በየጊዜው የሚቀያየረው ሳይንስ ስለ ዓለም የጠራ መረጃ የለውም። ፕላኔቶች 9 መሆናቸውን እየተናገረ ሕይወት ያለው አካል መሬት ላይ ብቻ እንደሆነ ይናገራል።
እውነታው ግን ከሳይንስ ባሻገር ነው። ዓለማት 20 ናቸው።
ሀ/ ከእሳት የተሰሩት የአምላክና የመላእክታት 9 ከተሞች
1/ ጽርሐ አርያም ፦ ቅድሥት ሥላሴ የሚገኝበት
የመጨረሻው ወደ ላይ ያለው ጣሪያ የሆነች ዓለም ናት።
2/ መንበረ ስብሐት ፦ መጠኗ መሬትን ታክላለች። አራት ማዕዘን ቅርጽ አላት። ሥላሴ ለፈቀዱት ሰው እየተገለጹ ይታዩታል፤ ያነጋግሩታል። ኢትዮጵያውያኑ ቅዱስ አቡነ ዮሴፍና ዘላስታ እና ቅዱስ ዘርዓ ብሩክ ዘግሽ ዓባይ... በተሰጣቸው ሰማያዊ ፀጋ መንበረ ስብሐት ድረስ በመሄድ ሥላሴ ጋር ይነጋገሩ ነበር።
3/ ሰማይ ውድድ፦ እንደ ዙፋን ያለች ዓለም ስትሆን ኪሩቤል ተሸክመዋት ትኖራለች።
4/ ሰማያዊት_ኢየሩሳሌም፦ 12 በሮች አላት። በአእማዶቿ ላይ ያለፉት ገና የሚወለዱት የጻድቃን ሰማዕታት ስም ተጽፎበታል። እቺ ከተማ የሳጥናኤል ከተማ የነበረች አሁን ግን ባዶ ናት። ከዓለም ፍጻሜ ቡሃላ ጻድቃን ሰዎች ይገቡባታል።
5/ ኢዮር ፦ ኪሩብ፣ ሱራፊ፣ ሚካኤል = በጥቅሉ 30 የመላእክት ነገዶች ይኖሩባታል።
6/ ራማ ፦ ገብርኤል፣ ሩፋኤል፣ ራጉኤል /ሱርያል/ = 30 የመላእክት ነገድ ይኖሩባታል።
7/ ኤረር፦ ፉኑኤል /ሰዳክያል /፣ ሳቁኤልና / ሰላትያል/፣ አፍኒን /አናንያል/= 30 የመላእክት ነገዶች ይኖሩባታል።
8/ ገሀነም፦ ከታላቁ ፍርድ ቡሃላ ክፉ ሰዎችም የሚገቡበት የስቃይ ቦታ ነው።
9/ የምድር ውስጥ የእሳት ከተማ:- በምድር ውስጥ ያለው የማይጠፋው እሳት -እሳተ ገሞራ ሆኖ የሚወጣው ምሳሌ አፋር ኤርታሌ። አጋንንት የታሰሩበት፣ የሰው /የክፉዎች / ነፍሳትም የሚሰቃዩበት ገላጋይ የሌለበት የልቅሶ፣ የጩኸት፣ የዋይታ፣ የጥርስ መንገጫገጭ ስፍራ ነው። አንዳንድ እጅግ ክፉ ሰዎች በሕይወታቸው መሬት ትውጣቸዋለች። ምሳሌ ዳታንና ቆሬን....
ለ/ ከውሀ የተሰሩ 4 ከተሞች
10/ ሐኖስ:- ከምናየው ሰማይ በላይ ያለው ሐኖስ ይባላል። የውሐ ከተማ ነው። ማን እንደሚኖርበት ሥላሴ ብቻ ያውቃሉ።
11/ ጠፈር ፦ ወደ ላይ የሚታየው ሰማይ ነው። የውሀ ከተማ ነው። ይህ የውሀ ከተማ ከፀሐይ የሚወጣው ሙቀት ፍጥረታትን አቃጥሎ እንዳይገድል እንደ ፍሪጅ ሙቀቱን እያመጣጠነ ይልካል። የእግዚአብሔር ስራ እፁብ ድንቅ ነው።
12/ ውቅያኖስ፦ በመሬት ላይ ያለው የውሃ ከተማ ነው። ብሔሞትና ሌዋታን፣ አሳ፣ አሳነባሪ.... የሚኖሩበት ትልቅከተማ ነው።
13/ ባህር፦ ከምድር ውስጥ ያለው ውሀ ነው። ከታላቁ የእሳት ከተማ በላይ ይህ ውሀ አለ። ከውሀው በላይ ሰውና እጽዋት የሚኖሩበት አፈር አለ። ጥቅሙ እሳቱ ከምድር ያሉትን ፍጥረታት እንዳያጠፋ ማቀዝቀዝ ነው። እፁብ ድንቅ ነው።
ሐ/ ከንፋስ የተሰሩ 2 ከተሞች
14/ ባቢል፦ ሐኖስን አቁሞ የያዘው የነፋስ ከተማ ነው። ውሀው ቁልቁል እንዳይፈስ ሽቅብ ወጥሮ ይዞታል። ከዚህ የንፋስ ከተማ ውስጥ ማን እንደሚኖር እግዚአብሔር ብቻ
ያውቃል።
15/ በርባሮስ ፦ መሬትን በአየር ላይ አቁሞ የያዛት የነፋስ አውታር ነው። መሬት ቦታዋን ለቃ እንዳትሄድ ወጥሮ ይዟታል። በሳይንስ centripetal and centrifugal force ብለው ለመጥራት ይሞክራሉ።
መ/ ከአፈር የተሰሩ 5 ዓለማት
16/ መሬት፦ የሰው ልጅ የሚኖርባት ማዕከላዊ አቅጣጫ ላይ ትገኛለች።
17/ ብሔረሕያዋን፦ ከመሬት ከፍ፣ ከሰማይ ዝቅ ብላ፣ ከመሬት በስተሰሜን አቅጣጫ ትገኛለች። ሞትን ሳይቀምሱ የሄዱት የቀደሙት ብሩካኑ አባቶች ሄኖክ፣ ኤልያስ፣ ዮሐንስ አቡ ቀለሚስ፣ ነአኩቶ ለአብ፣ አቡነ አረገዊ.... ይኖሩባታል።
በመጨረሻው ሰዓት የሀሰቱ ፈጣሪ ነኝ ባዩ ሲመጣ ውሸቱን ለማጋገለጥና ሰውን ለማዳን ወደ ምድር ይወርዳሉ። ይገላቸዋል። ከሞት ተነስተው ያርጋሉ።
18/ ብሔረብፁዓን፦ ከመሬት ከፍ ብላ በስተደቡብ አቅጣጫ ትገኛለች። ኤርሚያስ ዘመን እስራኤላውያን በባቢሎን ሲማረኩ የተወሰኑት በኃጢአታችን የመጣብን
መከራ ነው በማለት ወደ በረሀ በምናኔ ሲኖሩ አምላክ በደመና ጭኖ ከዚች ከተማ አኖራቸው ክብር ምስጋና ይግባውና። ይጋባሉ ነገር ግን በሕይወት ዘመናቸው 3 ጊዜ ብቻ ይገናኛሉ። 3 ልጅ ብቻ ይወልዳሉ። ወንድ ፣ ወንድ፣ ሴት ይወለዳሉ። 1000 ዓመት ብቻ ሳይጨምሩ ሳይቀንሱ ይኖራሉ። ሲሞቱ በደስታ ይቀበራሉ። ወደፊት ዘርዘር አድርጌ እጽፋለሁ።
19/ ሲዖል፦ ከመሬት ከፍ ብላ ከምዕራብ አቅጣጫ ትገኛለች። በዚህ ሰዓት ክፉ ሰዎች በነፍሳቸው የሚሰቃዩበት የመከራና የስቃይ ከተማ ነው።
20/ ገነት፦ ከመሬት ከፍ ብላ በስተምሥራቅ አቅጣጫ ትገኛለች። መልካም ሰዎች ሲሞቱ አሁን ገብተው የሚኖሩባት የደስታና የሐሴት ልዩ ውብ ከተማ ናት።
0 Comments