መልእክት ኀበ ሰብአ ጴንጤ

በአማን ነጸረ

(ከተመረጠው ደብተራ ወደ ጴንጤዎች የተላከች መልእክት)

በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ሰላም እላችኋለሁ! ብዬ ክብርት ነቆራዬን እጀምራለሁ ።

1.መጸለይ ጥሩ ነው፡፡ ጸልዩ! ለሀገርና በሥልጣን ላሉ መጸለይ እኛም ዘወትር የምናደርገው ነው፡፡ ቢያስተውሉም ባያስተውሉም ‹‹ሀብ ምክረ ለመኳንንተ አሕዛብ - ለሕዝብ ገዥዎች ማስተዋልን ስጥ›› ማለት አልተውንም፡፡ ጸሎት ጥሩ ነው፡፡

2. ‹‹የበኣል መሠውያ›› ለማፍረስ የሚባል አሽሙር ግን ጸያፍ ነው፡፡ ፒያሳ በመልሶ ማልማት ሲፈርስ ‹‹ጋኔን ተሰደደ››፣ የካ ሲነሳ ‹‹ጠንቋይ ጉዱ ፈላ›› ስትሉ ታዝበን ታዝበን ታዝበን አልፈናል፡፡ ድህነትን ከሰይጣን ጋር የማስተሳሰር ፍጥነታችሁ ደስ የማይል ነገር አለው፡፡ የድሮ ሚሽነሪ ለድሆች ት/ቤትና ክሊኒክ ሲሠራ እንጂ የስላቅ ስም ሲሰጥ አናውቅም! የእናንተ ተለየ! ሀገር በቀሉ ጴንጤ በቀደምት ሚሲዮናውያን ተግባር እየተኩራራ በተግባር ግን ፀረ ደሀ ሆኖ ታየ፣ ተስተዋለ እያልን እያማናችሁ ነው፡፡ የሆነ የሞራል መላሸቅ ነገር!  የእመቤታችንን ልደት በምናከብርበት ቀን፣ ያውም ፒያሳ ላይ ልደታ ካቶሊክ ካቴድራል፣ በመሀል ከተማ የሀገሪቷ መናገሻ ታላላቅ ክፍሎች ከሆነው የአንዱ (የልደታ ክ/ከተማ) መጠሪያ የሆነችው ማኅደረ ሰብሐት ቅድስት ልደታ ማርያም ባለችበት ከተማ ላይ ዕለቷን ‹‹የበኣል መሠውያ›› ምናምን ብሎ አጓጉል አሽሙር አይደብርም? ወይስ እኛም በማግስቱ ‹‹የዳንኪራ መሠውያ ማፍረሻ ጉባኤ›› ብለን እንቀጥል?!

3.የብሔር ብሔረሰቦች ቡራኬ ብሎ ነገር አሙቁልኝ አይሆንም? ስናነብ የምናገኘው ፕሮቴስታንት ከተሜነትን፣ ሜትሮፖሊታንነትን፣ ጥረትን፣ የሐሳብ ነጻነትንና ድንበር ተሸጋሪነትን የሚሰብክ ነው፡፡ ወዲህ ያለው ጴንጤ የቁንጩኒና የቡርሰማ የጎሳ ደረጃ ላይ ነውሳ! ሜትሮፖሊታን ስትሆን ብሔር ብሔረሰብ ማለት ሳያስፈልግህ ሆነህ ትገኛለህ፡፡ ካልደበረህ የእኛን ጥምቀት ውሰደው፡፡ ስለብሔር አናነሳም፣ ከለሩን ግን መሬት ላይ በተግባር እናሳያለን፡፡ እንደዛ ነገር ተጫወቱ! ጵንጥጥናን ከልብስ አራዳነት የተሻገር የከተሜ ቀለም አላብሱት፡፡ በእርግጥ ለኪነ ጥበብ ጽዩፍና ፈሪሳዊ አቀራረባችሁ የባሕል ቀራጺነት ላይ ለመድረስ ገና ይታገላችኋል፡፡ ‹‹ካልቸር ሜክ›› የማድረግ አቅማችሁን በራሳችሁ ጊዜ ገድላችሁታል (በቤታችን ያሉ ነሆለሎች እንዳሉ ሆነው በእርግጥ ይህ ሽሽታችሁ ለእኛ አድቫንቴጅ ነው)፡፡  ድብን ይበል ጠላቴ! በሚል ወቀጣ ብቻ ባሕል ልተቀርጽ እንደማትችል ብነግርህ እንዳትቀየመኝ! በሚሲዮናውያን ‹‹ሚድል ክላሱን›› ይዞ በጥብቅ የሥራ ዲሲፒሊን የከተማ ባሕል ይቀርጻል የተባለው ጴንጤ በሚራክል መኒ የሚናውዝ የጩሉሌ መንጋ መሆኑ በውኑ ድቀት አይደለምን? በዚህ አካሔድ ወንበሩን የያዘ ዘመድ ቢኖራችሁም፣ ግንባር ግንባር የከተማ ቦታ ብትይዙም ገዥ መሆን አትችሉም፡፡ ክርስትና በታሪኩ በከተማ መስፋፋት የጀመረ ሃይማኖት በመሆኑ ለ‹‹ዳይቨርሲቲ›› እንግዳ እንዳልሆነ ታውቃላችሁ፣ እናውቃለን፡፡ እያወቃችሁ በፖለቲካ ቅኝት ‹‹ቡርሰማ ቁርጠማ›› ለምን እንደምትጫወቱ በእውነቱ አልተገለጠልንም፡፡  የብሔር አወቃቀርና ውጥረት ሥርዓታዊ በሆነበte ሀገር ላይ የጴንጤው ሚና አብሮ ማጋጋልና ማነፈስ መሆኑ የምር ያሳዝናል! የብሔር መሳሳብና መጓተት ሰብአዊ ቀለሙን እንዳያጣ ብዙ ማድረግ ስትችሉ እዛው የምትርመጠመጡት ነገር በጣምኮ ይደብራል!

4.ፖለቲካዊ አጀንዳ ሲነሳ መናጆ የምትሆኑት ነገር ደሞ ከቃላቱ ጀምሮ አይመስጥም፡፡ በኢህአዴግ ጊዜም ነውኮ! ተዉ! 

እኔ ግን የቡራኬ ሥልጣን ስላለኝ እባርካችኋለሁ፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ! 

(መልሶ ተባረክ የሚለኝ ጴንጤ አልተማረም! እኛ ደባትር እንባርካለን እንጂ አንባረክም!)

Post a Comment

0 Comments