የሮማዊው ያንበሳ ወኔ “በሊቃውንቷ” የባርነት ትርክት ተመትቶ፣ የሮማውያንን ግዛት የወለደች ማኅፀን ሽልጥልጥና ቅብጥብጥ ዜጋን የምታመርት መካን ኾነች!
የሮም ታላቅነት በድንጋይ ላይ የታነጸ ሳይኾን፣ በወንዶቿ አርበኛዊ ጽናትና ለሀገር መሞትን እንደ ትልቅ ክብር በሚቆጥረው እሴት ላይ የቆመ ነበረ።
ይኹን እንጂ ይህን የአንበሳ ግርማ የሰለቡት በቤተ መንግሥቱና በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የነበሩ “ሊቃውንት” ናቸው። እነዚህ ሊቃውንት ጀግንነትን እንደ “ኋላቀርነት”፣ አርበኝነትን ደግሞ እንደ “ጭካኔ” እየተረጎሙ ትውልዱን በረቂቅ ትርክት ማምከን ጀመሩ።
የታሪክ ጸሐፊዎቿ የጥንቱን ድል በ”ሞራል ክለሳ” ካራ እየሰለቡ፣ ትውልዱ በአባቶቹ ጀግንነት ከመኩራት ይልቅ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ ተገደደ።
ለዚህ የታሪክ መክሸፍ ትልቁ ማስረጃ የሮም ሊቃውንት ያመጡት የ”ኢፒኩሪያኒዝም” ፍልስፍና ሲሆን፣ ይህም ወጣቱ ሮማዊ ለሀገሩ ከመዋደቅ ይልቅ ለግል ተድላና “ለረቂቅ ሰላማዊነት” እንዲገዛ አደረገው።
ኤድዋርድ ጊቦን The History of the Decline and Fall of the Roman Empire በተሰኘው ታዋቂው ድርሳኑ እንደገለጠው፣ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የነበሩ መሪዎች “ትሕትናንና ታጋሽነትን” ያለ አውዱ በመስበክ፣ ሮማዊው ወንድ የነበረውን ወታደራዊ ወኔና የዜግነት ኃላፊነት እንዲጥል አደረጉት። ጀግንነት እንደ “ኃጢአት” ተቆጥሮ፣ ወጣቱ ወታደር ከመኾን ይልቅ ተድላን ወይም ገዳምን እንዲመርጥ በሊቃውንቱ ተገፋፋ።
ይህ በሊቃውንት የተጋተው ወኔን የሚያኮላሽ ትርክት ትውልዱን ልባልባ አድርጎ አስቀርቶታል። ሮማዊው ወንድ ሀገርን የመጠበቅ የአርበኝነትና የመሪነት አባወራዊ ወኔው ሲሰለብ፣ ትኩረቱን ወደ ሽቅርቅርነትና ወደ ከእናቱ እቅፍ የማይወጣ ጥገኝነት አዞረ።
(የጣልያን ወንዶች ከእናታቸው እቅፍ ሳይወጡ እስከ ጉልምስና ድረስ የሚቆዩበት፣ አግብተውም ከእናታቸው ቁጥጥርና ክትትል የማይወጡበት ወንድነት አባወራነታቸውን የሰለበ ጥገኝነት ነው)
ዛሬ ጣሊያን ለዘመናት በተሠራባት ትውልድን የመስለብ አደገኛ ሥራ፦ ተተኪ፣ ሀገር ተረካቢ ትውልድ አጥታ፣ መንደሮቿ ጭር ብለው የተወረረ ከተማ ኾነውባት አዝናለች።
ሮም በሰይፍ ሳይኾን በትርክት ተሸነፈች! የሊቃውንቱ “የሰላማዊነት፣ የትዕግስት፣ የትኅትና፣ የፍቅር” ስብከትና አርበኝነትን የመኮነን ሂደት ሮማዊውን ወንድ ሳይዋጋ የተሸነፈና ለባዕዳን ወራሪዎች እጁን የሰጠ “ልባልባ” አደረገው።
“የአንድን ማኅበረሰብ የጀግንነት ታሪክ እየኮነኑ ትውልዱን መጋት፣ ራሱን በራሱ የሚሰልብበትን ካራ በእጁ እንደመስጠት ነው” ያልነውን ደግመህ አስታውስ።
የሮማውያን ጥንታዊ አርበኛዊ እሴቶች በሊቃውንቱ ዘንድ እንደ “አሮጌና አላስፈላጊ” ተቆጥረው ተጣሉ። ይህም ትውልዱ ከመጣበት አርበኛዊ ትውፊት ተቆርጦ፣ በገዛ ታሪኩ እንዲያፍርና ለባዕዳን ወራሪዎች እጁን እንዲሰጥ አደረገው።
ሮም ታላቅ ነበረች፤ ነገር ግን የቤተመንግሥቱም ኾኑ የቤተመቅደሱ ሊቃውንቷ አርበኛዊ ወኔዋን ስለሰለቡባት፣ የጀግኖች መፍለቂያ የነበረችው ምድር ዛሬ ለትውልድ መጥፋት፣ ለማኅበረሰብ ምክነት ህያው ምስክር ኾና ቀርታለች።
ከወታደራዊው ሽንፈት በፊት በሊቃውንቱ የተሰለበችው ሮም ውድቀቷ፣ ጥፋት ምክነቷ እርግጥ ኾነ! አንድም አርበኛዊ፣ አባወራዊ፣ አባታዊ ወንድነት መክሊቱን፦ ጀግንነቱን፣ ድፍረቱን፣ ተዋጊነቱን፣ ኃይለኝነቱን፣ ወኔወን...፤ “አዋቂ ነን” ባሉ ሊቃውንት የተሰለበው ሮማዊ ወንድ ጠላት ወሮ በባርነት የሚነዳው ስልብ ጃንደርባ ኾነ!
ይህ ስልበቱም ለጥቂት ጊዜ ለማንሰራራት ቢሞክርም ተመልሶ እንዲጠፋ፣ እንዲከስም ተደርጓል! አሁን ግን እጅግ አስጊና ብሔራዊ አደጋ ኾኖ ለሀገሪቷ ሕልውና አስግቷል!
ታሪክን ሲያውቅ መልዕክት ጭብጡን ያንሻፈፈ ሊቅ ትውልዱን ይሰልባል፤ ትውልዱን የሰለበ ደግሞ ማኅበረሰቡን ያመክናል፣ ሀገሩንም ያፈርሳል!
ኢትዮጵያን እያሰባችኋት ነው ብዬ እገምታለሁ! እኔም ወደ እርሷ እየተንደረደርኩ ነው! የዘወትር ጥያቄዬ “ትውልዴ ይህ ሁሉ የጀግንነት፣ የአርበኝነት ታሪክ እያለው እንዴት አድርጎ ልባልባ፣ ስልብ ጃንደርባ ኾነ?” የሚለው!
0 Comments