አባታችን በዳይ ሥርዓቱም ጨቋኝ አይደለም!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር   

በወንድነት ላይ በተለይም በአባወራው ላይ ይበልጡንም በአባታችን ላይ ትውልዱን በእኩልነት፣ መብትና ነፃነት ስም የሚያሳምጸው በወዳጅ መልክ የተገለጠ ጠላት ነው!

የሀገር መሠረቱ ቤተሰብ የሚቆመው ጠንካራ ስብዕና ባለው አባት ላይ ነው። አባት የቤተሰብ ምሰሶ፣ የባህል ጠባቂ፣ የእሴት መመሪያና የእምነት አርአያ ነው።

ምንም እንኳ ቤተሰብ የእርሱና የሚስቱ አንድነት፣ ውሕደትና ውልደት ውጤት ቢሆንም፣ ጠንካራ አባት ለጠንካራ ቤተሰብ ግንባታ ምሰሶው ነው።

ይህ አባት የፍቅርና የነፃነት ምንጭ ቢኾንም እነዚህ በገደብ የሚፈሱበትን የሥርዓትን ጅረት የሠራ ነው። ትውልዱ ድኅነታቸው ከሚፈጸምበት ከዚህ የሥርዓት ጅረት ወጥተው ሲንሸራተቱ የሚጠብቃቸው የአባታቸውን እቅፍ ሳይሆን፤ የጠላታቸው ያፈጠጠ ዓይን፣ ያገጠጠ ጥርስና የዘረዘረ ጥፍር ነው። አባት “አይኾንም” የሚለው ልጁን ጠልቶ ሳይኾን፣ ከአጥር ወዲያ ያለው ተኩላ እንዳይበላው ሊጠብቀው ወዶ ነው።

እርሱ አባታችን በሌለበት፦ አልጫው በበዛበት፣ ምስኪኑ በሞላበት፣ ቀላጩ በቀበጠበት፣ ሆዳደሩ በፋነነበት፣ አስመሳዩ በገነነበት፣ አድርባዩ በሚርመሰመስበት ማኅበረሰብ ትውልዱ በቁጥር እየሳሳ፣ በስብዕናው(character) እየከሳ፣ ማንነቱን እየረሳ ይመጣል።

አባትነት በእውነት ላይ ተተክሎ፣ በጸጋው ላይ ሠልጥኖ ወደ ጽድቁ በመዘርጋት፤ ለትውልዱ መውረጃ በቅጡ መፍሰሻ፦ ፈለግ ሥርዓቱን፣ ዳና ምልክቱን፣ ፋና ብርሃኑን የሚሰጥ የሚተው ኃላፊነት ነው።

አባት ለሴት ልጁ ጠበቃ፣ መከታ፣ ጋሻ፣ አለኝታ፣ ይኹንታ ሲኾን እርሷ የዐለሙ ድምቀት፣ ውበት ኾና እርሱን ከሚመስለው አባወራ ጋር ተጣብቃ ትኖር ዘንድ በሥነ-ምግባሩ መሥርቶ፣ ሴትነቷን አጉልቶ ይሞሽራታል።

ወንዱ ፈለጉን ተከታይ ነው! ሳይናገረውና ሳይነግረው ልጁ ዳናውን እየረገጠ የሚመስለው። ስለኾነም አባት የሚረግጥውን መሬት፣ የሚደርስበትን ምዕራፍ ልጄ “ያየኛል፣ ይሰማኛል” ሳይል መጠንቀቅ አለበት።

ጠላት ግን ትውልዱን በባርነት መንዳት ይፈልጋልና እርሱን የሚኮንን ትርክት በመብትና ነፃነት ስም በወጣቱ በተለይም በሴቶቹ መካከል ይረጫል።

አባት ማለት ራሱን ለቤተሰቡ መሠረት አድርጎ የሰዋ “ሕያው መሥዋዕት” ነው። ከፀሐይ ግለትና ከነፋስ ቁር ልጆቹን ለመጠበቅ ደረቱን ጋሻ የሚያደርግ፣ የራሱን ፍላጎት ሸፍኖ የልጆቹን ሕይወት የሚያለመልም ታላቅ ባለቤት ነው።

አባት ሀገርን የሚያቅናው መጀመሪያ በቤቱ ውስጥ ሥርዓትን በማጽናትና ትውልድን በምግባር በማነጽ ነው። አባት ሀገሩን የሚመራው መጀመሪያ ሚስቱን ሲቀጥልም ልጆቹን ወደ አንድ ዓላማ ምዕራፍም መምራት ሲችል ነው።

ጠላት አባትነትን “በዳይ” አድርጎ የሚስለው ዝም ብሎ አይደለም። አባት ከቤቱ ሲወገድ ወይም በልጆቹ ዘንድ ተቀባይነት ሲያጣ፣ ቤተሰቡ “ጠበቃ፣ ጠባቂ አልባ” ይኾናልና ነው።

አባት የሌለው ቤት፤ እነ አንቶኒዮ ግራምሺ እንደሚፈልጉት ለጠላት ዘመቻ፣ ለማርክሳውያን አብዮት “የባህል ወረራ” ወለል ብሎ የተከፈተ ነው።

ወንድነትን እንደ “እርግማን” በመሳል፣ ወጣቱ ወንድ አባቱን መምሰል ትቶ “አልጫና ምስኪን” እንዲኾን ይደረጋል። ይህ ደግሞ ትውልዱን በሥነ-ልቦና የመስለቢያ፣ ማኅበረሰቡንም የማምከኛ ስልት ነው።

አባት በቤቱ ውስጥ ሥጋዊ መሪ ብቻ ሳይኾን “ካህንም” ነው። ልጆቹ እግዚአብሔርን እንዲፈሩ፣ ለሃቅ እንዲቆሙና ለጽድቅ እንዲጨክኑ የሚያደርግ የእምነት መምህር ነው።

ጠላት “Storytelling” ብሎ “መብትና ነፃነት” እያለ የሚያመጣው ትረካ፣ ይህንን የአባትነት መንፈሳዊ ሥልጣን ለመንጠቅ ነው።

አባት “አይኾንም” የሚለው ክልከላ፣ ልጁን ከመንፈሳዊ ውድቀት፣ ከባህላዊ ባርነት፣ ከሰውነትም ጥፋት የሚጠብቅ “ቅዱስ ቁጣ” እንጂ ጥላቻ አይደለም።

እነዚያ “እኩልነት” ሰባኪዎች ሴት ልጅን ከአባቷ ጥበቃ እንድትወጣ የሚገፋፏት ለነፃነቷ ሳይኾን እርሷንም ኾነ ዘሯን ለመበዝበዝ እንዲመቻቸው ነው።

አባት ለሴት ልጁ ያለው ፍቅርና ጥበቃ “ቁጥጥር” ተብሎ ሲፈረጅ፣ እርሷ ግን ለአታላዮችና “ለሥነ-ተዋልዶ ጤና”፦ ሞት ነጋዴዎች ሲሳይ ትኾናለች።


Post a Comment

0 Comments