✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ
የአንድ ታላቅ ሕዝብ የጀግና ታሪክ በቀጥታ መደምሰስ፣ መደለዝና መሰረዝ ባይቻል እንኳ በረቂቅ “የእሴት ትንታኔ”፣ በዐዲስ ትርክት፣ በሞራልም ሚዛን በሊቃውንቱ እጅ ታሪኩ ይከሽፋል፤ ትውልዱም ይመክናል!
አቡነ ፊሊጶስ ከዐፄ ዓምደጽዮን ጋር እንደተሟገቱ
ለዚህ ጽሑፍ ምርምር እተመለከትኳቸው ያሉ ሦስት ዐበይት መጻሕፍት አሉ እነርሱም፦
፩ኛ የጋሽ ተክለጻድቅ መኩሪያ፦ የኢትዮጵያ ታሪክ- ከዐፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዐፄ ልብነ ድንግል፤
፪ኛ የመሪ. ራስ. ኤ. ኤም. በላይ የጥንቷ የኢትዮጵያ የትንሳኤ ታሪክ
፫ኛ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት አራቱ ኃያላን
በተጨማሪም ሌሎችንም አጫጭር ድርሰቶችን ተጠቅሜያለሁ።
“ይህ ሁሉ የጀብድ የጀግንነት ታሪክ ያላት፣ ትውልዷን በጠንካራ ስብዕና መገንባት የሚያስችል እሴት ያላት ሀገር፤ ታሪኳን የሚያውቅ ነገር ግን ከእሴቱ ያልተካፈለ፣ ትውፊቱን ያላስቀጠለ ልባልባ ትውልድ ለምን ተገኘ?
👉 ታሪኩስ ይህንን ትውፊታዊ የጀግንነት፣ የክብር፣ የነፃነት ቅብብሎሽ ማስቀጠል እንዳይችል በቦታውም እንከፍ፣ ምስኪን፣ ጃንደርባና አልጫ ትውልድ ይወጣ ዘንድ ለምን ከሸፈ?
በዚህ ምርምር በዐፄ ዓምደ ጽዮን እና በአባ ፊሊጶስ መካከል የተፈጠረውን የታሪክ ግጭት የ”አራቱ ኃያላን” ደራሲ ለራሱ “የሐሰት ትርክት” ግንባታ እንዴት እንደተጠቀመበትና ይህም ታሪክን የማክሸፍ ሴራ የሚያሰኘው በምን ምክንያቶች እንደኾነ እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን፦
፩. የታሪክን የንጉሥንም “ግርማ” በ”ነውር” የማጠየም፣ የማጠልሸት፣ የማስጠላትና የመቅበር ስልት፤
ዐፄ ዓምደ ጽዮን በኢትዮጵያ ታሪክ ብቻ ሳይኾን በዓለም አቀፍ ወታደራዊ ስትራቴጂ የሚደነቁ፣ ድንበር ያስከበሩና የሀገርን ሉዓላዊነት ያጸኑ ታላቅ አርበኛ መሪ ነበሩ።
የንጉሡን ኃያልነትና የስትራቴጂክ አስተሳሰብ ጥልቀት ከሚያሳዩ የታሪክ ሰነዶች መካከል፣ በዘመኑ የነበሩት የግብፅ ሹማምነሰት በዚያ በነበሩ በክርስቲያኖች ላይ ግፍ ሲፈጽሙ “አባይን ገድቤ አቅጣጫውን በማስለወጥ ግብፅን በረሃ አደርጋታለሁ” ብለው ያስፈራሩበትና የተገዳደሩበት ታሪክ አንዱ ነው።
ይህ ፉከራ ንጉሡ ከወታደራዊ ኃይል ባሻገር የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጸጋና የጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነት የተረዱ፣ ለሕዝባቸውና ለሃይማኖታቸው ክብር በዓለም መድረክ የሚሟገቱ “ኃያል” መሪ መኾናቸውን ያሳያል።
ሆኖም ደራሲው ይህን የመሰለውን የጀግንነትና የብሔራዊ ኩራት ምንጭ የኾነ ታላቅ ታሪክ ወደ ጎን በመተው፣ ትኩረቱን ንጉሡ በፈጸሙት የግል “የሥነ-ምግባር ስህተት” ላይ ብቻ እንዲያርፍ ያደርጋል።
ሸፍጡ(ሴራው)፦
፩.፩ ከንጉሡን ግርማ ይልቅ “የተወቀሱበትን” ማጉላቱ
ግብፅንና የዓለምን ኃያላን ያስበረገገውን ባለ ግርማ ንጉሥ በሚስትና በእቁባት ታሪክ ውስጥ “ቀብሮ” በማቅረብ፣ ትውልዱ ስለ ንጉሡ ሲያስብ ከአባይ ገዳቢነታቸው፣ ከድንበር አስከባሪነታቸው፣ ከተፈሪ ግርማቸው ይልቅ “ነውራቸው” ብቻ ትዝ እንዲለው ያደርጋል።
🚨 አደጋው፦በዚህ የተዛባ ትርከት የሚገኘው ትውልድ ከንጉሡ ታሪክ የግርማ ወኔን ከመቅዳት ይልቅ፣ በአባቶቹ ታሪክ እንዲሸማቀቅና የጀግንነቱ ሰንሰለት እንዲበጥስ ይገፋፋል፣ ከታሪኩ የሚያገኘውን እሴት በማጠልሸት እንዲከሽፍ ይደረጋል። ይህ በትክክል ትውልዱን በታሪኩ እንዲያፍር “ልባልባም” እንዲኾን የሚያደርግ ነው።
፩.፪ አርበኛዊ አባወራነትን አክሽፎ እንከፍ ምስኪንንነትን ማቀባበሉ
ትውልዱ ከትውልዱም በተለይ ወንዱ ንጉሡ ለግዛቱና ለሕዝቡ የነበራቸውን ቀናኢነትና መስዋዕትነት በጀግንነት ተተርኮለት፣ ትርጉሙና እሴቱ ተፈቶለት ቢታነጽ ኖሮ፣ እርሱም ለገዛ ክብሩ (ለሚስቱ፣ ለልጆቹ፣ ለቤተሰቡና ለሀገሩ) የሚዋደቅ ኩሩ፣ አርበኛ አባወራ ይኾን ነበር።
ነገር ግን በሊቃውንቱ የሐሰት ትርክት በተለይም በዚህኛው መጽሐፍ ደራሲ “የአርበኝነት ጭካኔ፣ የንጉሡም ነውረኛነት” የሚል መልዕክት ያለው መርዝ ሲጋት፣ ወንዱ ለክብሩ መቆምን ይተዋል።
አንድ ሕዝብ የጀግንነትና የክብር ታሪክ እያለው ትውልዱ “ልባልባና ጃንደርባ” የሚኾነው እንዲህ ዓይነት ትንታኔዎች ሲሰሩበት ነው። የንጉሡ የግል ሕይወት “ስህተት” እንደ ንጉሥነታቸውና እንደ አርበኝነታቸው ሚዛን ተጠብቆ ሊቀርብ ሲገባው፣ ደራሲው ግን “ስህተቱን” ብቻ አጉልቶ ንጉሡን “ነውረኛ” አድርጎ ይስላቸዋል።
ይህም ትውልዱ የጀግናውን ፈለግ ከመከተል ይልቅ፣ ጀግናውን እንደ ባዕድ እንዲቆጥርና ራሱን ከታሪካዊ ግርማው እንዲያገል ያደርገዋል። ይህ ማለት ታሪክን የሰለበ ትውልዱን ይሰልባል፤ ትውልዱን የሰለበ ደግሞ ሀገሩን ያመክናል!
🚨 አደጋውም እጅግ አሳዛኝና አሳፋሪ የኾነ አልጫ፣ ግዴለሽ፣ ንዝህላልና “እንከፍ” የኾነ ትውልድ ያፈራል።
ይህ የደራሲው “ታሪክን ማክሸፍ”፤ አንድም ራሱ ያከሸፈውን ታሪክ እንደ ትልቅ ሥራ ለትውልድ ማስቀረት፦ ትውልዱ ክብሩን ከመጠበቅ፣ ለክብሩ ከመሞት ይልቅ ለጥቅሙ እንዲሮጥ፣ ባፍጢም ተደፍቶም በሆዳደርነት፣ በእናት ጡት ነካሽነትና በባንዳነት ቤተሰቡንና ሀገሩን አሳልፎ የሚሰጥ አስመሳይ አድርባይ የሚያደርገው ይኾናል።
፩.፫ በሴቷ ዘንድ የሴትነት መርከስ
በሌላ በኩል ደራሲው የንጉሡን የጀግንነት ታሪክ አጠልሽቶ “ኩነኔውን” ብቻ ሲያገንነው፣ ሴቷም ከዚህ ተኮንኖ ከቀረበላት የአባቷ፣ የአባቶቿና የቅድማያቶቿ ታሪካቸው የምትቀስመው ውድቀት አለ።
እርሱም፦ ንጉሡ ለግዛቱና ለእርሱ ለኾነው ሁሉ በጀግንነት እንደተዋደቀ ቢነገራት ኖሮ፣ እርሷም “የእኔ” የምትለውንና የምትከብርበትን የሰውነት ተፈጥሮዋን፣ የሴትነት ጸጋዋን፣ የሚስትነት ክብሯንና የእናትነት ማዕረጓን በንጽሕና ለመጠበቅ ትተጋ፣ ፈተናውን ተጋፍጣ ትጠብቅ፣ መከራውም ላይ ጨክና ታበለጽገው ታተርፍበትም ነበር።
ነገር ግን የጀግንነትና የባለቤትነት ትርክት ሲጠፋ፣ ለክብር መቆምና መዋደቅ በጥቃቅን ሰበቦች ሲጠለሽ፣ ሲጣልና ሲቀበር፤ እርሷም የእኔ ለምትለው፣ ለምትከብርበት፣ ለምትከበርበት፣ ለምትጠበቅበት፦ ሰውነቷ፣ ንጽሕናዋ፣ ሥነ-ምግባሯ መቆም አትፈልግም።
አንድም በኹነኛና ተገቢ ትርክት ንጉሡ “የእኔ” የሚለውን ግዛቱን አቅንቶ፣ አስፍቶ፣ አልምቶ ያሠለጠነበትን ትርክት አጠይመውባታልና፤
እርሷም “የእኔ” በምትላቸው በምትከብርባቸው፣ በምትከበርባቸው፣ በምትጠበቅባቸው ጸጋዎቿ ሠልጥናባቸው ጽድቅ አትፈጽምባቸውም፦ አግብታ፣ አርግዛ፣ ወልዳ፣ አሳድጋ ቤተሰብ አትመሠርትባቸውም፣ ማኅበረሰብ አትገነባባቸውም፤
ለምን?
ለዚያ የሚያበቃን ትርክት እርሱም ክብርን ከአባቶቿ ታሪክ አላገኘችምና! ለዚያ ለሚያበቃ ክብር በጀግንነት የተዋደቁት አባቶቿ ታሪክ እሴቱ ተጥላልቶ፣ ጠልሽቶ በአእምሮዋ ናላ፣ በእውቀት ሰሌዳዋ ላይ ተስሎባታልና ከየት ታመጣዋለች።
ስለ ክብሩ በጀግንነት የተዋደቀውን አባቷን፣ አያቷን፣ አርበኛውን፣ አባወራውን “ስሕተት-ድክመቱን” ፈልገው፣ ከቅዱሳኑ ጋር የነበረውን ፍጥጫ አድምቀው፣ ግጭት-አለመስማማታቸውን አጉልተው ጽፈውላታልና ለክብሩ መዋደቁን ትረሳዋላች፤ አንድም ትንቀዋለች፤ የሚዋደቅለት ክብር እንዳለው እንኳ ትጠራጠረዋለች።
ሸፍጡ(ሴራው) ይህ ነው!
ለትውልዱ በከሸፈ ታሪክ፣ የተወላከፈ የሞራል ሚዛን ሰጥቶ፤ የዛሬ አምስት መቶና አንድ ሺህ ዓመታት በፊት ጀብድ ፈጽሞ ያለፉትን አባቶቹን ደርሶ በአጉል መንፈሳዊነትና ዘመናዊነት ታጅሮ እንዲወቅስ፣ እንዲከስና ከታሪካዊ-እሴታቸውም እንዳይማር የማይማርም “ልባልባ” ማድረግ ነው።
🚨 አደጋው ታዲያ ምን ብትማር(ዓለማዊም መንፈሳዊም ትምህርት) እና ብትዘምን የክብር ትርጉሙ የተምታታባት፣ የሞራል ሚዛኑ የተዛነፈባት፣ ትውልድን ከማስቀጠል ይልቅ በመብትና ነፃነት ስም ዘሯን አምክና የምታስቀር የምታጠፋም ሴት ማፍራት ይኾናል።
በዚህም “የማንም ሳትኾን የትም ለማንም” በቢላሽ ለከንቱ የምትወድቅ፣ ለራሷ ክብር የሌላትና ቤተሰባዊ አንድነቷን፣ ውሕደቷን፣ መሠረቷን የምታፈርሥ “ልባልባ” ትኾናለች።
ይህ በንጉሡ የታሪክ ግርማ ላይ የተሰነዘረ “የትርክት መዶሻ” ትውልዱን ያለ ክብር እንዲጠፋ፤ አንድም ክብሩን በራሱ እንጅ እንዲያጠፋና ክብረቢስ የኾነ ከእንሰሳት ያልተሻለ የሕይወት ሳይኾን የጥፋት መንገድ እንዲከተል ያበረታታዋል።
፩.፬ ስልብ ጃንርባ ትውልድ መፍጠር
በዚህ ደግሞ ደራሲው መንፈሳዊነትን እንደ “ማደንዘዣ”፣ እንደ “ታሪክ ማፍረሻ” መሣሪያ በመጠቀም፣ ትውልዱ ለእርሱ ከሚስማማው፣ ከሚመስለውና እንደ ማኅበረሰብ ከሚያኖረው የንጉሡና የሕዝቡ ሕይወት ይልቅ በማይኖርበት፣ በማይመጥነውና በመካንነት በሚያጠፋውም የባሕታዊነት ሕይወት ውስጥ በአጉል መንፈሳዊነት ስም አመጻድቆ እንዲሸሸግ በማድረግ የአባወራነትና የአርበኝነት ኃይሉን፣ ወኔዉን፣ ልቡን በራሱ እጅ እንዲሰልበው ያደረገበት መንገድ ነው።
የመናኙ ታሪክ ለሕዝባዊው አይጠቅምም ባይባልም በይበልጥና በተለይ ግን ምናኔን ፈልጎ፣ ከሕጋዊነት ተለይቶ አምላኩን ማገልገል ለሚፈልገው ይኾናል።
ነገር ግን የመናኙን ታሪክ በዚያም የሚገኘውን እሴት ለሕዝባዊው አድምቆ ማቅረቡ፣ በተለይም ደግሞ ለዓለማዊው አርአያ፣ አብነት፣ ምሳሌ ከሚኾኑት ነገሥታት (Archetype) ጋር አጋጭቶ ማቅረቡ ትውልዱን፣ ማኅበረሰቡን፣ ቤተክርስትያንን ተተኪ፣ ተረካቢ እናም ተጠያቂ፣ ተማጋች፣ ተቆርቋሪ ማሳጣት፣ በቁሙ መስለብም ነው።
እንዲህ ያለው ትርክት ትውልዱን በሁለት ዓለማት መካከል እንዲቀደድ፣ እንዲሰነጠቅ ያደርገዋል። በኑሮው ንጉሡንና ሕዝቡን መስሎ በዓለም እያለ፣ በትርክቱ ግን “መናኙን ነኝ” ብሎ እንዲያስብ እንዲሰለብም ይደረጋል።
ይህ ደግሞ ትውልዱ በገዛ ሰውነቱ፣ በተፈጥሮውና በፈጣሪውም ላይ እንዲያምጽ፣ ራሱንም እንዲጠላ ሲያደርገው፤ ጽድቅ እንዲፈጽምበት፣ መራራዋ ዓለምን እንዲያጣፍጥበት የተሰጠ ጸጋውን፣ ወንድነት መክሊቱን ኮንኖ እንዲጠላው፣ እንዲጥለውና እንዲቀብረውም ይጋብዛል።
🚨🚨 ይህም ሁሉ በአጉል መንፈሳዊነት ሰበብ ሲፈጸም፤ በውጤቱም ለቤተሰቡና ለሀገሩ የማይበጅ፣ ለክብሩ የማይቆም፣ ነገር ግን በመንፈሳዊ እብሪት የተወጠረ፣ ራሱን ከአባቶቹ የሚሻል አድርጎ የተመጻደቀ፣ ነገር ግን ለማንም አጎብዳጅና አጎንባሽ የኾነ አልጫ ጃንደርባም መኾን ነው።
ይህ ትውልድ በተሰጠው፣ በራሱ ጸጋ መንገሥ ሲገባው፣ በሐሰት ትርክት ተሸንፎ ለባርነትና ለማኅበራዊ መመከን ይዳረጋል።
ደራሲው አባ ፊሊጶስን “ኃያል” ብሎ ሲሰይም ትውልዱን ወደ ጽድቅ ከመምራት፣ ጻድቁንም ከማክበር ይልቅ፤ በንጉሡ የታሪክ ግርማ ውስጥ ያለውን አርበኛዊ ወኔ በመስለብ፣ ልጆቹ እንዳይከተሉት ለመጣው አንባገነን ሁሉ በባርነት እንዲያድሩ የሚያደርግ ነው።
ትውልዱ በማይኖርበት የመናኝ ኃያልነት እየተመካ፣ ሊኖርበት የሚገባውን የአርበኝነት አባወራነቱን ኃይል እንዲያጣ ሲደረግ ታሪኩም ትውልዱም ከሸፈ።
፩.፭ የምዕራባውያንና የጠላትን አጀንዳ በረቂቅ መንገድ ማሳካት
የሀገር ጠላቶች ሳይቀሩ የቀኑባቸውንና የፈሯቸውን ታላቅ ንጉሥ፣ በዚህ መልኩ በብዕር እንዲረክሱና እንዲቆረቆዙ ማድረግ ትልቅ የትርክት ስርቆት ነው።
ንጉሡ የሰሩትን የድንበር ማስከበርና የሕዝብ ነፃነት የማስጠበቅ ታላቅ ሥራ፣ በሚስት ቁጥር ሰበብ “ቅድስና የሌለው” አድርጎ ማቅረብ ለጠላት መንገድ የሚጠርግ “የውስጥ ክህደት” ነው።
ይህም ትውልዱን ያለ አርበኛዊ ኩራትና ያለ መሪ “አልጫ” ኾኖ እንዲቀር በማድረግ ለባርነት ያመቻቸዋል።
ባጠቃላይ፣ ደራሲው ይህን ግጭት መሣሪያ በማድረግ የፈጠረው ትርክት ታሪክን ለትውልድ ግንባታ ከመጠቀም ይልቅ፣ ታሪክን ለማክሸፍና ትውልዱ ምን ቢማር “ልባልባ” አድርጎ ለማስቀረት የታለመ “የሐሰት ትርክት” ነው።
ወደ ሁለተኛው ትችቴ ስሄድ
በ፪ኛው ደራሲው “የሚስት ብዛትን” የነገሥታቱን ቅድስና መወሰኛ አድርጎ ማቅረቡን እናያለን።
0 Comments