እሴቱን እንዲጠላ በመንፈሳዊነት ስም ለተሰለበው


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

የቆመበትን እሴት-መሠረት፣ መራጃ ሰጥተውት እንዲያፈርስ፤ መች ይገኛል በቦታው፣ በራስ ጠልነት ልቡ የጠፋው! ጀግንነትና ክብሩን “ባልጫ ክርስትና”፣ አርበኛ አባወራነቱን በጃንደርብነት ለባርነት ላጨው ትውልዴ!

ታሪክን በደማቸው የጻፉ፣ ድንበርን በአጥንታቸው ያጠሩ፣ ክብራቸውን በደረት አቅፈው ለነፃነትና ለጽድቅ የቆሙ(የተዋደቁ)፣ እንደዛሬው የእናት ጡት ነካሹ “ሊቅ” በሆዳደርነት ባፍጢም በመደፋት የማይታሙ አባቶች በነበሩባት ምድር፤

ዛሬ “መንፈሳዊነት” የሚል ካባ የደረበ፣ ነገር ግን ውስጡ ራስን፣ ታሪክን፣ እሴትን፣ ተፈጥሮን በተለይም ወንድነትን፣ ጀግንነትን፣ ክብርን እንዲጠላ የተሰለበ ትውልድ በቅሏል።

ይህ ትውልድ ጀግንነትን እንደ እብሪት፣ ራሱን ማስከበርን ደግሞ እንደ ትዕቢት፣ ልባምነቱን ደግሞ እንደ ኃጢያት እንዲቆጥር፤ ይህንን የመሰለውን የአባቶቹንም ፈለግ ኮንኖ እንዲርቅ ባልጮቹ “ሊቃውንት” ትምህርት ተደልሏል።

“ሀገሩ በሰማይ” የኾነው ይህ የስልብ እንከፎች፣ የምስኪን አልጮች ስብስብ “እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ሊል የሚችልበት ምንም ዓይነት አግባብ፣ አባቶቹን የተከተለበት ፈለግ፣ እነርሱንም የሚመስልበት ወግ በጭራሽ የለውም!

እንኳን ወረቀቱና ብራናው፣ የሀገራችን ሳርና ቅጠሏ፣ ተራራውና ወንዟ ይቅርና የውጪ ሃገራት ሳይቀሩ ጀግንነት ኩሩነታቸውን፣ የጠንካራ ስብዕና ባለቤት የ”አማልክት” ወዳጅነታቸውን የሚያውቁላቸው የሚመሰክሩላቸው አባቶቻችን እንደ ዛሬው በአስመሳይነትና በአድርባይነት ባፍጢም ተደፍተን በወኔቢስ ጥላቢስም ኾነን ከመታወቃችን በፊት ባለግርማ ነበሩ፤ ነበርንም።

ለእነሱ ክርስትና ለሐቅ መቆም፣ ለጽድቅ መጋደልና ለሀገር መከታ መኾን ይህም ልክና ተገቢ ክብርም ነበር። ዛሬ ግን ይህንን የትውልድ “አውራነት” ሰልበው፣ ትውልዱን ወኔቢስ ጃንደርባ የሚያደርግ ያባቶቻችን ትውፊት ያይደለ የባርነት “ክርስትና” ተጋብቶበታል።

“ቀኝህን ሲመቱህ ግራህን ስጥ” የሚለው መለኮታዊ ትምህርት፣ ከግል ይቅርታ አልፎ እንደ ማኅበረሰብ ራስን ለመከላከልና ለክብር ለመቆም እንደ ድክመት ተተርጉሞ ለባርነት ታጭቶበታል።

ወንድምዓለም! ዛሬ ዛሬ ጠላት ከውጭ መጥቶ ቤትህን አያፈርስም፤ ይልቁንም አንተ “አይነኬ፣ አይወቀሴ፣ አይከሰሴ” ያደረግካቸውን፣ ከእውነት ይልቅ ያስበለጥካቸውን፣ ባታስተውለው እንጂ ጣዖት ኾነውብህ የምታመልካቸውን ሆዳደር ሊቃውንትና ተቋማት ይልካቸዋል እንጂ።

እነርሱም በአጉል መንፈሳዊነት የልቦናህን ዓይን አሳውረው፣ “እውቀት” ብለው በሚግቱህም እብሪት አሳብጠው፣ የአባቶችህን ትውፊት እንድትጠላና እንድትጥል አሳምነው፤ በዚያም አንተኑ መራጃ አስጨብጠው የቆምክበት መሠረትህን፣ የመጣህበት ታሪክህን እንድታፈርስ ያደርጉሃል እንጂ።

ጃንደርባነት ዘር መተካትና ራሱን መከላከል የማይችል፣ ለጌቶቹ ምቾት ብቻ የሚታዘዝ ስልብ ማንነት ነው። ዛሬም ትውልዱ የሞራል ጀግንነቱን ተነጥቆ “ለጃንደርባነት” ታጭቷል።

ክብሩ ሲገፈፍ “ትሑት ነኝ፣ መንፈሳዊ ነኝ፣ ሀገሬ በሰማይ ነው” በሚል በአስመሳይ አድርባይ ሊቃውንት ኾን ተብሎ በተጋተው ሰበብ ራሱን ይደበቃል፤ ለሐቁ መጮኽ ሲገባው በ”ሆዳደርነት” ዝምታን ይመርጣል፤ የታሪክ መዝገብ ላይ “አርበኛ-አባወራ” ኾኖ መገኘት ሲገባው፣ እርሱ ግን ጸድቆለት በተሰጠው የቅኝ ግዛት መንፈስ ተለክፎ ከቦታው ይጠፋል ይመክናልም።

ይህ የባህል አብዮት ጥሪ ነው!

የጃንደርባነትን ሰንሰለት ሰባብሮ፣ ያንን የቆየውን የጀግንነትና የኃላፊነት መንፈስ መልሶ የመትከል ዘመቻ ነው! ትውልዱ “መልካም” የኾነውን እሴቱን ጥሎ፣ በ”ሆዳደርነት፣ በራስወዳድነት” ጠፍቷልና ሊነቃ ይገባል።

“ያልጮች ክርስትና” የሚሰብከው እውነትን፣ ክርስቶስን ሳይኾን በመንፈሳዊነት ስም እሴትን አስጥሎ፣ ራስን አስጠልቶ፣ ልባልባ የሚያደርገውን ሐሰትን ነው።

ትውልዱ ከዚህ አልጫነት እስካልወጣ ድረስ ጃንደርባ የታሪክ ቅሪት እንጂ አባወራ የታሪክ ባለቤት ሊኾን አይችልም።

ከጃንደርባነት መንፈስ ተመለስ! ያንተ አባቶች በዓለም መድረክ የተፈሩ፣ ባለ ግርማ የጀግንነት ልክ ነበሩ። ዛሬ መንፈሳዊነትን ካባ አድርገህ እሴትህን፦ ጀግንነት ክብርህ፤ አታፍርስ!

ልባምነት፣ ጀግንነት የእምነትህ ፍሬ እንጂ የኃጢአት ምልክት አይደለም! ቆመህ ታሪክህን እንደ ወረቀትና ብራና አትተርክ፤ ታሪክህን ኾነህ፣ እሴትህን ለብሰህ ተገኝ!

አለበለዚያ ሆዳደሩ ሊቃውንት እንደተቀጠረብህ ልባልባ አልጫ ኾነህ፣ በጃንደርብነት ለባርነት ተላልፈህ የምትሰጥ አባቶችህን ፍጹም የማትመስል የትውልድ ማፈሪያ አልጫ (Demoralized ) ትኾናለህ!

Post a Comment

0 Comments