የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች


ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታር

ለልጅህ ልትሰጠው ጓግተህ ከመዘርጋትህ በፊት አንተ የቆምክበትን እሴት መቀበልክን እርግጠኛ ኹን! የትናንት ማንነትህን ተጠይፈህ፣ ለልጅህ የምትሰጠው “ዛሬ” እርሱም ልክ እንዳንተው የሚጠየፈው “ትናንቱ” ይኾናል!

ትውልድ የሚቀጥለው በሥጋና በቁስ ቅብብል ብቻ ሳይኾን በልብ ትስስርም ጭምር ነው። ትንቢተ ሚልክያስ 4፡6 ላይ “የአባቶችን ልብ ወደ ልጆች፥ የልጆችንም ልብ ወደ አባቶች ይመልሳል” የሚለው ቃል፣ ምድር ከእርግማን(ፍሬያማ ከመኾን ከመምከን) የምትድንበት ብቸኛው መፍትሔ መኾኑን ይነግረናል።

ኾኖም ይህ ቅብብል እንዲሳካ፣ አባወራው ለልጁ ልቡን ከመክፈቱ፣ እጁን ከመዘርጋቱ በፊት በቅድሚያ እጁ ላይ ያለው፣ ከአባቶቹ የተቀበለው “ሀብት” ምን እንደኾነ ሊመረምር ይገባል። “የተቀበልኩት መልካም ነገር የለም!” ብሎ የማንነቱን ምንጭ ራሱን ለሚያደርገው ልባልባ፣ ተቀባይ እንኳ ቢኖረው የእርሱ ቢጤ ልባልባ ነው።

ዛሬ ብዙ አባወራዎች ለልጆቻቸው “መልካም ሕይወትን” ለመስጠት ይጋደላሉ፤ ነገር ግን ራሳቸው አባቶቻቸውንና ትውፊታቸውን የተጠየፉ “ልባልባዎች” ኾነው ሳለ ለልጆቻቸው የሚሰጡት “ዛሬ” ተቀባይነት ሲያጣ ይገረማሉ።

አንተ ራስህ ማንነትህን ካልተቀበልከው፣ ባልተቀበልከው በካድከውም ማንነትህ የምትሰጠውን የሚቀበል ልጅህ የሚክደው እንጂ “ልባም” ሊሆን የሚችልበት ተፈጥሯዊ መንገድ የለም።

አድርባይ ሊቃውንት በትውልዱ ላይ የፈጸሙት ትልቁ ደባ ትውልዱ ከትውልዱም ወንዱ በራሱ ማንነትና ታሪክ ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርበት ማድረጋቸው ነው።

ትናንትናህን፣ የአያት ቅድመ አያቶችህን የጀግንነትና የጽድቅ ታሪክ እንደ “ኋላ ቀርነት” እንድታየው ተደርገሃል። ጀግኖቹን፣ ለክብርና ለድንበር የተዋደቁትን ከዚያ በተለየ መነጽር እንደ እብሪተኛ እንድታያቸው፣ አጥፊና ወራሪዎቹን ደግሞ እንደ ወዳጅ እንድትቆጥራቸው በአስመሳይ አድርባየቹ በረቀቀ መንገድ የተሸረበ ነው።

በዚህም ምክንያት የራስህን “ትናንት”፣ የአባቶችህን ትውፊት ተጠይፈህ፣ ለልጅህ የምታቀርበው “ዛሬ” የባዕድ ርዕዮተ-ዓለም ነጸብራቅ፣ የራስ ጠልነት ውጤት፣ የማርክሳውያን የብሶት ትርክት፣ የአልጫነትም ትሩፋት ብቻ ኾኗል።

ልብ በል! አንተ የአባቶችህን እሴትና ትውፊት ካልወረስክ፣ ለልጅህ የምትሰጠው ባዶ-ልብአልባነትን ብቻ ነው። ልጅህም ልክ እንዳንተው ያንተን “ዛሬ” (ለእርሱ ትናንቱ የሚሆነውን) የሚጠየፍና የሚንቅ፣ ሕይወት ዘሩን፣ ጽድቅ ትውፊቱን ማስቀጠል የማይፈልግ ስልብ፣ ጃንደርባ ኾኖ ያድጋል።

እርግማኑም ይኸው ነው፦ አባቶቹን፣ የአባቶቹን ፈለግ የጠላው ትውልድ፤ ራሱን እየጠላ የሚመክንበት፣ በዚያም በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት አሳቦ የሚመጻደቅበት የውድቀት አዙሪት!

ስለሆነም፣ የአባወራ ንቅናቄ ቀዳሚ ጥሪ አባወራው ራሱ ወደ አባቶቹ ልብ እንዲመለስ ነው። ጽድቁን በፈጸሙበት ጀግንነታቸው ዓለምን ያስገረሙሙ እነዚያን ልባም አባቶችህን ሳትቀበል ለልጅህ አባት ልትኾን አትችልም።

የአባወራው ልብ በአያት ቅድማያቶቹ ትውፊት ሲታነጽ ብቻ ነው ለልጁ የሚዘረጋው እጅ በረከት የሚኖረው። ያኔ ነው “የአባቶች ልብ ወደ ልጆች” የሚፈሰው። አንተ በአያቶችህ ታሪክ ስትከብር፣ ልጅህም ባንተ ይኮራል፤ ልቡም ወደ አንተ ይመለሳል።

አለበለዚያ ግን ከአባቶችህ “ፍጽምና” ጠብቀህ እንከን ድክመታቸውን አጉልህ በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት “ለመሻል” ብትታጀር፤ የታጀርክበት እብሪቱ ውድቀትህን፦ የትውልድ መረን መውጣት፣ መምከንና መጥፋትን፤ ሲያስከትል አትደነቅ።

ልባም ትውልድ የሚፈጠረው አባወራው ራሱን ታሪክን እየበረዙ፣ እየደለዙና እየሰረዙ ከሚተርኩ አድርባይ ሊቃውንት ራሱን ሲያነጻ ነው።

መልካም፣ ልክ፣ ተገቢና ውብ የኾነውን የምትለይበትና የምታሳይበት የአባቶችህን እሴት በሙሉ ልብህ ተቀበል። ያኔ ለልጅህ የምትሰጠው “ዛሬ” እርሱም በክብር የሚረከበውና ለልጆቹ የሚያወርሰው”ትናንት” ይኾናል።

ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብና ትውልድ የሚታደሱት በዚህ የልብ እርቅና ትስስር ነው። የአባቶቻችንን እሴት ኮንነው ከእርሱ ያራቁንን፣ ያጣሉንና ያስጣሉንን የዘመኔን “ሊቃውንት” በቃችሁ ልንላቸው ይገባል።

አልጫነት እንደ መንፈሳዊነት የተነገርበት፣ ጃንደርብነትም እንደ ጽድቅ የተቆለጳጰሰበት የአስመሳይ አድርባዮች “ክርስትና” በእናት ጡት ነካሾች የተሰበከ ሕዝቡን ለባርነት የማረከ፣ ትውልዱንም ለመጥፋት፣ ማኅበረሰቡንም ለምክነት የዳረገ ነው!

ይህ ስልብ ጃንደርባ ያልኾነ የአባወራው ትውልድ ንቅናቄ ነው!💪

Post a Comment

0 Comments