✍ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
መልካም፣ ቅን፣ ደግ፣ የዋህ፣ ጥሩ፣ ቸር፣ አሳቢ፣ አጋዥ፣ ታዛዥ፣ አዛኝ፣ ደጋፊ፣ አቃፊ፣ ረዳት፣ ተንከባካቢ፣ ዝምተኛ፣ ዝግተኛ፣ ሰላማዊ፣ ተስማሚ፣ ተከታይ፣ ትኁት፣ጨዋ፣ጭምት፣ታጋሽ፣ ታማኝ፣ ለጋስ፣ ሩህሩህ... እነዚህ ብቻቸውን በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ስም ለወንዶቻችን ይቀርባሉ! ምስኪንነታቸውም ይረጋገጥበታል!
እነዚህ የለሰለሱ ጠባያት ብቻቸውን ለወንዶቻችን ሲሰበኩ፣ ወንዱን በውስጡ ያለውን ተፈጥሯዊ የአንበሳነት ግርማ እንዲጥል ይገፋፋሉ።
በዘመናዊው ዓለምና በተሳሳተ መንፈሳዊ ትርክት ውስጥ ታዲያ ወንድ ልጅ “ተምሳሌት” ተደርጎ የሚቀርብበት መንገድ እጅግ አደገኛ ወደ ኾነ “የምስኪንነት” አዘቅት እየገፋው ወደ “ባርነትም” እየነዳው ይገኛል።
ወንዱ በባሕርይው ሊኖሩት የሚገቡትን እንደ ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ አስፈሪነትና ተዋጊነት ያሉትን የአንበሳነት ግርማዎቹን “መርዛማ” በሚል፦ስምበማጥፋት"፤ በምትኩ ለሴትነት (Feminine) ጠባይ የቀረቡትን ዝርዝሮች ብቻ እንደ ብቸኛ የወንድነት መገለጫ እንዲቀበል ይገደዳል።
አንድ ወንድ ታዛዥ፣ ተከታይና ተስማሚ ብቻ እንዲኾን ሲሰበክ፣ የራሱ የኾነ ጽኑ አቋምና መሪነት የሌለው “ስልብ ጃንደርባ” ይኾናል።
ዝምተኛና ዝግተኛ እንዲኾን የሚመከረው ወንድ፣ እውነት ሲገፋና ቤተሰቡ ሲደፈር ድምፁን ከፍ አድርጎ የሚከላከልበትን ድፍረት ይነጠቃል። እነዚህ ባሕርያት በዘመናዊነት ስም ሲቀርቡ ወንዱን “ተከታይ” እና በቀላሉ የሚነዳ “ፍዝ አልጫ” ያደርጉታል።
ሚዲያውና ዘመናዊው ሥርዓት ወንዱን አጋዥ፣ አቃፊና ተንከባካቢ በሚሉ ቃላት ውስጥ አስረውት ይገኛሉ። እነዚህ ባሕርያት ከጀግንነትና ከኃይለኝነት ተለይተው ለብቻቸው ሲቆሙ፣ ወንዱንም ኾነ ቤተሰቡን ለጥቃት የተጋለጡ ያደርጓቸዋል።
አዛኝ፣ ሩህሩህና ለጋስ መኾን ውበት የሚኖረው ኃይልና ግርማ ሲታከልበት እንጂ፣ ኃይል ለሌለው “ሰነፍ፣ አቅመቢስና ጎስቋላ” ወንድ እነዚህ ባሕርያት የፈሪና የእንከፍ ምስኪን መግለጫዎች ኾነው ያገለግላሉ።
የዘመኑ ሚዲያ ነባሩንና ጥንታዊው፣ ትውፊታዊውን “አባወራ” (The Patriarch) እንደ ጨካኝ፣ ኋላ ቀርና “መርዛማ” (Toxic) አድርጎ ይፈርጀዋል።
በአንጻሩ “ተንከባካቢና ረዳት” የኾነውን፣ ሚስቱንና ማኅበረሰቡን ሳይጠይቅ፣ ሳይሞግት የሰጡትን እየተቀበለ የሚከተለውን “አልጫ ምስኪንም” ወንድ እንደ ሥልጡንና መንፈሳዊ አድርጎ ያቀርባል።
ይህ ምስል በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ሲቀረጽ፣ ወጣቱ ወንድ በውስጡ ያለውን ጽድቅ ይፈጽምበት ዘንድ የተሰጠውን ጀግንነትና ቆራጥነት እንደ ነውር እንዲቆጥረው ይደረጋል።
በውጤቱም ለቤተሰቡ የማይቆረቆር፣ ለሀገሩ የማይዋደቅ፣ ለቤተክርስትያኑም የማይገደው፣ “እሱ ያመጣውን እሱው ይመልሰው እንጂ” ብሎ በአሰስነቱ የሚወዘት አላዛኝና ነፍራቃ ትውልድ ይፈጥራል።
ትውፊታዊው አባወራ ቆፍጣና፣ ቆራጥ፣ ገሳጭ፣ ቀጪና መሪ ነበር። ይህ ግርማው ደግሞ ቤተሰቡን ከመንፈሳዊም ኾነ ከሥጋዊ ወረራና ጥቃት ይጠብቅ ነበር።
አሁን ግን በየሚዲያው ወንዱ ጭምት፣ ለስላሳ፣ ቀሰስተኛ፣ ጨዋና ሰላማዊ እንዲኾን በመገፋቱ፣ በቤቱ ውስጥ ያለውን የጠባቂነት ሚናውን እየተወው ይገኛል።
አንድም በመንፈሳዊነት ስም ትሕትናንና የዋህነትን ብቻ መስበክ፣ ወንዱን የመከላከያ ክንድ እንደሌለው ምስኪን ያደርገዋል። እውነተኛ ትሕትና ኃይል ኖሮት ያንን ኃይል መግዛት እንጂ፣ ኃይል አልባ ወኔቢስ መኾን አልነበረም።
ወንዱ ገሳጭ፣ ቀጪና መሪ መኾኑ ሲቀር፣ ቤተሰቡ ለርኩሰትና ለውድቀት የተጋለጠ ይኾናል። የዋህነት ብቻውን ምስኪንነት እንጂ ቅዱስነትን አይወክልም። በዚያም በቤቱ ሥርዓት ቅጡ ጠፍቶ ትውልዱ መረን ይኾናል።
የመገናኛ ብዙኃኑና የማትገጹም የጥንቱን ቆራጥና ቆፈጣና አባወራ ስብእና ከትውልዱ ልብ በማውጣት፣ ከሚዲያ በማጥፋት በማጥፋት፣ ወጣቱ ትውልድ አርአያ የሚኾኑትን ጠንካራ አባቶችና እሴታቸውን እንዳያውቅ ተደርጓል።
ይህ ጥሩ፣ ደግና ቅን የመኾን ማኅበራዊ ግፊትና ጫና ወንዱን ላልተስተዋለ ጃንደርባነት አቅርቦታል። ወንዱ ኃይሉንና ቆራጥነቱን ሲጥል፣ ማኅበረሰቡ መሪ፣ ጠባቂ የሌለውና ለጠላት የተመቸ ይኾናል።
ታጋሽና ታማኝ መኾንም ያለበት ለዓላማና ለእውነት እንጂ፣ ለውርደትና ለውሸት፣ ለአስመሳይነትና አድርባይነት ለኢፍትሐዊነትና ለጥቃት መኾን አልነበረበትም።
አንድም ነባሩ አባወራ አርበኛ፣ ቆፍጣና፣ አስፈሪና ጠባቂ ነበር። ይህ ባሕርይው ደግሞ ለጠላትና ለክፉ ሥርዓት የማይመች “እልከኛ” አድርጎታል።
ዘመናዊው ዓለም ግን የሚፈልገው በቀላሉ የሚነዳ “ምስኪን” ወንድን በመኾኑ፣ የጥንቱን አርአያነት ከዕይታ ውስጥ እንዲጠፋ ያደርጋል።
ወንዱ አቃፊና ደጋፊ ተንከባካቢም ብቻ እንዲኾን ሲገፋ፣ አጥር ኾኖ ቤቱን የሚጠብቅበትን፣ ማኅበረሰቡንም የሚታደግበትን “ተዋጊነት” ይረሳል።
ዛሬ፤ አሁን ባለንበትም ጊዜና ዘመን የጠፋው ወንድነት፣ ከትውልዱ የራቀው አባወራነት፤ እነዚህ የለሰለሱ፣ ታይታና ይኹንታን ያስቀደሙ፣ ብቻቸውን ቅብጠትና ቅልጠትን የሚያስከትሉቱ፤ ለወንዱ ብቸኛ የጽድቅ ጠባያት እንደኾኑ ተደርገው፣ እንዲኾኑም ታቅደው ስለሚቀርቡ ነው።
ይህም ኾን ተብሎ የሚፈጸም ነው!
☀️ ጀግንነት፣ ጠንካራነት፣ ጉልበተኛነት፣ ድፍረት፣ ኃይለኝነት፣ ጨካኝነት፣ ተዋጊነት፣ ትጉነት፣ ጽኑነት፣ ብርቱነት፣ ንቁነት፣ ጠርጣራነት፣ ድለኝነት፣ ጀብደኝነት፣ አርበኝነት፣ ጨካኝነት፣ አስፈሪነት፣ ቆራጥነት፣ ቆፍጣናነት፣ ቅዱስነት፣ ጠባቂነት፣ ተቆጪነት፣ ገሳጭነት፣ ቀጪነት፣ መሪነት፣ ልበሙሉነት፣ ልባምነት፣ እልከኝነት፣ ቁጡነት...
🌙 መልካም፣ ቅን፣ ደግ፣ የዋህ፣ ጥሩ፣ ቸር፣ አሳቢ፣ አጋዥ፣ ታዛዥ፣ አዛኝ፣ ደጋፊ፣ አቃፊ፣ ረዳት፣ ተንከባካቢ፣ ዝምተኛ፣ ዝግተኛ፣ ሰላማዊ፣ ተስማሚ፣ ተከታይ፣ ትኁት፣ ጨዋ፣ ጭምት፣ ታጋሽ፣ ታማኝ፣ ለጋስ፣ ሩህሩህ...
የመጀመሪያው ዝርዝር (ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ኃይለኝነት...) አድራጊ(active) የኾኑ ኃይሎች ናቸው። ዓለምን ለመግራት፣ ጠላትን ለመመከትና መዋቅርን ለመገንባት የሚያገለግሉ የወንድነት መክሊቱ ናቸው።
ሁለተኛው ዝርዝር (አሳቢነት፣ ተንከባካቢነት፣ ርኅራኄ...) ደግሞ ውስጣዊ፣ ተቀባይ፣ መጋቢ የኾኑ፣ ሕይወትን የሚያለመልሙና ትውልድን በለሰለሰ መንገድ የሚያንጹ የሴትነት ጸጋዎች ናቸው።
በዘመናዊውነትና መንፈሳዊነት ትርክት ውስጥ የምናስተውለው ትልቁ ችግር፣ ወንዱን ከራሱ “ወንድነት” አውጥቶ ወደ “ሴትነት” ጠባያት እንዲጠጋ የማድረግ ዝንባሌ ነው። ወንዱ “ምስኪን፣ ታዛዥና ዝምተኛ” እንዲሆን ሲገፋ፣ ሴትነትን እንዲላበስ እየተደረገ ነው።
የወንድ ጠባይ በወንድነቱ፣ የሴት ጠባይም በሴትነቱ ሲገኝ መልካም፣ ልክ፣ ተገቢ፣ ውብና ሰላማዊም ይኾናል።
ወንዱ የሴትነትን ጠባይ እንዲላበስ ሲገደድ፣ በቤት ውስጥ ሁለት “ሴት ወይም ሴትነት” ይፈጠራል።
ይህ ደግሞ መሪ፣ ጠባቂ የሌለውና ለጥቃት የተጋለጠ ቤተሰብን ሲፈጥር፤ በሴቷና በወንዱ፣ በባልና በሚስቱ፣ በእናትና በአባቱ መካከልም የፍቅርን ስሕበት ያጠፋል፣ መከጃጀልን አስቀርቶ መደባበርን ያመጣል፤ መፈቃቀድን አጥፍቶ መናናቅን ያስከትላል፤ መፋቀርን ትቶ መቻቻልን ይሰብካል፤ መዋሰብም ቀርቶ መተቃቀፍ ያዘወትራል።
ይህ ወንዶቻችን እንዲኾኑ የሚገፋላቸው ወንድነት ነው!
0 Comments