹን የሚነጥቅበትን በር ይከፍታሉ።

የትውልዱን ማንነት የሚሰልቡ የምዕራባውያን ፖሊሲዎች (እንደ SRHR) በቤተ-ክርስቲያንና በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ጥቂቶቹ እንዲሰርግ ሲሠሩ፣ ብዙኃኑ ግን ብንነግራቸውም ጥቅማቸውን ላለማጣት ሲሉ ዝምታን መርጠዋል!

አባቶቻችን በደምና በአጥንት ያቆዩትን እነ ሆሜርና ሄሮደተስስ እስኪመሰክሩበት፣ እንግሊዛውያን ራሳቸው እስኪቀኑበት ድረስ ድንቅና ጠንካራ ስብዕና ያለው ትውልድን ያነጸ አባወራዊ ሥርዓት፣ አርበኝነትና ወንድነትን በ”ዘመናዊነት” ስም እንዲጠፋ ከጠላት ጋር በመርዙ መክረዋል፣ በሸፍጡ ሠልጥነዋል፣ ለጥፋቱም ተሰማርተዋል!

ሀገሬን የቸገራት በእውነት ለጽድቅ የጨከኑ፣ በመልካምና ጠንካራ ስብዕና የታነጹ፣ ፍትሕን የሚያሰፍኑ ልባምና ልበ-ሙሉ ሰዎች እንጂ በፊደል የተካኑ “እንከፎች”፣ በደረሱበት “እውቀት” “ሠርቆ አደሮች” መኾናቸውን የሚጠቁሙን ሆዳደሮች አይደሉም!

በራስ ላይ፦ በስሜት ላይ፣ በፍላጎት ላይ፣ በሃሳብ ላይ፣ በብልት ላይ ሳይሠለጥኑ፤ ነገር ግን ማስትሬትና ዶክትሬት ጭነው፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ተብለው የሚንጎማለሉት፣ ትውልዱን ይመሩ ዘንድ ከላይ የሚወጡት፦ እነርሱ በልተው፣ ጠጥተው፣ ጠግበው፣ ደግሞ በጎተራ ከምረው ላይበሉት ስለሚያበሰብሱት ያሳስባቸዋል እንጂ ችግረኛው ትውልድ ትዝም አይላቸው።

ሆዳደርነታቸው መዝኖ በሆዳቸው ባፍጢም የተደፉ እነዚህ ምሁራን በትውልዱ ላይ እንዲህ ሲነግዱ እንኳ ጨርሶ በሚጠፋበትና በሚመክንበት ጽንሰሃሳብ መኾኑ ለጠላት ያደሩ፣ በምንዳ የተቀጠሩ ባንዳ መኾናቸውን ይገልጣል።

መማር ማለት ማንነት፦ እናትና አባትን፣ እህትና ወንድምን፣ እሴትና እምነትን እውነትንም መሸጥ ከኾነ፣ ማወቅ ማለት ጠላታችንን ወደ ቤታችን ጓዳ መንገድ ማሳየት ከኾነ፣ እንዲህ ዓይነቱ “ሊቅነት” ከድንቁርና የከፋ አጥፊ ነው።

ዛሬ የምናያቸው አብዛኞቹ ሊቃውንት የትውልዱን ወኔ፣ በተለይም ጽድቅ የሚሠራበትን የወንዱን ወንድነት መክሊቱን “በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት” ስም ሰልበው “አልጫ” አድርገውታል።

ወንዱን በተለይም አባወራውን ለእምነቱ፣ ለእውነቱ፣ ለእሴቱ አርበኛ ከማድረግ ይልቅ ምስኪንና አልጬ፣ ቅልጥ ያለ ታይታና ይኹንታ የሚፈልግ ቅብጥብጥ ቀላጭም አድርገው ለባርነት ገርተውታል።

ይህ በአስመሳይነት ተለምዶ፣ በአድርባይነት ተገምዶ በሆዳደርነት ተዋዶ እናት ሀገርን፣ እናት ቤተክርስትያንን እውነትንም ከከዳ ባንዳነት የመነጨ ደባ፣ ትውልዱን ልብአልባ አድርጎታል።

ወንድምዓለም! እውነተኛ ልባምነት በራስ ላይ ሠልጥኖ ወደ አባወራነት ልዕልና በመውጣት ይጀምራል። አባወራነት ደግሞ በራስ ላይ ሠልጥኖ፣ ለራስ ደርሶ፣ ከራስ አልፎ ለቤተሰብ፣ ለሃይማኖትና ለሀገር መቆርቆርና መከላከል ነው።

ልባምነቱን በልበሙሉነት ተጠቅሞ ጽድቁን ሊሠራበት ላለው፦ክፋቱን ክፋት፣ ሸፍጡን ሸፍጥ ለማለት፤ በዚያም መልካሙን፣ ልኩን፣ ተገቢዉን፣ ውቡን ለመፈጸም የጨከነ ነው።

ልጆቻችን ድግሪ ብቻ የጫኑ ሳይኾኑ፣ ለወገን የሚራሩ፣ ለጠላት የማይንበረከኩ፣ ለእሴታቸው የሚቆረቆሩና የቤተሰባቸው፣ የማኅበረሰባቸው ጠባቂ (አባወራ) እንዲኾኑ በቅተን አብቅተን፣ አሳይተንም ልናሳድጋቸው ይገባል።


Post a Comment

0 Comments