ክፍል አራት
ማሳሰብያ ፦ ይህን ትምህርት ስታነቡ ውስጣችሁ ሊበሳጭ እና ዓይነ ጥላው ሊያጉረመርም ስለሚችል በትዕግስት አንብቡ፡፡
መፍትሔ በመጨረሻው ክፍል ይቀርባል።
ወዳጆቼ በክፍል ሦስት ዓይነ ጥላ ከሰው ጋር እንዳንግባባና በመጨረሻም ትዳር አልባ፣ እጮኛ አልባ ብሎም ሰው አልባ አድርጎ ሊያስቀርን እንዴት እንደሚሞክር አይተናል፡፡ አሁን ደግሞ በዚህ ክፍል እኛ ላይ እና ሰው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ጥላቸውን በምን ዓይነት የተንኮል ስልት እንደሚዋጋን እናያለን፡፡ አምላከ ቅዱሳን ምስጢሩን ይግለጥልን!
ተወዳጆች ሆይ አጋንንት ብዙ ነገራችንን ሊያበላሽ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ‹‹ለምን እና እንዴት›› ብሎ የሚያጨቃጭቀን ጉዳይ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አሁን ሁላችንም በምድር ላይ የምንኖረው ሕይወት በአጋንንት ቀድሞ በሰማይ ቤት የተበላሸ ሕይወት ነው፡፡ በሰማይ ቤት በሰይጣን የተሰበረ ሕይወት ነው በምድር ተሰነጣጥቆ የምንኖረው፡፡ በምድር የምንኖረው በእግዚአብሔር ሳይሆን በሰይጣን በኩል የመጣ የውድቀት ኑሮአችንን ነው፡፡
ወዳጆቼ የዓይነ ጥላ አጋንንት በክፋቱ በተንኮሉ በእግዚአብሔር የተጠላ ስለሆነ እኛን እጅጉን ይጠላናል፡፡ ዓይነ ጥላ እኛን በሁለት መንገድ በሰዎች ዘንድ እንድንጠላ ያደርገናል፡፡ አንደኛው እኛ ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ግንባራችን ላይ፣ዓይናችን ላይ፣ፊታችን ላይ ሆኖ ለሰዎች ፊታችንን በማየት ብቻ አስከፊና የተንኮለኛ ሰው ገጽታን አስመስሎ በማሳየት እንድንጠላ ያደርገናል፡፡
ይህ ማለት ሁለት ማንነት ይዘን እንድንታይ ያደረገናል፡፡
> ደግ ሆነን ንፉግ ሆነን እንድንታይ፤
> መልካም ሰው ሆነን ክፉ ሰው ሆነን እንድንታይ፤
> ጨዋ ሆነን ባለጌ ሆነን እንድንታይ
> ለአንደበታችን ለከት ያለን ሆነን ሳለ ወረኛ አድርጎ ለሰው ያሳየናል፡፡
> ትእግስተኛ ሆነ ሳለ እሳት የላሰ ነገረኛ አድርጎ ያሳየናል፣
> ሐቀኛ ሆነን ሳለን ከሰው ሙልጭ ያለ ሌባ አድርጎ ያሳየናል፡፡ ወዘተ
በአንድ ሰውነት ሁለት ማንነትን ይዘን እንድንታይ ያደርገናል፡፡ ይህ ሁሉ ዓይነ ጥላው የፊታችንን ገጽታ ለሰው በማሳየት በግምት እንድንጠላ የሚያደርግበት ክፉ ሴራው ነው፡፡
ሁለተኛ ሰዎች ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ያለ ምክንያት ከመሬት ተነስተው ስለ እኛ ምንነት ምንም ሳያውቁ እንዲጠሉን፣ በሰዎች ልቡናና ህሊናው ውስጥ ክፉ ሰው እንደሆንን በማሳሰብና የፊት ገጽታችንን ብቻ በማየት እንዲጠሉን ያደርገናል፡፡ እኛ ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ሰዎች ከውጭ ሲያዩን ግንባራችንን ብቻ በማየት የክፉ ሰው ምስል ያያሉ ወይም ክፉ ሰው መስለን እንድንታያቸው ያደርጋል፡፡ ለአንዳንዱ ደግሞ ከመኮሳተሩ የተነሳ ግንባሩን የተሰበሰበ እና የተከሰከሰ ፊት አድርጎ ያሳየዋል፡፡ ለሌሎቹ ደግሞ ነገረኛ እና ተናጋሪ ሰው የሚመስል ምስል ያሳያቸዋል፡፡ ሰዎች ቀርበውን ካላዩን በስተቀር እኛ ሁሌም ለሰዎች ክፉ እና መልካምነት የሌለን ይመስላቸዋል፡፡ ለዚህም ነው ሰዎች ቀርበው ሲያዩን በውጭ ስለ እኛ ያላቸው አመለካከት በበጎ የሚቀየረው፡፡
ዓይነ ጥላው ይህንን የሚያደርገው የነገን ሕይወታችንን ለማጠየፍ ነው፡፡ በተለይ ወንዶች እና ሴቶች በወጣትነት ጊዜያቸው ዓይነ ጥላቸው በእድሜ እኩዮቻቸው ዘንድ እንዲጠሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በነገ በእጮኝነት በትዳር ሕይወታቸው ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድርባቸዋል፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ በሰውነታችን ላይ ለምሳሌ የጥርስ መግጠጥ፣ የአይን ፈጠጥ የማለት ነገር ካለ የእኛ እና ሰው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ አግንኖ ለሰው እንድንታይ ያደርገናል፡፡ በተለይ በተፈጥሮና ከጊዜ በኃላ በመጣ ምክንያት የቁመና አለመስተካከል ካለብን ለሰዎች እንደተንሻፈፍን፣ እንደተንጋደድን አድርጎ ያሳያቸዋል፡፡ ሲያዩን አንጥማቸውም፡፡
ወዳጆቼ ሰዎች ሳይሆኑ እነሱ ላይ ያለው ዓይነ ጥላ እንደሆነ የሚጠላችሁ ለማወቅ ለእነዛ ሰዎች ምንም ብታደርጉላቸው፣ ውለታ ብትሰሩላቸው፣ በችግራቸው ጊዜ ብትደርሱላቸው፣ ማንም የማያደርግላቸውን ነገር እንኳን ብታደርጉላቸው ለጊዜው የውሸት ምስጋና ያቀርቡላችኃል እንጂ ውሎ ሳይከርም ጥላቻቸውን ይገልጹላችኃል፡፡ ብትሰጡ፣ ብታበሉ፣ ብታጠቱ አትመሰገኑም፡፡ ለሰዎቹ ግዴታችሁ ሁላ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ይህ የዓይነ ጥላው ጠባይ ‹‹ውይ ከሰውስ አውሬ ይሻላል›› ብላችሁ ከበጎ ምግባር እናንተን ለማራቅ ይጠቀምባችኃል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም እጮኛሞችን ተዋደው ብዙ ነገር ውስጥ ገብተው ሲፋቀሩ ከሁለት ያንዳቸው ዓይነ ጥላ ቀድሞ በፍቅር አይን ዓይቶ ልብ ያላለውን ነገር ለምሳሌ መልክን፣ ቁመናን፥ ዳሌን፣ ቅንድብን፣ ጸጉርን ገልብጦ በማሳየት ‹‹ለካ ይህ ነገርዋ አያምርም፣ ለካ ይህ ነገሩ አይማርክም›› እያስባለን የወደድነውን ያፈቀርነውን ሰው እንድንጠላ የጥላቻ ምስሎችን ያሳየናል፡፡ ለዚህም ነው በፍቅራቸው የተመሰከረላቸው እጮኛሞች ለእርቅ በማይመች መንገድ የሚጣሉት፣ የጀመሩትን የፍቅር ሕይወት ወደ ትዳር ሳይቀይሩት ከመንገድ የሚቀሩት፡፡
ያለ አንዳች ምክንያት በሰዎች ዘንድ የሚጠሉ ሰዎች ሰው ሁሉ የሚወዳቸው ስለማይሰማቸው የዝምታ፣ የድብርት፣ የጭምተኝነት ባሕርይ ይንጸባረቅብቻዋል፡፡
የራሳችን ዓይነ ጥላ በራሳችን እናት አባት ባንጠላም ከሌሎች ወንድም እህቶቻችን በታች ያለመወደድን ነገር በእኛ ላይ ያሳያል፡፡ ዓይነ ጥላው በቤት ውስጥ አንድ ስም ያሰጠንና ሁሌም የመጥፎ ሰው አርአያ ተደርገን እንድናድግ ያደርገናል፡፡ በዚህ መልኩ በልጅነት የጠመደን ዓይነ ጥላ ከፍ ስንል ግልጽ ውግያውን በገሀድ ይጀምራል፡፡ እኛም ሰዎች እንጂ ዓይነ ጥላው እኛ እንድንጠላ እንዳደረገን ልብ አንልም፡፡
በሰው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ደግሞ በሁለት መንገድ እንድንጠላ ያደርገናል፡፡ አንደኛ ሰውዮው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ሲያየን ደመ ግቡ አንሆንለትም ስለዚህ ይጠላናል፡፡ ሁለተኛ ሰው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ እኛ ጋር ያለውን የእግዚአብሔር ጸጋ፣ ሞገስ፣ የጸሎት በረከት፣ ረድኤት እና የተፈጥሮ ጸጋ ለምሳሌ እውቀት፣ መግባባት፣ ከሰው ጋር ባለን መዋደድ ወዘተ በማየት ይጠላናል፡፡ በእነዚህ ስጦታችን የሚጠላን ዓይነ ጥላ እሱ ጠልቶን በሰዎች ዘንድ የበለጠ እንድንጠላ ሰፊ ሥራ ይሠራል፡፡
ለምሳሌ ያለ ስም ስም እንዲሰጠን ያደርጋን፣ ያልሠራነውን ሠራችሁ ተብለን ጠብ ሊመጣብን ይችላል፡፡ ከወንድ ወይም ከሴት ጋር በታየን ቁጥር እንደ ዘማዊ እንድንቆጠርና ዘሙተዋል ብሎ ሊያስወራብን ይችላል፡፡
ሰው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ መልካም ንግግራችን ወደ መጥፎ ይቀይራል፡፡ መፍትሔ ብለን ሐሳብ ብናፈልቅ ‹‹ኤጭ›› እያለ ጥላቻውን የእኛን ነገር በመናቅ ያሳየናል፡፡ በዚህም ከሰው ጋር በፍጹም መግባባት እንደማንችል አድርጎ ሊያሳምነን ይሞካራል፡፡ እኛ የምንናገረው ማር የሆነ ነገር ዓይነ ጥላ ላለበት ሰው ሬት ሆኖ ንግግራችን ይጎመዝዘዋል፡፡ በዚህም እኛን በማበሳጨት መልካም ነገሮችን ለማሳጠት ይጠቀምበታል፡፡ ይህ የእጮኛሞች እና የባለ ትዳሮች አንዱ ዓይነ ጥላዊ በሽታቸው ነው፡፡
አንዳንድ ሰዎች ለራሳቸው ማወቅ እስኪሳናቸውና የግራ ግራ እስኪገባቸው ድረስ በሰዎች ዘንድ ይጠላሉ፡፡ እነሱም የተወዳጁትን ሰው ‹‹ቆይ ግን እኔ ክፉ ነኝ›› እያለ ክፉው ዓይነ ጥላ እንዲጠሉ እንዳደረጋቸው ሳያውቁ ሰውን ይጠይቃሉ፡፡ ዓይነ ጥላው ሲከፋብን ሰዎች ገና ቀርበው ባሕርያችንን ሳያውቁ፣ድምጻችንንም በወል ሳይለምዱ ዓይነ ወኃችንን በማየት ብቻ ይጠሉናል፡፡ ወዳጆቼ በእነዚህ ክስተቶች ዓይን ጥላችንና የሰው ዓይነ ጥላ ነው የጥላቻውን ጥግ የሚያሳን፡፡
አንድ ሴት ወንድየው በስንት ልመና ጓደኛ ካልሆንሽኝ ብሎ ለምኗት እጮኛሞች ይሆናሉ፡፡ በጣም ተቀራርበው፣ ተላምደው፣ ተዋደው ባልታውቀ ምክንያት ይጠላታል፡፡ አንድ ሴት በስንት ልመናና ጉትጎታ ለአንድ ወንድ እጮኛ ትሆናለች፡፡ አንዳንዶቹ መዋደድ ሳይጀምሩ በመጀመርያ ቀን ቀጠሮ ሲገኛኙ ዓይነ ጥላዋ እጮኛዋን ያስጠላትና ግንኙነታቸውን ያቋርጣል፡፡ ሌሎቹን ርቀው ከተጓዙ፣ ብዙ ነገር ከተማዘዙ በኃላ አቃቂር እያወጣች፣ ነገር እየፈለገች፣እየተነታረከች እየወደደችው እንድትጠላው ብሎም እንድትለየው ዓይነ ጥላዋ ውስጥ ውስጡን ይሠራና ያለያያታል፡፡
አንዳንድ ሴቶች አሉ ገና ወንድ ሲያዩ ‹‹ሲያስጠላ›› ብለው ጥላቻቸው እንደ ሕፃን ልጅ ቅርሻት ይሆንባቸዋል፡፡ ከጥላቻቸው የተነሳ እንኳን ለማናገር ለማየት አይፈልጉም፡፡ ግን ዓይነ ጥላቸው የነገን የፍቅር ብሎም የትዳር ሕይወት ከወዲሁ መገርገር፣ማጨናገፍ እንደጀመረ አያውቁም፡፡
ወንዶቹም አንዲትን ሴት ይወዱና የሚፈልጉትን ነገር ከእሷ ካገኙ በኃላ ዓይነ ጥላቸው እንዲጠላት፣እንዲንቃት፣ምቾት እንዳልሰጠችው በማሳሰብ እንዲተዋት ያደርጋቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ የሚገለጠው ዓይነ ጥላ ወንዶችን ሴት አውል ያደረጋቸዋል፡፡
እጅግ የሚገርመው ደግሞ ተዋደው የተጋቡ ባለትዳሮች ደግሞ ባል ወይም ሚስት ድንገት ባልዋን መጥላት ይጀማራሉ፡፡ የሚያሳዝነው የጥላቻቸውን ምክንያት አያውቁትም፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ጠልተው የጥላቻቸውን ምክንያት ለማጽናት ጠብና ንትርክ ይፈልጋሉ፡፡ ይህም ዓይነ ጥላቸው ባለ ትዳሮችን ለመለያየት አሳማኝ ምክንያት ለመፈለግ ነው፡፡ የቀድሞ ፍቅር፣ክብር እየቀነሰ ጥላቻቸው እያየለ ይሄዳል፡፡ባለ ትዳሮችን ደግሞ በስንት ዓመት የእጮኝነት ጊዜያቸው ያላዩትን ነገር በትዳር መሃል ዓይነ ጥላቸው አጨልሞ ገልብጦ ያሳያቸል፡፡
አንዳንዱ ባለትዳርማ ቀድሞ አንሶላ ተጋፎ ያገባና በትዳር መኖር ብሎም ሲወልዱ የሚስቱ ውበት፣ቁመና፣የሰውነት ቅርጽ የእሱን ልጆች ወልዳ እንደተበላሸች፣ሁሉን ነገርዋን ለእሱና ለልጆችዋ ስትል እንዳጣች ያዘናጋቸውና ‹‹ለካ እሷ እንዲህ ናት›› በማለት ሚስቱን መናቅ ይጀምራል በዚህም ወደ ውጭ ማየት እና መመኘት ብሎም መዘሞት ይጀምራል፡፡ ዓይነ ጥላው በትዳራቸው ሲቀና የሚስቱን ነገር በሙሉ ገልብጦ በተቃራኒ መልኩ ያሳየዋል፡፡ ሴቶቹም የባላቸውን ነገር እንደዛው ያያሉ፡፡
እጅግ አደገኛው የዓይነ ጥላው ተንኮል ደግሞ የእጮኛችንን፣ የትዳር አጋራችንን እኛ በፍቅር ዓይን ተሰውሮብን ያላየነውን ቦታ ያልሰጠውን የአንዱ መናጢ ዓይነ ጥላ በቤተሰብ፣በጓደኛ ላይ ተጭኖ ይመጣና ‹‹እጮኛህ፣ሚስትህ ለካ እንደዚህ አላት፣ይህ ነገርዋ ለካ እንደዚህ ነው›› በማለት የምንጠላበትም ነገር ያሳየናል፡፡ እኛም ስንት ዓመት ያላየነውን ነገር ስናይ ያኔ የዓይነ ጥላው የጥላቻ መንፈስ ይዋረሰንና የራሳችን ሰው የሆነ ነገር መጥላት እንጀምራለን፡፡
በሥራ ቦታ የራሴ የምትሉት ሰው ድገት የሚያንገፈግፍ ጥላቻ ውስጥ ገብቶ የጥላቻ በትሩን በተለያየ ነገር ቢገልጽላችሁ እሱ ሳይሆን ሰውየው ላይ ያደረው ዓይነ ጥላ ነው የሚጠላችሁ፡፡ በተለይ ‹‹ዛሬ ቤተክርስትያን ሄጄ መጣሁ›› ካላችሁማ ሰውዬው ላይ ያለው ዓይነ ጥላ ጠንቋይ ቤት ሄዳችሁ የመጣችሁ እስኪመስላችሁ የጥላቻ መገለጫውን ታያላችሁ፡፡
ወዳጆቼ የእግዚብሔርን አምላካዊ ፍቅርን እየተነገረን፣ እየተማርን ካለደግን እግዚአብሔር የሚነግስበትን የልባችን ዙፋን ላይ ዓይነ ጥላው ይቀመጥበት እና ሰዎችን እንድወድ ሳይሆን እንድንጠላ፣ እንዳናምን፣ እንድንጠራጠር ብሎም ሰውን እንዳናከብር ንቀቱን ጥላቻውን በእኛ ይገልጣል፡፡ እኛም በራሳችን ባልሆነ ግን በዓይነ ጥላው መሰሪ ባሕሪ ሰው ጠልተን በሰው እንድንጠላ ያደርገናል፡፡
ወዳጆቼ የአንዳንዱ ዓይነ ጥላማ ገና ፊቱን ስታዩት ተዘፍዝፎ፣አኩርፎ የምታዩት ነው የሚመስለው፡፡ የደስታ የፈገግታ ፊት አያሳያችሁም፡፡ ይህም የሚሆነው ዓይነ ጥላው ሰውዬውን በሰዎች ዘንድ ለማስጠላት፣እንዲጠጉት ላለማድረግ የሚጠቀምበት ግልጽ ወግያው ነው፡፡
ፍቅርን ሳይሆን ጥላቻን፣ ሰብአዊ ከብርን ሳይሆን ስድብን፣ማክበርን ሳይሆን ሰው ማዋረድን፣ መታዘዝን ሳይሆን እንቢኝን፣ መታገስን ሳይሆን የልብን መናገርን፣ ማለፍን ሳይሆን መለፍለፍን መገለጫው ባደረገ ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ውስጥ አድገን ዓይነ ጥላው እነዚህን መጥፎ ገጽታዎችን እያላበሰን እያዋረሰን አድገን እኛም በዓይነ ጥላው ባሕርይ ተቀርጸን ብንወጣ ምን ይደንቃል?
ከቤተሰባችን ጸጋን ሳይሆን ቁጣን ወርሰን፣ መዋደድን ሳይሆን መጠላላትን እያየን አድገን ዓይነ ጥላው የጥላቻው ማስፈጸሚያ ቢያደርገን አያስደንቅም፡፡ ከእግዚአብሔር ሰማያዊ በረከት ርቀን አድገን መናፍስቱ በሕይወታችን፣በባሕርያችን ቢሰለጥኑ አይገርምም፡፡
ወዳጆቼ ሰው ቢጠላችሁ አትደነቁ፡፡ እግዚአብሔር ብቻ አይጥላችሁ፡፡ እግዚአብሔር ጥላቻ ለባሕሪው አይስማማውም ግን እግዚአብሔር በመልካም ጠልቷል፡፡ ‹‹ያዕቆብን ወደድሁ ዔሳውን ጠላሁ›› ብሏል፡፡ በእግዚአብሔር ዘንድ መጠላት የነበረበት ያዕቆብ ነበር፡፡ ምክንያቱም የወንድሙን የዔሳውን በረከት በማታለል ወስዷልና፡፡ ስለዚህ የእግዚአብሔር በረከት የሚገኘው በብልጠት በማታለል ሳይሆን በመልካምነት በበጎ ሥራ ነው፡፡ ግን እግዚአብሔር ‹‹ያዕቆብን ወደድሁ ዔሳውን ጠላሁ›› ማለቱ ለሰው ልጅ የሰጠውን ተስፋ በበኩሩ በዔሳው ሳይሆን በያዕቆብ በኩል ለማስተላለፍ እንደ ፈቀደ ለማመልከት ነው፡፡ ት.ሚል 1÷2‚ ሮሜ 9÷13‚ ሉቃ 1÷33
ስለዚህ በሰዎች ዘንድ መጠላት በእግዚአብሔር ዘንድ የመጣላት ምልክት አይደለም፡፡ በሰዎች ዘንድ መወደድም በእግዚአብሔር ዘንድ የመወደድ መሥፈርትም አይደለም፡፡ ስለዚህ በየትኛውም ሕይወታችን የእኛ እና በሰዎች ላይ ያለው ዓይነ ጥላ እንድንጠላ ሊያረገን ስለሚችል ሞራላችን ሊነካ ብሎም እጅጉን ሊከፋን አይገባም፡፡ በጸሎት ከበረታን በጥላቻ የዘመተብን ዓይነ ጥላ ይርቀንና እግዚአብሔር ደግሞ የመወደድን ጸጋን ይሰጠናል፡፡ ስለዚህ የጥላቻ ዓይነ ጥላ እንዲርቀን እግዚአብሔር በጸሎት ሊቀርበን ይገባል፡፡ በተሰጣችሁ ጸጋ የተጠላችሁት ደግሞ ሰው ሳይሆን ክፉው መንፈስ እንደጠላችሁ እወቁ፡፡
0 Comments