የሁለት ዓለማት ዘውዶች ..ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው


✍ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር 

​ክብርና ልዕልና በአንድ ዙፋን ላይ ተጋብተው፣ የሥልጣን ግርማና የመለኮት ጥላ ተዋህደው የሚታዩበት ‘የንግሥና’ ምስጢር ለኢትዮጵያዊያን ባዕድ ጽንሰ-ሐሳብ አይደለም። እኛ ስለ ንጉሥና ስለ መንግሥት ግርማ ስንተርክ፣ እንደ ሌሎች አህጉራት ከመጻሕፍት ገጾች በቃለ-ታሪክ ተነግሮን ወይንም በልብ-ወለድ ድርሳናት ተስሎልን ሳይሆን፤ በደማችን ውስጥ በሚመላለስ የታሪክ ቅርስና በነፍሳችን ውስጥ በታተመ የማንነት አሻራ ኖረን ስለምናውቀው ነው። ንግሥና ለእኛ የፖለቲካ ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ከሰማያዊው መንግሥት ጋር የተቆራኘ የቅድስናና የሕልውና ማረጋገጫ ድልድያችን እንደነበር እናውቃለን።

​የጥንት አባቶቻችን የታሪክ ድርሳናትን ስናገላብጥ፣ በጊዜ ገደብና በዘመን አጥር የማይታጠር፣ እንደ ፀሐይ የሚያበራና የማይጠፋ የራሳችንን የሥልጣኔ ብርሃን እናገኛለን። ይህ ብርሃን ከምድያም ተራሮች ተነስቶ እስከ አክሱም ሐውልቶች፣ ከላሊበላ ድንቅ ጥበብ እስከ ጎንደር ቅጥሮች ድረስ የነገሥታትን ድምቀትና የዘውድን ክብር ሲያውጅ ኖሯል። እኛ የታሪክ ተቀባዮች ሳይሆን የታሪክ ሠሪዎች፣ የክብር ተመልካቾች ሳይሆን የግርማ ባለቤቶች ነን። ለዚህም ነው ስለ ንግሥና ድምቀትና ስለ ዘውድ ሥርዓት ምንነት ለመረዳት የባዕዳንን መዝገብ መፈተሽ ወይንም ወደ እሩቅ ሀገራት መጓዝ የማይጠበቅብን።

​የሌሎችን ሀገር ነገሥታትና የዘውድ ጭነት ሥነ-ሥርዓቶች ለምሳሌነት ለመጥቀስ ብንሞክር እንኳ፣ የእኛን ያህል ረጅም ዘመን ያስቆጠረ፣ ከሃይማኖታዊ ይዘት ጋር የተቆራኘና ከሕዝብ የልብ ትርታ ጋር የተጋመደ ሥርዓት ማግኘት አዳጋች ነው። የአውሮፓ ነገሥታት ግርማ በወርቅና በዕንቁ ድምቀት ቢታጀብም፣ የኢትዮጵያ ነገሥታት ግን "ንግሥና ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚሰጥ ጸጋ ነው" በሚል የጠለቀ ፍልስፍና የሕዝብና የፈጣሪ መገናኛ ሆነው ኖረዋል። ይህ የራሳችን የሆነ የዘውድ ትርክት፣ ዛሬ ላለንበት ማንነት መሠረት፣ ለነገው ተስፋችን ደግሞ መሪ ብርሃን ነው።

​በዚህ መንፈሳዊና ታሪካዊ መነጽር ውስጥ ሆነን፣ በ1923 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የታየውን እጅግ ዘመናዊና ደማቅ የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የንግሥ ሥርዓት ስንመለከት፣ በአንድ በኩል የምድራዊውን ክብር ከፍተኛ ጥበብ እናያለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ይህንን ግርማ "እንግዳውና ትሑቱ የክርስቶስ ንግሥና" ጋር ስናነጻጽረው፣ በምድራዊ ግርማና በሰማያዊ ትሕትና መካከል ያለውን ድንቅ የሀሳብ ፍጭት እንረዳለን። ታሪኩ ላይ ባንደርስበትም፣ በድርሳናቱ ውስጥ የምናገኘው ሀቅ ግን አንድ ነው፦ ንግሥና በኢትዮጵያ ምድር የኖረ እንጂ የተነገረ እውነት አይደለም።

ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ሰማይ በጥቁር ባሩድ ጭስና በነጭ ርግቦች ዝማሬ ተሞልቶ ነበር። በዚያ ታሪካዊ ንጋት፣ ኢትዮጵያ የጥንታዊ ሥልጣኔዋን ግርማ በዓለም ፊት የምታሳይበት፣ ክብሯን የምታድስበትና አዲሱን ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የምትሾምበት ዕለት ነበር። ይህ ሥርዓት በምድራዊ መለኪያ "ፍጹም" የሚባል የዘውድ ጭነት ነበር። የወርቅ ሰረገላዎች፣ የከበሩ ዕንቁዎች፣ የ101 መድፍ ድምፅና የዓለም ኃያላን መንግሥታት ልዑካን የታደሙበት ታላቅ ድግስ።

​ሆኖም፣ ይህንን ምድራዊ ግርማ "የባይተዋሩ የኢየሱስ የዘውድ ሥርዓት" ጋር ስናነጻጽረው፣ በሰማይና በምድር መካከል ያለውን ያህል ሰፊ ልዩነት እናገኛለን። የኢየሱስ የንግሥና ጉዞ—ወደ ኢየሩሳሌም በሆሳዕና መግባቱ—ምድራዊውን የንጉሥ አቀባበል ሕግጋት በሙሉ የገለበጠ፣ ዓለም አይታው የማታውቀው "የትሕትና ዘውድ" ነበር።

​የክብርና የዝቅታ ፍልሚያ፦ ሰረገላውና ውርንጭላዋ፣ 

በአዲስ አበባው የንግሥ ሥርዓት ላይ፣ ንጉሠ ነገሥቱና እቴጌ መነን የተሳፈሩት ከጀርመኑ ካይዘር ዊልሄልም የተገዛውን፣ በወርቅ ቅብ የተለበጠበውንና በፈረሶች የሚሳበውን ታላቅ ሰረገላ ነበር። ይህ ሰረገላ የሥልጣን፣ የሀብትና የሉዓላዊነት ምልክት ነበር። መንገዱ የተጠረገውና በኤሌክትሪክ መብራት የደመቀው ለንጉሣዊው ግርማ የሚመጥን ድባብ ለመፍጠር ነበር።

​በተቃራኒው፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ወደ ከተማው የገባበት መንገድ "እጅግ እንግዳ" ነበር። እርሱ ሰረገላ አልፈለገም፤ ፈረስም አልጋለበም። ይልቁንም ማንም ያልተጫነባት፣ የጭነት እንስሳ የሆነችውን የአህያ ውርንጭላ መረጠ። የዓለም ነገሥታት ለክብራቸው ሲሉ ምርጥ ፈረሶችንና የጦር ሰረገላዎችን ሲያሰናዱ፣ የሰላሙ ንጉሥ ግን በውርንጭላ ላይ ሆኖ መጣ። ይህ ምርጫው ብቻውን ለዓለም መሪዎች ትልቅ መልእክት ነበረው፦ የእርሱ መንግሥት በኃይልና በጭቆና ላይ ሳይሆን በትሕትናና በሰላም ላይ የተመሠረተች መሆኗን። የኢየሱስ "ሰረገላ" የድሆችና የትሑታን መገለጫ የሆነችው አህያ ነበረች።

​የታዳሚው ማንነት፦ የነገሥታት ልዑካንና የገሊላ ዓሣ አጥማጆች፣ 

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሲነግሡ፣ በአዲስ አበባ ፣መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን የተሰበሰቡት የእንግሊዝ፣ የፈረንሳይ፣ የጣሊያንና የጃፓን ልዑካን ነበሩ። እነዚህ ታዳሚዎች የዓለምን ፖለቲካዊ ሚዛን የሚወክሉ፣ በክብርና በሀብት የተሞሉ ነበሩ። የለንደን ታይምስና ሌሎች የዓለም ጋዜጦች የዚህን ንግሥ ታላቅነት በውጭ ሀገር ልዑካን ዓይን አማካኝነት ዘግበውታል።

​በሆሳዕናው የንግሥ ሥርዓት ግን ታዳሚዎቹ እነማን ነበሩ? የኢየሱስ አጃቢዎች "ልብሳቸው ዓሳ ዓሳ የሚሸት  ዓሣ አጥማጆች፣ ድሆችና በመንገድ ላይ የተሰበሰቡ ተራ ሰዎች" ነበሩ። ከእርሱ ጋር የነበሩት ከኃጢአታቸው የተመለሱ የቀረጥ ሰብሳቢዎች፣ ዓይናቸው የበራላቸው አይነ ስውሮችና የተናቁ የገሊላ ገበሬዎች ነበሩ። የዓለም ኃያላን (ሮማውያንና አይሁድ መሪዎች) ይህንን "የዘውድ ሥርዓት" ሊታደሙ ቀርቶ፣ ሊመለከቱት እንኳ አልፈለጉም። የኢየሱስ ታዳሚዎች በክብር የተሸለሙ ዲፕሎማቶች ሳይሆኑ፣ በጸጋ የተሸለሙ ኃጢአተኞች ነበሩ።

​ምንጣፉና ልብሱ፦ የሐር ምንጣፍና የቆሸሹ ጋቢዎች፣ 

ለአፄ ኃይለሥላሴ የንግሥ በዓል፣ አዲስ አበባ አዲስ ገጽታ ለብሳ ነበር። መንገዶች ታድሰዋል፣ አደባባዮች አምረው ነበር። ንጉሡ የሚረግጡትና የሚጓዙበት መንገድ ሁሉ የሀገሪቱን ታላቅነት በሚያሳዩ ምልክቶች ተሞልቶ ነበር።

​በኢየሩሳሌም መንገድ ላይ ግን የታየው ምንጣፍ "የትሕትና ምንጣፍ" ነበር።  ሕዝቡ የቆሸሹና የሚሸቱ ልብሶቻቸውን መንገድ ላይ ያነጥፉ ነበር። አሮጌ ጋቢዎቻቸውንና የዘንባባ ቅርንጫፎችን መሬት ላይ ማድረጋቸው፣ "ያለን ነገር ይኸው ነው፣ ያለንን ግን ላንተ ሰጥተናል" የሚል የመገዛት ምልክት ነበር። ይህ ምስኪን ሕዝብ ለንጉሡ ያነጠፈለት የሐር ምንጣፍ አልነበረም፤ ይልቁንም የዕለት ጉርስ የሚቸገሩ ሰዎች የሰውነት መከለያቸውን አውልቀው የፈጠሩት "የፍቅር ምንጣፍ" ነበር። ይህ ትዕይንት ለምድራዊ ንጉሥ ቢደረግ ንቀት ሊመስል ይችል ነበር፤ ለሰማያዊው ንጉሥ ግን እጅግ የከበረ መሥዋዕት ነበር።

​ዘውዱና ትርጉሙ፦ የወርቅ አክሊልና የእሾህ ትንቢት፣ 

የጥቅምት 23ቱ በዓል ዋና ማሳረጊያ፣ አቡነ ቄርሎስ 7 ኪሎ ግራም የሚመዝነውን፣ በወርቅና በአልማዝ ያጌጠውን ዘውድ በንጉሠ ነገሥቱ ራስ ላይ የጫኑበት ቅጽበት ነበር። ይህ ዘውድ የኢትዮጵያ ሦስት ሺህ ዘመን ታሪክ፣ የሰሎሞናዊው ስርወ-መንግሥትና የሉዓላዊነት ምልክት ነበር። ይህ ዘውድ ንጉሡን ከሌላው ሕዝብ ከፍ የሚያደርግ፣ የሚለይና የሚያከብር ነበር።

​ኢየሱስ ግን በሆሳዕና ዕለት ሊቀበለው የመጣው ዘውድ "እንግዳ" ነበር። የሆሳዕናው ጩኸት "አሁን አድን (ሆሳዕና)" የሚል ቢሆንም፣ ይህ ንግሥና በቀጥታ ወደ ቀራንዮ የሚመራ ነበር። ሕዝቡ ምድራዊ ነጻነትን የሚያመጣ የወርቅ ዘውድ የጫነ ንጉሥ ቢጠብቅም፣ ኢየሱስ ግን ለሰው ልጆች ኃጢአት የሚከፈል የእሾህ አክሊል ሊቀበል ተዘጋጅቶ ነበር። ምድራዊው ዘውድ ንጉሡን ሲሾም፣ የኢየሱስ "እንግዳ ዘውድ" ግን የዓለምን ኃጢአት ተሸክሞ እንዲሰቀል የሚፈርድበት ነበር።

​ድል አድራጊነቱ፦ ጦርነትና ሰላም፣ 

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ንግሥ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት በግርማ ታይቷል። የአንበሳ ለምድ የለበሱ ጀግኖች፣ በዘመናዊ መሣሪያ የሰለጠኑ ወታደሮችና የፈረሰኞች ጦር የንጉሡን አሸናፊነትና ሀገር የመከላከል ብቃት ያሳዩ ነበር። ይህ ጦር ጠላትን የሚያስፈራ፣ ድንበር የሚያስከብር ኃይል ነበር።

​የኢየሱስ ድል አድራጊነት ግን የተለየ ነበር። "እርሱ የመጣው ለጦርነት ሳይሆን ለሰላም ነው"። ኢየሱስ የሮማውያንን ወታደራዊ ኃይል ለመደምሰስ ጦር አልሰበሰበም፤ ይልቁንም በሕዝብ መካከል ሰላምንና ፍቅርን ሰበከ። የእርሱ ድል አድራጊነት በጦር አውድማ ላይ ሳይሆን፣ በሰው ልብ ውስጥ የሚገኝ ድል ነበር። እርሱ ሊያሸንፍ የመጣው ቄሣርን ሳይሆን ሞትንና ኃጢአትን ነበር። ለዚህም ነው ንግሥናው "እንግዳ" የሆነው፤ ዓለም ድልን የምታውቀው በደም መፋሰስ ሲሆን፣ እርሱ ግን ድልን ያመጣው የገዛ ደሙን በማፍሰስ ነበር።

​የሕዝቡ ጩኸት፦ ከክብር ወደ መስቀል፣ 

የአፄ ኃይለሥላሴ ንግሥ በዓል በታላቅ እልልታና "ሺህ ዓመት ይንገሡ" በሚል ምርቃት ተፈጽሟል። ሕዝቡ ለንጉሡ ያለውን ታማኝነትና ክብር በጭብጨባና በእልልታ  ገልጿል። ይህ ክብር ንጉሡ በዙፋናቸው ላይ እስካሉ ድረስ የቀጠለ ምድራዊ ክብር ነበር።

​በሆሳዕናው ዕለት ግን የተሰማው "ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ" የሚለው ጩኸት "የሕዝብን ወላዋይነት" የሚያሳይ ነበር። ዛሬ "አሁን አድን" እያለ ልብሱን ያነጠፈው ሕዝብ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ "ስቀለው!" ብሎ እንደሚጮኽ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። ይህ የዘውድ ሥርዓት እንግዳ የሚያደርገውም ይኸው ነው፦ ንጉሡ የሕዝቡን ስሜት ሳይሆን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለመፈጸም መምጣቱ። ሕዝቡ የሚፈልገው "ተአምር ሰሪና ሆድ የሚሞላ" ንጉሥ ነበር፤ ኢየሱስ ግን "ኃጢአትን የሚያጥብና ነፍስን የሚያድን" ንጉሥ ሆኖ መጣ።

​የማይጠፋው ዘውድ ምስጢር፣ 

በአጠቃላይ፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንግሥ ሥርዓት የምድራዊ ክብር፣ የታሪክና የብሔራዊ ኩራት መግለጫ ሲሆን፣ የኢየሱስ የሆሳዕና ንግሥና ግን የመለኮታዊ ፍቅር፣ የትሕትናና የድነት ምስጢር ነው። የኢየሱስ የዘውድ ሥርዓት "እንግዳ" የሆነው ለምድራዊው ሰው አስተሳሰብ ስለማይመጥን ነው።

​ምድራዊ ነገሥታት ሲነግሡ ሕዝብን ይገዛሉ፤ የናዝሬቱ ኢየሱስ ግን ሲነግሥ ለሕዝቡ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። ምድራዊ ነገሥታት በወርቅ ዘውድ ይከብራሉ፤ እርሱ ግን በእሾህ አክሊል እኛን አከበረ። በአዲስ አበባ የነበረው ሰረገላና ድምቀት የሀገር ታሪክ ሆኖ ሲዘከር፣ በኢየሩሳሌም የታየው የውርንጭላ ጉዞና የሆሳዕና ጩኸት ግን የሰው ልጅን ከዘላለም ሞት ያዳነ የሕይወት መንገድ ሆኖ ለዘላለም ይኖራል።

​እውነተኛው የዘውድ ሥርዓት በወርቁ ድምቀት ውስጥ ሳይሆን፣ በውርንጭላዋ ትሕትና ውስጥ ነበር። እውነተኛው ንጉሥም በታላላቅ ልዑካን የታጀበው ሳይሆን፣ "ለጌታ ያስፈልጉታል" ተብሎ የቀረበው የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። እርሱ በመጀመሪያ የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ካልታረደ በቀር ለማንም ንጉሥ ሊሆን አይችልም። የሆሳዕናው ጉዞም ይህንን ታላቅ እውነት ለዓለም ያበሰረበት "እንግዳው የዘውድ ሥርዓት" ነበር።

“..ሆሣዕና፤ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው፤”

Post a Comment

0 Comments