ለታናሼ ለልጄም የተተወ ሕያው የታሪክ ምስክርነት


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር


የትውልድ ምሽግ፣ የእሴት መከተቻ፣ የእምነት ማኅደሩ የኾነውን ክርስትያናዊ በተለይም ኢትዮጵያዊው ቤተሰብ ተንዶ ስታይ ከመደነቅ፤ ከውስጥ በባለቤቶቹ እንደፈረሰ ስታውቅ እንድትቆጭ!

ይህንን የታሪክ ማስታወሻ የምጽፍልህ ነገ አንተ ሀገርን፣ ቤተ ክርስቲያንን እና የማንነትህን እሴት ለመረከብ ስትነሳ፣ እኛ ዛሬ የቆምንበት መሬት ምን ያህል በሚያስደነግጥ ሁኔታ እየተሸረሸረ እንደነበር እንድታውቀውና ለቀጣዩ ተጋድሎ እንድትዘጋጅበት ነው።

ዛሬ አንተ የምታየው የቤተሰብ መፍረስና የትውልድ መረን መውጣት በድንገት የመጣ መቅሰፍት እንዳይመስልህ። ጠላትም ቢኾን፣ እኔ ደጋግሜ የምጠቅሰው የማርክሳዊ እሳቤም ቢኾን በሩን ሰብረው አልገቡም፤ ይልቁንስ በሩን የከፈቱለት የራሳችን እረኞችና ሊቃውንት ናቸው እንጂ።

እነርሱም ጥፋተኞች ቢኾኑ እንኳ ከስሕተታቸው ካልተማርክና፣ ጣትህን በነርሱ ላይ መቀሰር ከመረጥክ አንተም ከእነርሱ የባሰ አስመሳይ፣ አድርባይና ባንዳ መኾንህ አይቀርም።

እናም ታናሼ! ከስሕተታቸው ተማር!

እነርሱ ምን ቢማሩ፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ቢባሉም በእውነትና እምነቱ በአባቶቻቸውም እሴቱ ባልታነጸና ጽድቁን ይፈጽሙበት ዘንድ ባልሠለጠኑበት ሰውነት በድለዋል።

ስለኾነም አንተ ይህንን ጽሑፍ ካነበብክበት ጊዜ ጀምሮ በግፍና በኢፍትሐዊነት፣ በአስመሳይነትና በአድርባይንት ላይ ተቆጭተህ ጽድቁን ለመፈጸም ከመነሳትህ በፊት ይህንን አስተውል፦

  • በአባቶችህ እሴት ባልታነጸው ልብህ፣ ባልሠለጠንክበት ሰውነትህ ነገር ግን በትምህርት ብቻ በተሳለው እውቀትህ ከእነርሱም የባሰ በዳይ እንደምትኾን ይወቅ!

በዚህ እኛ በነበርንበት ጊዜና ዘመን ላይ ጠላት መጀመሪያ የመጣው በሥነ-መለኮት ኮሌጆቻችንና በልማት ተቋሞቻችን በኩል ነው።

EOC-DICAC (የቤተ ክርስቲያኒቱ የልማት ኮሚሽን) ከውጭ ለጋሾች በሚመጣ የገንዘብ ድጋፍ ተደልሎ፣ ኢትዮጵያዊውን፣ ክርስትያናዊውን የአባወራነት ምሰሶ የሚንዱ አጀንዳዎችን በይፋ ተቀብሎ አስተናገደ።

የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያንን (Church of England) ምዕመን አልባ ያደረጋት ያው “የሥርዓተ ጾታ መርዝ፦ ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት” በሚል የካባ ስም camouflage በዲካክ በኩል ወደ እኛ መጣ።

ይህም “ጾታዊ ጥቃትን እንከላከላለን” የሚል ማራኪ ስም ቢሰጡትም፣ በውስጡ ግን ሀገር፣ ድንበር፣ ቤተክርስትያን፣ እሴት ጠባቂውን አርበኛ አባወራውን “በዝባዥ፣ ጨቋኝና በዳይ” አድርጎ የመሳል፣ በትውልዱ የማስጠላት፣ ከቤቱም የማስወጣት ስውር አጀንዳ ነበር።

የራሳችን ሊቃውንት ይህንን እያወቁ ለገንዘብ ሲሉ የሮሚና ኢስትራቲን የ”ድልድል ፕሮጀክት” ደጃፋቸው ላይ “ምንጣፍ አንጥፈው አበባ ጎዝጉዘው” ተቀበሉ።

ይህንንም የነገርናቸው አካላት “እናውቀዋለን እኮ፣ ተቋሙ ገንዘብ ከሰጡት የማይቀበለው አጀንዳ የለም እኮ” ሲሉ ጽድቅ በማይፈጽሙት “እናውቃለን” ሲሉ ብቻ በሚታጀሩበት እብሪት ምንም ዐዲስ ነገር እንደማይመጣ፣ ሁሉን አውቀው ጨርሰው የተወዘቱበት እንደኾነ አስረግጠው የጠላትንና የሆዳደሮቹን ጥፋት አጠናከሩ።

ታናሼ! በአንድ ወቅት ማኅበረ ቅዱሳን የቤተሰብ ችግሮችን ለመወያየት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። በዚያ መድረክ ላይ እውነተኛ መፍትሔ ይወጣል ብለን ስንጠባበቅ፣ የታዘብነው ግን የአድርባዮችን ሸፍጥ ነበር።

በውይይቱ ላይ የቀረቡት “መፍትሔዎች” ራሳቸው የጥፋቱ አካል ነበሩ። ለምሳሌ፦ኦርቶዶክሳዊዋ እናት ልጆቿን በቤቷ እንድታሳድግ ከማበረታታት ይልቅ፣ ማርክሳዊ መነሻ ያለውን “የሕጻናት ማቆያ” (Day care) እንደ ታላቅ ስኬት ሲያቀርቡልን ነበር።

ይህ ማለት እናት ከቤቷ እንድትወጣና ትውልዱ በእንግዳ እጅ እንዲያድግ፣ አንድም እናት ከቤቷ ከልጆቿ ይበልጡንም ደግሞ ከባሏ ይልቅ የምታስቀድመው፣ የምትታዘዘውና፣ የምታገለግለው ቀጣሪዋን ወይንም መንግሥትን እንዲኾን መንገድ መክፈት መኾኑን ዘነጉት።

እኛም “ከብዙ ሥራና ተልዕኮ ጫና የተነሳ ላይታያቸው ይኾናል፣ መፍትሔ ፈልገው ተሰብስበዋልና ያልታያቸውን ብንጠቁማቸው ለሁላችንም ይበጃል” ብለን በአቅማችን የገባንን በተለይም ደግሞ እነርሱ የመከሩበትም መንገድ ሌሌሎች ሀገራትንም ያከሰራቸው እንደኾነ በጽሑፍ አድርገን በትኅትና አቀረብን።

የኾነው ግን ከጠበቅነው ይልቅ እጅግ አሳዛኝ ነው!

እረኞቻችን ለውይይት ሲቀመጡ እየጠፋ ያለውን ትውልድ፣ በፍቺ ምክንያት እየመከነ ያለውን ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ ለማዳን መስሎን ነበር።

ይኹን እንጂ ለእኛ የሰጠናቸውን ንድፈ ሐሳብ ዐይተው ከመወያየት፣ እኛን ጠርቶ ማብራሪያ ከመጠየቅ፣ አፈጻጸሙንም ከመመርመር ይልቅ፣ ለካ አስቀድመው የማርክሳዊው አብዮት፣ የግራምሺያዊው የእሴት ብሶት ከሚቀጣጠልባት እንግሊዝ በሮሚና ስትራቲ አማካኝነት የመጣላቸውን የቀበሉትንም “መፍትሔ” ለማስተዋወቅ ነበር።

ወንድምዓለም እወቅልኝማ!

ይህንን እኛ ዝም ብለን አልተመለከትንም! እየጠፋ የመጣውን ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ በተፈጥሮአዊ እውቀት ለመታደግ፣ አባወራውን (መሪውን) የሚያበቃና ቤተሰቡን ከጥፋት የሚታደግ ባለ 11 ገጽ ስልታዊ ንድፈ-ሐሳብ (Proposal) ለጠቅላይ ቤተ ክህነት፣ በወቅቱ “ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ በፍቺ እየጠፋ ነው” ሲል ባስ የማስመሰያ ድራማ ለሠራው ለማኅበረቅዱሳን፣ ለዐዲስአበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ሕብረት አቅርበን ነበር።

መሪዎቹ ግን የእኛን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ተፈጥሮአዊ መፍትሔ ከማየት ይልቅ፣ የሮሚናን ሸፍጣዊ፣ ማርክሳዊ፣ የጥፋት “መፍትሔ” መረጡ።

ለካ የሮሚና ስትራቲ ዳጎስ ያለ ጉርሻ ከማኅበረቅዱሳን የወቅቱ ሰብሳቢ ጀምሮ እስከ የተመረጡ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች እንዲሁም እስከ ቤተክርስትያና የልማትና ክርስትያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን (EOC-DICAC) ድረስ ያላጠገበው አልነበረም።

እኛ ይህንን የመፍትሔ ሃሳብ ስናቀርብ ለዓመታት የእንግሊዝ ቤተክርስትያን ያደረገችውን የቁልቁለት ጉዞ፣ ትውልዷንም አጥፍታ ማኅበረሰቧን ልጅ አልባ ጃንደርባ አድርጋ ያመከነችንበትንም የጥፋት መንገድ ስናጠና ቆይተን ነው።

ኾኖም ግን የእኛን ወንዱ በተሰጠው ጸጋ ላይ ሠልጥኖ፣ በልጽጎና አይሎ መከራንም በመጨለጥ ጽድቁን የሚፈጽምበትን፣ ስለ ቤተሰቡና ማኅበረሰቡ፣ ስለሀገርና ስለቤተክርስትያን ቤዛ የሚኾንበትን መንገድ ገፍተው፤

በጾታ እኩልነት፣ መብትና ነፃነት እንዲሁም ጸረ-ጾታዊ ጥቃት ስም የእንግሊዝን ቤተ ክርስቲያንን ያፈረሰውን የሮሚናን መርዝ የመረጡት ለምን መረጡ።

ታናሼ ሆይ፤ የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን (Church of England) ዛሬ የደረሰችበት የጥፋት ዳርቻ ለእኛ ማስጠንቀቂያ ነበር። እኛ ቀድመው ለተጠቀሱት ተቋማት ያስገባናቸው ሰነዶች ላይ እነዚህን በዝርዝር አስቀምጠን ነበር።

እውነተኛ እረኞቿ ይህንን ጥፋት አስቀድመው በማየት ምዕመኗን መታደግ ሲገባቸው፣ በዝምታና በሸፍጥ ለጥፋቱ በመተባበር ማኅበረ ምዕመኑን አጠፉ።

ዛሬም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ፣ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሊቃውንት ያንኑ የነገርናቸውን፣ ያሳየናቸውን የእንግሊዝን የታሪክ ስህተት እግር በእግር እየደገሙት ነው።

ወንድምዓለም! እኛ በዘመናችን የቻልነውን ያህል እየጮህን፣ ከመጮህም ይበልጥ በደረስንበት እውነት፣ እምነትና እሴት እየታነጽን ፈተናውንተ ተጋፍጠን እንኖራለን፤ እንዲህ ዓይነት ክስተት ሲኖር ደግሞ ሰነድ አዘጋጅተን፤ ለጠቅላይ ቤተ ክህነትም እናሳውቃለን።

ይህንን የምነግርህ ነገ ታሪክ ስትመረምር ቤተሰብ የተበተነው የፈረሰው በጠላት ጥንካሬ ሳይኾን፣ የአባት እናትህም ትዳር የፈረሰው፦ በገዛ እረኞቻችን አድርባይነት እስከ ሰንበት ትምህርት ቤት እና ግቢ ጉባኤያት ድረስ በሆዳደሮች በተዘረጋ የጥፋት ሰንሰለት መኾኑን እንድታውቅ ነው።

ይህንን ጥቂቶች “የቤተክርስትያን፣ የማኅበረ ምዕመኑም ነገር ይቆጫቸዋል” ያልናቸው ጋር አደረስነው ነገር ግን እነርሱ አስመሳይ ነበሩና ጆሮ ሊሰጡን አልወደዱም ነበር።

🌟 “ማዘን፣ ማላዘን፣ መነፋረቅም እንደጽድቅ በተቆጠረበት ማኅበር የአባቶቻችን የአባታችንም ሰልፍ፣ ተዋጊነት ድለኝነቱ ኩነኔ ቢኾን አይገርምም!

መሪዎቻችን በሰጡት አሳሳች መመሪያ፣ የነፍስ አባቶችም በያዙት ልክየለሽ ጣልቃ ገብነትና ሊቃውንቱ በመረጡት መጤ ዕይታ ምክንያት የኦርቶዶክሳዊው ቤተሰብ ማኅበረሰብም የሕልውና አደጋ ላይ ወድቋል፤ ይህም ለጠላት ሰርግና ምላሽ ኾኗል!

ወንድነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተወግዟል! በተለይም አባትነት በራሳቸው ለትውልዱ “አባት ነን” በሚሉ፣ አባታችንን እንድናመልክ በሚያስተምሩ አስመሳይ አድርባዮች፣ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎች ተኮንኗል!

እናትነትና ሴትነት ሴት መኾንም የተሻለ እንደኾነ ወንዶቻችን እንዲረዱት በቀጥታ ያይደለ በነገር እና በድርጊት ይሰበካል።

እጅግ በሚያሳዝን መልኩም ሴቶቻችንም እንደዚያ የተቆለጳጰሰ ሴትነታቸውን እንኳ እንዳይቀበሉት ይልቁንስ ከወንድ እኩል ይኾኑ ዘንድ እንደወንድ እንዲያስቡ፣ እንዲያደርጉ፣ እንዲወጡ፣ እንዲውሉ፣ እንዲኖሩ ይሰበካሉ።

መቼ፣ ማንን አግብተን እንዴትስ አድርገን ክርስትያናዊ ቤተሰብ ልንመሠርት እንዳለን ስንመረምር ፍጹም የማይቻል “የሕልም እንጀራ ኾኖብን” የእንግሊዝ ቤተክርስትያን ራሷንና ማኅበሯን ሀገሯንም ጭምር ይዛ ከወደቀችበት የጥፋት አፋፍ ላይ ቆመናል!

ልጆቻችን ወንድ መኾንን እስኪጠየፉ ድረስ ብሶተኛ ኾነዋል! የአባቶቻችን አርበኝነት፣ አባትነት፣ አባወራነትማ የማይሞክሩት የአንባገነኖች ሙያ ተደርጎ በልባቸው ተስሎባቸዋል።

ከዚህ ወዲያ ግን እንከፍ፣ ምስኪን፣ ጅል፣ ጅላጅል፣ ስልብ፣ ጃንደርባ፤ የጽድቁ፣ የፍትሑ፣ የእውነቱ ነገር የማይገደው፣ ከአያት ቅድማያቶቹ ፈለግ፣ ከትውፊት እሴታቸውም የተለየ ሆዳደር አልጫ እንዲኾን፦ ዝም ብለህ ኑር፤ አርፈህ ልጆችህን አሳድግ እየተባለ በሚቀልባቸው በጥምቅ በተሳሰሩቱ ይበረታታል።

ይህንንም ደግሞ ትውልዱን ለማጥፋት ሠልጥነው፣ ኦርቶዶክሳዊውንም ማኅበረሰብ ለማምከን ታጥቀው በተነሱ፣ ተነስተው በዘመቱ “ምሁራን” የቅድመ ጋብቻው ሥልጠና፣ የሴትና የወንዱ ስጦታና ሚና ጠላት እንደሚፈለገው አልጮችን ያፈራ ዘንድ በስፋት ይሰጣል።

ታናሼ! እኛ ዛሬ የሚጠበቅብንን እስከምንችለው ለማድረስ እረፍትን ሳንሻ፣ እንቅልፍም እየነሳን እየሠራን ነው። በተለይም እንዳንተ ልባቸው ባፍጢም በተደፉ አስመሳይ፣ አድርባይ ሆዳደሮች ስብከት ያልጠፉቱን ከአባቶቻችን በተቀበልነው እኛም ለጽድቅ ጨክነን በምንኖረው ወጉ ማሠልጠን!

አንተም ነገ የማንነትህን ጡብ ስትገነባ፣ ከእነዚህ “በር ከፋች” ሊቃውንትና አድርባዮች ተጠንቀቅ! ማስትሬትና ዶክትሬት ካላቸው፣ ሊቅና ሊቀ-ሊቃውንት ተብለው ካባ ላንቃ ከደረቡቱ ተጠንቀቅ!

የአባቶችህን ወንድነት ለሺህ ዘመናት ኖረውበት ከዚህ ያደረሰንን አርበኛዊ አባወራነትህን አጥብቀህ ያዝ! እርሱ ከመንፈሳዊነትም ኾነ ከዘመናዊነት ጋር የማይጋጭ አንተነትህን አጽንቶ የያዘ፣ አጥብቆ ያቆመ ነው።

እርሱን “በዝባዝ፣ ጨቋኝ፣ በዳይም ነው” የሚሉህ ለጠላት ሊማርኩህ በምንዳ የተገዙ አስመሳይ ቀጣፊዎች ናቸው።

አንተ አባወራው የቤተሰብህ የማኅበረሰብህም እረኛው፣ መሪው፣ ጠባቂው ሰትመጣ በጎች-ልጆችህ እንደሚበተኑ፣ ተኩላ-ጠላትህ፣ ሆዳደር “ሊቃውንትህ” ያውቃሉና፤

👉 እጅግ ከፍተኛ የራስ ላይ ሥልጣኔን ገንዘብ ባደረገ ጠንካራ ስብዕና ልትሰለፍ፣ አደራህንም ትጠብቅ ዘንድ ምሽግህን ልታጸና ይገባል።

👉 መከራን ስትጋፈጥ፣ በጦርነትም ስትፋለም እርሱ ዛሬ እኔ እንዳቀበልኩህ ቅብብሎሽ እንደኾነ እንጂ “በእኔ ጊዜ ጨርሼ አጥፍቼው” አትበል!

👉 ስለኾነም በዚያ በመከራ ውስጥም ቢኾን ፈለግህን ተከትሎ፣ በራሱ ላይ ሠልጥኖ፣ መከራውንም ጨልጦ፣ ጽድቁን መፈጸሙን የሚቀበልህን ትውልድ አምጥህ መሥራትን አትዘንጋ!

በርታ! የአባቶቻችን አምላክ ይጠብቅህ!💪

Post a Comment

0 Comments