ከኢያሪኮ እስከ ቀራኒዮ (ክፍል ስድስት)


ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር

ወደ ኢየሩሳሌም የሚወስደው መንገድ አሁን በአቧራ ሳይሆን በዝማሬ ተሞልቷል። ከፊት ለፊቴ ያለው ብርሃን እየደመቀ፣ ድምፁም እየጎላ መጣ። እኔ በኢያሪኮ መንገድ ዳር ልብሴን ጥዬ የወጣሁት ሰው፣ አሁን በታላቁ የሆሣዕና ሰልፍ መካከል ነኝ። የሚያስገርመው ግን፣ እኔ የጣልኩት ያ አሮጌ ልብስ ትርጉሙ ተቀይሮ እዚህ ኢየሩሳሌም መግቢያ ላይ በሌላ መልክ አገኘሁት።

​ሰዎቹ መጎናጸፊያቸውን አውልቀው በመንገዱ ላይ ያነጥፋሉ። ይህ ትልቅ የእምነት ምስጢር አለው። እኔ በኢያሪኮ ልብሴን የጣልኩት "ከጭለማዬ ለመውጣት" ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ግን ልብሳቸውን የሚያነጥፉት "ለብርሃኑ ንጉሥ መንገዱን ለመጥረግ" ነው። የእኔ መራቆት ለነፃነቴ ነበር፣ የእነርሱ መራቆት ግን ለክብሩ ነው። ይህንን ክስተት ዝም ብዬ  ስመለከተው፣ ሰው መጀመሪያ ራሱን ነፃ ለማውጣት ማንነቱን ይጥላል፣ ቀጥሎ ግን ለፈጣሪው ክብር ሲል ያለውን ሁሉ ዝቅ ያደርጋል።

​ያኔ በመንገድ ዳር ሆኜ "የዳዊት ልጅ ማረኝ" ብዬ ስጮህ፣ ጥቂቶች ብቻ ነበሩ የሰሙኝ። አሁን ግን መላው ኢየሩሳሌም "ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ" እያለች በአንድ ድምፅ ትጮኻለች። የእኔ የግል ጩኸት አሁን የማኅበረሰብ መዝሙር ሆኗል። ነገር ግን በሰዎቹ መካከል ሆኜ ሳስተውል አንድ ልዩነት አያለሁ፦ ብዙዎቹ የሚጮኹት በዓይናቸው ያዩትን ድል በመናፈቅ ነው፣ እኔ ግን የምጮኸው በጨለማ ውስጥ ሆኜ ያገኘሁትን ያንን ፍጹም ሰላም በማጣጣም ነው።

​በአህያይቱ ላይ ተቀምጦ ሲያልፍ፣ ዓይኖቼ አሁንም በእርሱ ላይ ተተክለዋል። እግሮቹ በሰዎቹ ልብስ ላይ ሲረግጡ፣ እኔ የጣልኩትን ያንን አሮጌ ማንነቴን አስባለሁ። ንጉሡ የሚራመደው በሀርና በወርቅ ላይ ሳይሆን፣ በሰዎች ትሕትናና መስዋዕትነት ላይ ነው። ይህ ነው ትልቁ የነፃነት —ክብር የሚገኘው ከፍ በማለት ሳይሆን፣ ዝቅ ብሎ ሌላውን ከፍ በማድረግ ነው።

​እኔ በኢያሪኮ መንገድ ዳር "እውር" ተብዬ የምታወቀው ሰው፣ አሁን በኢየሩሳሌም አደባባይ "አይን ያለው ምስክር" ሆኛለሁ። ሰዎቹ "ሆሣዕና" ይላሉ፣ እኔ ግን በውስጤ "አሜን" እላለሁ። ምክንያቱም ሆሣዕና ማለት "አሁን አድን" ማለት ሲሆን፣ እኔ ደግሞ ያንን ድኅነት በነፍሴ ቀምሼዋለሁ።

​መንገዱ አሁን ወደ ቤተ መቅደሱ ያመራል። ያ የጣልኩት አሮጌ ልብስ አሁን በአዲስ የክብር መጎናጸፊያ ተተክቷል።

​እኔ ማለት ከኢያሪኮ አቧራ ተነሥቼ የጽዮንን ክብር ለማየት የታደልኩኝ ሰው ነኝ።


Post a Comment

0 Comments