✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ልንሠለጥንበት፣ ልናበለጽገውና ጽድቁን ልንፈጽምበት ባለን ጸጋ ሳናተርፍበት እናተርፍበት ዘንድ ሳንፈልግም ስንቀር፤ ያተረፈበት ግን ሲኖር ከመማር ከመታረም ይልቅ ኮንኖ መቅበር ያይልብናል!
ከዚህ በፊት፦
“እነዚያ ከእርሱ በተቃራኒ የሚኖሩት ሰዎች በተለይም ወንዶቹ ይበልጡንም አባወራዎቹ እርሱ ባልሠለጠነባቸው ሁሉ በልጠውት “እስኪያሳጡት”
(ሊያሳጡት ፈልገው ግን አይደለም) ይቆማሉና ይርቃቸዋል” ብዬ ነበር።
ለምን?
1 በፍላጎትና ስሜቱ፦ ታይታና ይኹንታ መፈለጉ፣ አድናቆትና ጭብጨባ መሻቱ፣ ተከታይና አድናቂ መውደዱ፣ ገንዘብና ሆዱ ላይ ያለመጨከኑ፤ በእነርሱ መረታቱ፤ አባወራውን ግን እነዚህን አለመሻቱ፤
2 ሥርዓትና ምግባሩ፦ ለሚሠራውና ለሚናገረው ሥርዓት ማጣቱ ፦ባለጌ አይደለም፤ ነገር ግን በጊዜ፣ በቦታ፣ በመጠን የታወቀ የተገለጠ፣ የተረዳ ሥርዓት አለመያዙ፣ አለመቻሉ ይህንንሜ በሰበብ አስባብ ማጠሩ፤ አባወራው ግን በሥርዓት መገለጡ፤
5.3 አቋምና አቅሙ፦ የተናገረውን ቃል አለመጠበቁ፣ ላልጠበቀው ቃል ሰበብ መደርደሩ፤ ሊፈጽመው ላለው ጽድቁ አቅመቢስ ወኔቢስ መኾኑ ...፤ አባወራው ግን በቃሉ መገኘቱ፣ አቅሙን መገንባቱ፤
5.4 አስመሳይና አድርባይነቱ፦ ከላይ የዘረዘርናቸው ስንፍናና ሰበበኛነቱ እያሉበት እነርሱን አምኖና ተቀብሎ በራሱም ላይ ሠልጥኖ ወደ ወንድነት ልኩ ወደ አባወራነቱም ቁና ከመምጣት ይልቅ በቀላሉና በፍጥነት “ዘመናዊ መንፈሳዊ” ለመምሰል ወደ አስመሳይ አድርባይነቱ መገልበጡ፤ አባወራው ግን “ለመምሰል፣ ተቀባይነት ለማግኘት” አለመኖሩ፤
ስለኾነም ጡንቻውን፣ ወኔውን፣ ድፍረቱን፣ ኃይለኝነቱን፣ ጉልበቱን፣ ጥንካሬውን፣ ቁጡነቱን፣ እልኩን፣ ሥነ-ሥርዓቱን እና የመሳሰሉትን ሁሉ እርሱ “ደርሼበታለሁ” በሚላቸው “ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት” አሳቦ፣ ኮንኖ ይጠየፋቸዋል፣ ተጠይፎ ይጥላቸዋል፣ ጥሎም ይቀብራቸዋል።
እነዚህን ተከትሎ እንከፍ ምስኪኑ፣ ስልብ ወኔቢሱ፣ ምስኪን ጃንደርባው፣ አባወራውን ብቻ አይደለም፤ የእርሱን የትኛውንም ከሥልጣኔው የተነሳ የደረሰባቸውን ልዕልናዎች(his exellence) ሁሉ ይጠየፋል።
እነርሱን ይጠየፋልና ይኮንናቸዋል፣ ይኮንናቸዋልና አባወራውንም ይኮንናል፣ ይኮንነዋልና በትውልዱ መካከል ትውፊቱን ተቀባይ፣ እሴቱን አቀጣጣይ፣ ፈለጉን ተከታይ፣ እንዳይኖር ዳናውን ለማጥፋት ይተጋል።
የጠቆረ ፊቱን፣ የቀላ ዐይኑን፣ የከፋ ሥራውን ግን የሰማ ያየው ሁሉ እንዲቀበለውና እንዲተባበረው በተለመደው በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም አሳቦ ይፈጽመዋል።
“ለምን?” ቢሉ፤
እርሱ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ካባ ተከታይና አድናቂ ባፈራበት፣ ያድናቆትም ካባ ላንቃ በደረቡለት ማኅበረሰቡ መካከል ያሳጣዋልና፤
በተለይ ግን ይበልጡንም ደግሞ ውዳሴና፣ ታይታ ይኹንታንም አጥብቆ ከሚፈልግባቸው ሴቶች፣ ካገባም በሚስቱ ፊት ያሳጣዋልና፤ እጅግ ይጠላዋል፣ ይኮንነዋል፣ ያወግዘዋልም!
ስለኾነም ወንዱ በዐዲሱ የዘመናዊነትና የመንፈሳዊነት ትርክት ወዶና ፈቅዶ ተፈጥሮአዊ፣ ትውፊታዊ ወንድነቱን በተለይም አባወራነቱን ጥሎ ጃንደርብነትን አንጠልጥሎ በእንከፍ ምስኪንነት እንዲገኝ፣ በአስመሳይ አድርባይነቱ እንዲናኝ፤ ይህ ሰሞኑን የምታዩት “ወንድነት፣ ባልነት” በስፋትና በድግግሞሽ ይሠራጫል።
💪 ለአባወራዊው ወንድነት (Patriarchal Masculinity)፣
💪 ለአርበኛዊው ዜግነት፣
💪 ለአባታዊው ልጅነት፦ የሚወለድበት፣ ድምጹም የሚሰማበት፣ ድክ ድክ ብሎም የሚያድግበትም ስፍራ አይገኝለትም አይሰጠውምም፤ የትም እንዲሳደድ ይኾናል።
ጃንደርባነት ድሮ ለቤተ-መንግሥት አገልግሎትና ለታማኝነት ተብሎ በአካል ላይ እንደሚፈጸም ግፍ እንደኾነው ሁሉ፤
ዛሬ ደግሞ ወንዱ ለዘመናዊው ሥርዓት፣ በተለይም ኢፍትሐዊነትና ግፍ ለሠለጠነባት ዓለም ታዛዥና አገልጋይ አጎብዳጅም እንዲኾን ሲባል ወኔው ይሰለባል።
አንድም በእሴት የተገነባው ልቡ፣ በተገነባው ልቡም የታነጸው ጠንካራ ስብዕናው፤ አባቱ ለፈጠረው ጽድቁ እንዳይቆም እንዳይኖር በረቀቀ መንገድ በተለይ ወንድነቱ ይኮላሻል።
የዐለም ሥርዓት የሚፈልገው የማይጠይቅ፣ ኢፍትሐዊነትን የማይቃወም፣ ለታዘዘው ሁሉ “እሺ” የሚል፣ ለጽድቅ የማይጨክን ስብስብ በመኾኑ፣ ድፍረት ጥንካሬውንና ሥልጣኔውን ነጥቆ እንከፍ ምስኪን ይኾን ዘንድ በየመገናኛ ብዙሃኑና በየማትገጹ እንዲያ የሚያደርጉት ጠባያት ይሰበኩለታል።
ጠላት፣ የምዕራባውያን ርዕዮተ-ዓለም አራማጆች እና ለጥቅማቸው ያደሩ የእኛው ሆዳደር ሊቃውንት የትውልዱን እሴት፣ ትውፊትና እምነት ለመለወጥ ሲፈልጉ አስቀድመው የሚመቱት ይህንን የማኅበረሰቡን፣ የቤተሰቡን እውነት፣ እምነትና እሴቱን ጠባቂ ወንዱን ነው።
ከጠባቂነቱ የተነሳ ሊቃወማቸውና የባዕድ እሴትን ሊገታ የሚችለውን ወንድ ወኔውን፣ ድፍረቱንና እልሁን ይሰልቡታል። ከዚህ በፊት እንደጠቀስነው ከሚኖርበት ከባቢ አውጥተው ለማዳ የሰርከስ አሻንጉሊት እንዳደረጉት አንበሳ፤
ወንዱንም በሚስቱ፣ በልጆቹ፣ በቤተሰቡ፣ ሲመጡበትና እነርሱን ሲነጥቁትም ምንም የማይቆጣ ፍዝ፣ ድንዝዝ፣ ስልብ፣ ሙክት፣ ድልብ፣ ወኔቢስ ይኾን ዘንድ እነዚህኑ መንፈሳዊነት ሲሉ ጃንደርባነትንም እያጸደቁ ይግቱታል፤ እርሱም ሲቀበላቸው እንደዚያው ይኾናል!
በባሕርይው ጃንደርባ ሲኾን፣ ለጠላት ወረራና ለባህል መበረዝ የተመቸ፣ ከመጣው ጋር ተስማምቶ ለመኖር የተመቻቸ፣ ከንግሥና ይልቅ ለባርነት ራሱን ያመቻቸ፣ ለማደግደግና ለመታዘዝም ያልሰለቸ ይኾናል።
ይህ (ጽሑፉ) ያላተረፈበትን ነገር ግን ጽድቅ ይሠራበት ዘንድ የተቀመጠለትን፣ ሰውነት ተፈጥሮውን በተለይም ወንድነት መክሊቱን ከአባቱ በላይ “አዋቂ” ኾኖ በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም በታጀረበት እብሪቱ እንከፍ፣ ምስኪን ጃንደርባም ኾኖ ባፍጢም ለተደፋው ታሪኩ ነው!
አንተ የቱ ጋር ነህ?
ፊትህ ይጠቁራል፣ ዐይንህ ደም ይለብሳል፤ ከዚያም መክሊትህን ቀብረህ ያተረፈበትን ትኮንናለህ፤ ወይንስ “ለእርሱ ከተቻለው፣ ለእኔም ይቻላል” ብለህ ወደ ተጠራህለት ልዕልናህ ትዘረጋለህ?
0 Comments