አባ አባወራው ተነስ ለማንስ ተውከን?




ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

የሴቶቻችን ጩኸት፣ ለቅሶ ምሬታቸው ለአስመሳይ አድርባዩ እንጀራ ለሚነግድባቸው አታላዩም ግብር የማይከፍልበት ንግድ ነው!

“አባ... አባወራው ተነስ? ለማንስ አሳልፈህ ተውከን?

እነሆ ዛሬ በስማችን የሚነግዱ፣ በለቅሶአችን የሚከብሩ፣ በቁስላችን ላይ ‘ዶላር’ የሚቆጥሩ አታላዮች ተረከቡን።

አንተ የቤትህን ቅጥር ጥለህ ስትተኛ፣ እኛ የሆዳደሮች ሲሳይ ኾንን። በየመድረኩና በየሆቴሉ አዳራሽ በስማችን ‘ሲምፖዚየም’ ይቆማል፤ የኛ ስቃይ ግን የእነርሱ የዕለት እንጀራ መኾኑ ይገርማል!

‘ጾታዊ ጥቃት’ እያሉ ይጮኻሉ፤ ነገር ግን ጥቃቱን የሚመክት ወንድነትን ከማነጽ ይልቅ ባንተ ላይ እንድንቆጣ የሚያደርግ መርዝ ይግቱናል። ጥቃቱ ሲበዛ ለጌቶቻቸው የሚላከው ሪፖርታቸው ይሞላል፤ እኛ ስንሰበር የእነርሱ የገንዘብ ካዝና ሞልቶ ይፈሳል።

🌟 አባ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚነግድብን በዝቷል! ተነስ እንጂ ትውልድን ትተህ ትተኛ ዘንድ ማን አዚም አድርጎብሃል?

🚨 “እኩልነት፣ መብትና ነፃነት” እያሉ በጆሯችን ይጮኻሉ፤ ነገር ግን ነፃ ያወጡን ከመከራ ሳይኾን ከምንከበርበት ከትዳራችን፣ ከቤታችንና ካንተ ጥበቃ ነው።

🚨 “መብታችሁ ነው” ያሉን የገዛ ልጆቻችንን፣ ንጹሐኑን ሕጻናት በመርዝ በጣጥሰን በመቀስ ቆራርጠን የምናጠፋበትን እርኩሰትን ነው፤

🚨 “ነፃነታችሁ ነው” ያሉን ልጅ አልባ፣ ዘር አልባ፣ ትውልድ አልባ ኾነን የደረቅንበትን የትም፣ ከማንም፣ ለማንም እግራችንን አንስተን ነገር ብቻችንን የቀረንበትን ባዶነትን ነው።

🚨 አንተን ከመስማት፣ ባንተ የፍቅር ጥላ ስር ከማረጽም አውጥተው፤ እንዳንታዘዝህ አደረጉንና ለባዕድ አጀንዳ አገልጋይና አጎብዳጅ አደረጉን።

🚨 “የሥነ-ተዋልዶ ጤናና መብት” (SRHR) እያሉ ማኅፀናችንን ይበረብራሉ። “ጤናችሁ ነው” እያሉ ጽንሳችንን እንድንገድል፣ በነፃነት ስም ዘራችንን እንድናመክን፣ ተፈጥሮአችንን እንድንጠላ መከሩን።

በስማችን የሚሸጡት “መድኃኒት” ሳይኾን የትውልድ ማጥፊያ መርዝ ነው! እነርሱ በሰጡን “መብት” እኛ ስንጠፋ ስንመክን፣ እነርሱ ግን በሚሊዮን የሚቆጠር ትርፍ ያፍሳሉ።

🌟 አባ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚነግድብን በዝቷል! ተነስ እንጂ ትውልድን ትተህ ትተኛ ዘንድ ማን አዚም አድርጎብሃል?

እነዚህ አስመሳይ አድርባዮች በችግራችን ተጠቅመው ግብር የማይከፍሉበት የንግድ ሱቅ በ”ግብረሰናይ” ስም ከፈቱብን። እኛ በየጎዳናው ስንደፈር፣ እኛ በትዳር አልባነት ስንማቅቅ፣ እኛ ለልጆቻችን አባት ነፍገናቸው ሲሳቀቁ፤ እነርሱ “የሴቶች መብት ተሟጋች” ተብለው ይቆለጳጰሳሉ። የእኛ ለቅሶ፣ የእኛ መደፈር፣ የእኛ መታፈን፣ የልጆቻችንም ያለ አባት መንከራተት ለእነርሱ የሥራ ስኬት ማረጋገጫ፣ የሹመት መወጣጫ ኾነላቸው።

🌟 አባ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሚነግድብን፣ በስማችን “የዶላር ሱቅ” የሚከፍትብን፣ የሚከብርብንም በዝቷልና ተነስ፣ ለማን ተውከን?

👉 ለእነዚህ ሆዳደር ሊቃውንት?

👉 ለነዚህ የባዕድ ርዕዮተ-ዓለም ተላላኪዎች?

👉 ትውልዱን ለሚያመክኑት ከንቱዎች?

👉 እኮ ለማን?

ተነስ እንጂ! አባትነትህን፣ ባልነትህን፣ ወንድነትህን፣ ራስነትህን ናፍቀናል! ካንተ ጥላ ሥር ወጥተን የጠላት መጫወቻ ኾነናል! ከእቅፍህ ርቀን በዓይነትና በብዛት ለመጡ ሆዳደር ነጋዴዎች ሲሳይ ኾነናልና፤ ተነስ!

💪 ተነስና አብነት እንደኾነህ አባትህ፣ ምራሌ እንደሰጠህ መምህርህ ጅራፍን ግመድ!

እነዚህን በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ስም የሚነግዱብንን ነጋዴዎች ከቤታችን አስወጣቸው! በስማችን የሚነገደውን ሸፍጥ በአባቶችህ ግርማ፣ በአባትህም ድምፅ ገስጸው!

እኛ እኮ! ካንተ ሰው ከምንኾንበት፣ በሰውነት ከምናብብ ከምናፈራበት ጽድቅ ይልቅ የእነርሱን አሳሳች ስብከት እንድንሰማ የተገደድነው አንተ ተኝተህ ስለተገኘህ ነው።

🌟 አሁን ግን እኛም ነቅተናል፤ ሕመማችንን አውቀነዋል፣ ከነጋዴዎቻችንም ሱቅ ጠፍተናል፤ ነገር ግን ከጠላትና ቅጥረኛ ሆዳደሮቹ የሚጠብቀን፣ በእውነት፣ እምነትና እሴቱ ወደ ጽድቁ የሚመራንን አባወራዊ የአንባ-ግርማህን፣ ግሳት-ድምጽህን ናፍቀናልና ተነስ!

ጠላትም ግርማህን ዐይቶ ይደንግጥ፣ ነጋዴ ሆዳደሮችም ይረበሹ፣ እኛም፦ እናት፣ እህት፣ ሚስት፣ ልጆችህ የሰላምን ዐየር እንተንፍስ!

💪 አንተ የተኛህ አባወራ ሆይ ተነስ!


Post a Comment

0 Comments