✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር
ትውልዱን ከመጣበት እሴቱ ለኑሮ ከሚታጠቀው ድፍረቱ ለይቶ ልባልባ ማድረግ፦ ተስፋ የቆረጠ፣ የተሸነፈ፣ ሳይሟገት የተረታ፣ ሳያገባ የተፋታ፤ ወኔቢስ፣ ተስፋቢስ፣ መካን ያደርገዋል!
የአንድ ሀገር ህልውና የሚቀጥለው በድንበር ጥበቃ ብቻ ሳይኾን በትውልዱ ልብ ውስጥ በሚቀመጥ “የጀግንነት እሳት፣ የክብሩ ድምቀት፣ የእምነቱ ጽናት” ነው።
ይህ እሳት ደግሞ የሚነድደው ከእርሱ በፊት ባለፉት የታሪክ ድርሳናት፣ በጀግኖች ገድልና የክብር፣ የልዕልናና የሉዓላዊነት ትርክት ነው።
ጃፓን በአንድ ወቅት ዓለምን ያስገረመ የተዋጊ አርበኞች “ሳሙራይ” ወኔና የክብር መርሕ ባለቤት ነበረች። ነገር ግን ይህንን የአንበሳ መንፈስ ለመስለብና ሕዝቡን ወኔ-ቢስ ለማድረግ የተካሄደው ስልታዊ የታሪክ “ክለሳና ብረዛ” ሀገሪቱን ዛሬ ከታመመችበት ልታገግም፣ ከወደቀችበት ልትነሳ የማትችልበት የትውልድ መጥፋት የማኅበረሰብም ምክነት አሳልፎ ሰጥቷታል።
ታሪክን በዛሬው የሞራል መነጽር ብቻ እየለኩ የጥንቶቹን ጀግኖች “በጥቃቅን ስህተቶች” አኮስሶ የሚያቀርበው፤ ለታሪኩ ባለቤት ባርነትን በጽድቅ ስም የሚግት ልባልባ አልያም ሆዳደር ምንደኛ ነው።
ትውልዱን ከመጣበት እሴቱ መነጠል፤ በዚያ በመጣበት፣ በተጠበቀበት፣ ትውፊት በተቀበለበት የጀግኖች መንገድ እንዳይቀጥል፣ ወደ ባርነቱ ግዞት “በደስታ” እንዲቀላቀል ማድረግ ነው።
የጃፓኑ ትውልድ ከወገቡ አይለይ የነበረ የጀግንነቱ ማሳያ፣ የክብሩ ምልክት የሳሙራዩ ሰይፍ ከወገቡ ላይ ብቻ ሳይኾን ከልቡ ውስጥም እንዲወጣ ተደርጓል።
ጀግንነት እንደ “ኋላቀርነት”፣ ለክብር መሞት እንደ “እብደት”፣ ሀገርን መጠበቅ ደግሞ እንደ “ጥበብ አልባነት” ተደርጎ ተተረከለት።
ይህ ትርክት በትውልዱ ውስጥ የፈጠረው ውጤት ደግሞ የመታነጽበት የጀግንነትና የክብር እሴትን ያጣ ልባልባ ትውልድን ነው። ልቡ ውስጥ የጀግንነት ኩራት የሌለው ትውልድ፣ ለኑሮ፣ ለሕይወት፣ ለተስፋ የሚታጠቀው ድፍረት ይከዳዋል።
ዛሬ በጃፓን የሚታየው ማኅበራዊ ቀውስ፦ ማግባትና መውለድ አለመፈለግ፤ የዚሁ የመንፈስ ስብራት ውጤት ነው። ትውልዱ “ሳይዋጋ የተሸነፈ” የኾነው፣ የታሪክ ጀግኖቹ ስለተኮነኑበትና የሚከተለው አርአያ ስለታጣ ነው።
አንድም ትውልዱ ይኖርበት ዘንድ ወኔ ድፍረቱን ያጣው የጀግንነትና የክብር እንጀራ ልቡ ውስጥ የሚጋግረውን፣ በዚያ የተጋገረ እንጀራ ላይ ማር ማር የሚል ጣፋጭ ጽድቁን የሚሞላበትን፤ የአባቶቹን እሴት አንቋሸው ስለጣሉበት ነው።
“ሳያገባ ገና ቀድሞ የሚፋታው” ደግሞ የቤተሰብ መሪነት፣ ጠባቂነትን የሚጠይቀውን መስዋዕትነትና ኃላፊነት የሚሸከምበት “የአንበሳ ልብ” አስቀድሞ ስለተነቀለ ነው።
ይህ በጠላት ተቀጣጥሎ፣ በሆዳደሮች ተጧጡፎ የተተረከ የሞራል ክለሳ፣ የጃፓንን ትውልድ ጀግናውን ሲያሳጣው፣ ራሱን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከትና ለትልቅ ዓላማ መኖርን በተራና ጊዜያዊ ጥቅም እንዲተካ አድርጎታል።
ለትውልድ ታሪክ ሲነገር የሀገር መሪዎችንና የጀግኖችን ገድል በሚያጠለሽ መልኩ ሲጻፍ ውጤቱ በራስጠልነት የተተበተበ ልባልባ ትውልድ ይፈጥራል።
ጃፓን ዛሬ በቴክኖሎጂ ብትበለጽግም፣ በመንፈስ ግን “የመከነች”፣ የትውልዷም የመኖር ወኔ የተሰለበ ሀገር እየኾነች ያለችው ለዚህ ነው።
ትውልዱ በቅር ከተተረኩለት በተለይም በቴክኖሎጂ አማካኝነት ከተሰራጩለት ታሪኮቹ የሚያገኘው ስንቅ የውርደትና የክስ ትርክት፦ አባቶችህ ጦረኛ፣ አያቶችህ አርበኛ፣ ቅድምዓያቶችህ ኃይለኛ፤ የሚል ብቻ ስለኾነ፣ የእንዲህ መኾናቸው ዓላማ፣ ትርጉምና አንድምታ ስለማይነገረው ለነገው ኑሮው፣ ሕይወቱ፣ ትዳሩ፣ ቤተሰቡ፤ ተጋድሎ የሚኾን ወኔ አይኖረውም።
“ሳይዋጉ መሸነፍ” የሚጀምረው እንዲህ ታሪክ ሲበረዝ ሲከለስ ነው፤ ገና ሳያገባ ከትዳር፣ ከቤተሰብ፣ ከኑሮ የሚመጣን ፈተና በሩቅ ኾኖ ፈርቶ፣ “ነፃነቴን አጣለሁ” ብሎ ሰግቶ ያልጫ ኑሮ መኖርን ብቻ ሮጦ፣ ዘር ሳይተኩ መክኖ መሞትን የሚያስመርጥ የጃንደርባ ሕይወት።
ሳይሟገቱ መረታትም የሚመጣው እንዲሁ በሆዳደር ሊቃውንቱ የጀግኖቹ ግርማ ሲጠለሽ፣ ሞገሳቸው ሲንቋሸሽ፣ ክብራቸው ሲወቀስ፣ ገድላቸው ሲከሰስ፣ ነው።
ስለሆነም ታሪክን መከለስና መበረዝ ትውልድን እንደመስለብ፣ የዘር ፍሬ (ቆለጡን) ቢተዉም የልቡን-ፍሬ ወኔውን እንደማኮላሸት ይቆጠራል።
ትውልዱ ለኑሮ የሚታጠቀው ድፍረት እንዲኖረው፣ የታሪክ ድርሳናቱ ይበልጡንም እውነተኛ ሊቃውንቱ የጀግኖቹን ጀብድና ግርማ ጠብቀው መተርጎም አለባቸው።
አንበሳ ደቦል አንበሳ እንዲኾን፣ መንጋውን እንዲጠብቅና እንዲመራ፣ የጫካውም ንግሥናውን ከአባቱ ተረክቦ እንዲቀጥል ከተፈለገ የታላላቅ አንበሶችን፣ የአባቶቹን የአያት ቅድማያቶቹን የጀግንነት ታሪክ እየተነገረው ያድጋል፤ እርሱም በአንበሶች እየተተረከለት።
ነገር ግን ይኸው ታሪክ በቀበሮዎች አልያም በድኩላና በበጎች ለደቦሎቹ ቢነገር፤ እንሰሳቱን በእውነት የሚገዛበት፣ ጫካውን በፍትሕ የሚያስተዳደድርበት ጀግንነቱ፣ ኃይለኝነቱ፣ ጉልበቱ “ንጉሥማ ጀግና ንጉሥ ነበር ግን ጭካኔ ያበዛል እንጂ” ተብሎ ያ ጀግንነትና ክብሩ ላይ ጥርጣሬ በሚያሳድር ትርክት ለልጆቹ ይቀርባል።
ጃፓን የደረሰባት የታሪክ ስብራት ለእኛም ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነበር፤ ነገር ማን ይድረስልን። መድረክ የተሰጣቸው፣ ከቤተመንግሥት እስከ ቤተመቅደስ በር የተከፈተላቸው ምንጣፍ የተነጠፈላቸው “አቦ፣ አቦ” ተብለው ውዳሴ ቅኔ የቀረበላቸው “ሊቃውንት” ስልብ ወኔቢስ፣ ልባልባ አጫ ጃንደርባ የምንኾንበትን ትርክት በዘመናዊነት በተለይና በይበልጥ ደግሞ በመንፈሳዊነት ስም ጋቱን እንጂ!
“(እውነተኛ ሊቃውንቱ” አልኩኝ፦ባፍጢም ከተደፉት አስመሳይና አድርባይ ከኾኑት፣ የእናት ጡት ነካሽነትን ከመረጡት፣ ከባለቤትነት ይልቅ ምንደኝነትን ከመረጡት፣ ከታማኝነት ይልቅ ባንዳነትን ከፈቀዱት ስለይ “እውነተኛ ሊቃውንቱ” አልኩኝ!)
ወንድምዓለም! “እንቶኔ መንፈሳዊ፣ እንቶኔ የታሪክ፣ የእውቀት ማኅደር ነው” ስለተባለ ብቻ ትርክታቸውን በብቸኝነት አትቀበል፤ ይልቁንስ ከሌሎችም አመሳክር እንጂ።
ዛሬ የምታየው የትውልድ መደንዘዝና መፍዘዝ የመጣው ወኔውን በሚሰልብ ትርክት ከአያት ቅድማያቶቹ እሴት ነጥለው አምኖ የሰጣቸውን ልብ ሰልበው ልባልባ ስላደረጉት ነው። ይህንንም ደግሞ ማንም ተራ ሰው ሳይኾን “ሊቃውንቱ” አደረጉት!
የአባወራ ንቅናቄ ይህን ከትውልዱ እንዲጠፋ የተፈለገውን ወኔ እሳቱን፣ ደም ሙቀቱን፣ ልበ ሙሉነቱን፣ በመመለስ ለክብር የሚቆም፣ ለጽድቁም መስዋዕት የሚኾን በዚያም ደስታውን የሚሸምት ልባም ትውልድ ለመውለድ ነው!
ይህ የጃፓን ታሪክ ቢኾንም ታሪክ እያላቸው፣ እሴት እያላቸው፣ ትውፊት እያላቸው በ”ሊቃውንቱ” ልባልባ አልጫ ተደርገው በጃንደርብነት የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ወገኖቼንም ይወክላል!
0 Comments