ጠያቂ ትምህርት ክፍል ፲፮
✍ ዮሴፍ ኢትዮጵያ | አልፋና ዖሜጋ ዘተዋሕዶ
ኢየሩሳሌም በግርግር ተውጣለች። ከተማዋ በፋሲካ በዓል ተሳላሚዎች ተሞልታለች። በዚህ መካከል ድንገተኛ ጩኸት ተሰማ፤ ይህ ጩኸት ግን ተራ የደስታ ድምፅ አልነበረም። "ሆሳዕና! ሆሳዕና! ሆሳዕና!" የሚል ድምፅ ከተማዋን አናወጣት። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ውርንጫ ላይ ሆኖ ሲመጣ፣ ሕዝቡ ልብሱን በመንገድ ላይ እያነጠፈ፣ ዘንባባ እያወዘወዘ ይጮኻል።
"ሆሳዕና" የሚለው ቃል "ሆሼዕናህ" ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣ ሲሆን፣ ትርጉሙም "እባክህ አሁን አድን!" ማለት ነው ። ሕዝቡ "አድን" ብሎ ሲጮኽ፣ ጌታ እንዲያድናቸው የፈለጉት ከሮማውያን የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነበር። እነሱ ምድራዊ ነጻ አውጪ ይፈልጋሉ። ጌታ ግን በአህያ ላይ የተቀመጠው ከዚህ እጅግ የላቀ "የማዳን" ምስጢር ይዞ ነው። እሱ ሊያድናቸው የመጣው ከሮማውያን ሳይሆን ከዲያብሎስ ባርነት፣ ከኃጢአት እስራትና ከዘላለም ሞት ነበር።
ይህ ጩኸት በብሉይ ኪዳን መዝሙረ ዳዊት ላይ "አቤቱ እባክህ አሁን አድን" ተብሎ የተተነበየው መዝሙር ፍጻሜ ነው ። ሕዝቡ ሳያውቀው፣ የዓለም ቤዛ መሆኑን እየመሰከረ ነበር።
ቤተ ክርስቲያናችን እንደምታስተምረው፣ ሆሳዕና የሰው ልጅ ለዘመናት በጨለማ ውስጥ ሆኖ ያቀረበው የድረሱልኝ ጥሪ ማሳያ ነው።
"ሆሳዕና" ማለት የሰላም ጥሪ ነው። ዓለም በሁከት፣ በክፋትና በገንዘብ ፍቅር በታወከችበት በዚህ ዘመን፣ ጌታ ወደ ከተማችን (ወደ ልባችን) እንዲገባ የምንማጸንበት ቃል ነው።
ጌታ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው "ሊሞት" ነው። እውነተኛው ማዳን (ሆሳዕና) የሚፈጸመው በአህያ መቀመጥ ላይ ሳይሆን በቀራንዮ መስቀል ላይ መሆኑ የታሪኩ ትልቁ ምስጢር ነው ።
ታሪካዊ ጥናቶችና የቤተ ክርስቲያን ትውፊት እንደሚያሳዩት፣ በዚያች ዕለት በኢየሩሳሌም ሁለት ተቃራኒ ሰልፎች ነበሩ። ከከተማይቱ ምዕራብ በኩል የሮም ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ በታላቅ የጦር ፈረስ ላይ ተቀምጦ፣ በሠረገላና በታጠቁ ወታደሮች ታጅቦ ገባ። ይህ ሰልፍ "የሮም ኃይል አይበገሬ ነው፤ ሕግን የምናስከብረው በሰይፍ ነው" የሚል የኩራትና የፍርሃት መልእክት ነበረው።
በተቃራኒው፣ ከከተማይቱ ምሥራቅ በኩል የሰላሙ ንጉሥ በደካማዋ አህያ ላይ ተቀምጦ፣ በሕፃናትና በገበሬዎች ዝማሬ ታጅቦ ገባ። ጲላጦስ ኃይልን ሲያሳይ፣ ጌታ ግን ትሕትናን አሳየ።
ለምን አህያ ተመረጠች የሚለውን እንመልከት?
✨ የጦር ፈረስ ወይስ የአህያ ሰላም፦ በጥንቱ ዘመን ነገሥታት ለጦርነት ሲወጡ በፈረስ ላይ ይቀመጣሉ፤ ለሰላም ሲመጡ ግን በአህያ ላይ ይቀመጣሉ። ጌታ በአህያ ላይ መቀመጡ "እኔ የመጣሁት ዓለምን በሰይፍ ልወር ሳይሆን በፍቅርና በሰላም ልገዛ ነው" የሚል ታላቅ ምስጢር አለው።
✨ ዝቅተኝነትና ትሕትና፦ አህያ በሰው ዘንድ እጅግ ዝቅተኛና ዋጋ እንደሌላት የምትታይ እንስሳ ናት። የሰማይና የምድር ጌታ ግን ይህችን እንስሳ መረጠ። ይህም መንግሥቱ በምድራዊ ዝናና በታዋቂነት ላይ ሳይሆን በትሕትናና በአገልግሎት ላይ የተመሠረተች መሆኗን ያሳያል።
የኢየሩሳሌም ሕዝብ የሚጠብቀው የሮምን ቀንበር የሚሰብርላቸውን "የጦር ንጉሥ" ነበር። ጌታ ግን በአህያ ላይ ተቀምጦ ሲመጣ ሰልፉን አዩትና "ይህ ማነው?" ብለው ተገረሙ። ጌታ ለሕዝቡ የሰጣቸው የፈለጉትን "የጦር ፈረስ" ሳይሆን የሚያስፈልጋቸውን "የሰላም አህያ" ነበር።
ጌታ በአህያ የተቀመጠው አሳዶ ለመያዝ እንዲመቸው ሳይሆን፣ ሁሉም ሰው በፈቃዱና ሳይፈራ ወደ እሱ እንዲመጣ ነው—አህያ አታስፈራም። ጲላጦስ በፍርሃት ሊገዛ ሲመጣ፣ ጌታ ግን በፈቃደኝነት ሊያድን መጣ።
ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ከመግባቱ በፊት ለሁለት ደቀ መዛሙርቱ አንድ እንግዳ ትእዛዝ ሰጠ፦ "በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ፤ በዚያም የታሰረች አህያ ውርንጫዋም ከእርሷ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ" (ማቴ 21፡2)]። ደቀ መዛሙርቱ ከታላላቅ ተአምራትና ከሕመምተኞች መፈወስ ተግባር ወጥተው፣ ወደ "አህያ የመፍታት" ዝቅተኛ የሚመስል ተግባር ሲላኩ በመጠኑ ግራ ተጋብተው ሊሆን ይችላል።
የአህያዪቱ ባለቤቶች "ለምን ትፈታላችሁ?" ብለው ሲጠይቁ፣ ደቀ መዛሙርቱ "ለጌታ ያስፈልጉታል" የሚል አጭር መልስ እንዲሰጡ ታዘዋል። በቤተ ክርስቲያናችን ጥልቅ አንድምታ ትርጓሜ፣ እነዚህ "ባለቤቶች" የሰው ልጅን በኃጢአት አስረው የያዙ "ሕገ-ወጥ ጌቶች" ማለትም ሰይጣንና ክፉው ዓለም ናቸው። ጌታ "ያስፈልጉኛል" ሲል፣ የሰው ልጅ በእነዚህ ኃይላት እጅ ተይዞ እንዲቀር እንደማይፈቅድና የገዛ ንብረቱ (ፍጥረቱ) መሆናቸውን እያስመሰከረ ነው።
ታስሮ የነበረና የተፈታ ሕይወት፦
- የታሰረችው አህያ፦ በሕገ ኦሪት ተጠልፈውና በኃጢአት ታስረው የነበሩትን የእስራኤል ወገኖች (የግዝረት ወገኖች) ትወክላለች።
- ውርንጭላዋ፦ እስከዚያ ዘመን ድረስ በምንም ዓይነት መንፈሳዊ ቀንበር ያልተገሩትንና በራሳቸው ፈቃድ ይኖሩ የነበሩትን አሕዛብን ትወክላለች።
- ምስጢሩ፦ ጌታ ሁለቱንም አስፈታ። ይህም ክርስቶስ የመጣው ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን፣ መላውን የሰው ልጅ ከዲያብሎስ ባርነትና ከሞት እስራት ነጻ ለማውጣት መሆኑን ያበስራል።
ይህ ትእዛዝ ተራ የእንስሳት ርክክብ ሳይሆን፣ ሰማያዊው ንጉሥ በምድር ላይ ያወጀው "የነጻነት አዋጅ" ነው። ጌታ በአህያዪቱ ላይ መቀመጡ ለሸክም የሚከብደውን የኦሪት ሕግ መፈጸሙን ሲያመለክት፣ በውርንጭላዋ ላይ መቀመጡ ደግሞ አሕዛብን በወንጌል ቃል መግራቱን ያሳያል። ዛሬም ጌታ በሕይወታችን ያሉትን "እስራቶች" እንዲፈቱ ትእዛዝ እየሰጠ እንደሆነ አትርሱ። ግን ፈችና ተፈች ያስፈልጋል ። ታዛዥ ያስፈልጋል ።
በዚያች ሰዓት ኢየሩሳሌም በታላቅ የደስታ ማዕበል እየተናወጠች ነው። የሕፃናት ጩኸት፣ የዘንባባ ዝንጣፊዎች፣ "ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ" የሚለው ዝማሬ አየሩን ሞልቶታል። በዚህ እጅግ ደማቅና ንጉሣዊ በሆነ የአቀባበል ሥነ ሥርዓት መካከል ግን አንድ ያልተጠበቀ ውጥረት ተፈጠረ። የሰልፉ መሪ የሆነው ንጉሥ ፈገግ አላለም፤ ይልቁንም መለኮታዊው ፊቱ በዕንባ ረጠበ።
ሕዝቡ "ይህ ማነው?" እያለ በሚገረምበትና በደስታ በሚቦርቅበት ሰዓት ጌታችን ለምን አለቀሰ? (ሉቃ 19፡41)። አባቶቻችን ይህንን ዕንባ በሁለት ጥልቅ ምስጢራት ይተረጉሙታል፦
፩) የመጎብኘትን ዘመን አለማወቅ፦ ጌታችን ያለቀሰው ለኢየሩሳሌም ከተማና ለሕዝቧ ነው። "የመጎብኘትሽን ዘመን አላወቅሽምና" በማለት የከተማይቱን የጥፋት ዘመን (በሮማውያን እጅ የምትጠፋበትን ጊዜ) አስቀድሞ በመመልከቱ በጥልቅ ሐዘን ተሞላ። ይህም አምላክ ለፍጥረቱ ያለውን እጅግ የላቀ ርኅራኄና አገራዊ ፍቅር ያሳያል።
፪) የጩኸቱ ተለዋዋጭነት፦ ሌላው ምስጢር ጌታችን የሰውን ልጅ ጠባይ ጠንቅቆ ማወቁ ነው። ዛሬ "ሆሳዕና" ብለው ዘንባባ የሚያነጥፉት እጆቻቸው፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ (በዕለተ ዓርብ) "ይሰቀል" ለማለት እንደሚነሱ፤ ዛሬ የሚያወድሱት አንደበቶቻቸው ነገ እንደሚሳደቡ አስቀድሞ አውቋል።
መለኮታዊው ፍቅር-
በዚህ ዕንባ ውስጥ የሚታየው ትልቁ ትምህርት የጌታችን "ፍቅረ ሰብእ" (የሰው ልጅ ፍቅር) ነው። የሚሰቅሉትን ሰዎች መከራ እያሰበ ያለቀሰ አፍቃሪ ንጉሥ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን አምላክን እንደ "እብድ አፍቃሪ" የምትመስለው በዚህ ምክንያት ነው—ክህደታችንን እያወቀ፣ ለፍቅራችን ሲል ዕንባን እያፈሰሰ ወደ ኢየሩሳሌም (ወደ ሞቱ) ገባ።
ሆሳዕና የድል ቀን ብቻ ሳይሆን፣ የንጉሡን ልብ የምንመለከትበት መስኮት ነው። ሕዝቡ የሚዘምርለትን ምድራዊ ዙፋን እሱ ግን በዕንባ አልፎታል። ዛሬም ጌታ ወደ እኛ ሕይወት ሲገባ የሚፈልገው የላይ ላዩን ምስጋና ሳይሆን፣ "የመጎብኛችንን ዘመን" አውቀን በንስሐ እንድንመለስለት ነው።
የሆሳዕና ታሪክ እዚህ ጋ ወደ ጥልቁ ምስጢር ይገባል። ቤተ ክርስቲያናችን አምላክን እንደ "እብድ አፍቃሪ" ትመስለዋለች። ይህ ሲባል አምላክ ለሰው ልጅ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ የሚያደርገው ጥረት ከሰው ልጅ ምክንያታዊ አስተሳሰብ በላይ መሆኑን ለማሳየት ነው።
አንድ ንጉሥ በታላቅ የክብር ሰልፍ እየገባ፣ ሕዝቡ ሁሉ እያመሰገነው እያለ፣ እሱ ግን የሚያስበው ስለ ዙፋኑ ሳይሆን ለእነዚያ ለሚሰቅሉት ሰዎች ስለሚከፍለው ዋጋ ነው። አፍቃሪነቱ ራሱን እስከ መስጠት (እስከ ሞት) ያደረሰው ፍቅር ነው።
ጌታችን በሆሳዕና ዕለት ወደ ኢየሩሳሌም የገባው እንደ ተራ ንጉሥ ሊነግሥ ሳይሆን፣ ለወደደው ሕዝብ ሲል "ሊታረድ" ነው። ይህ ፍቅር ዓለምን ያስገረመና በምክንያት የማይገለጽ "መለኮታዊ ምስጢር" ተብሎ በአባቶች ይገለጻል።
የሆሳዕና እሑድ ፀሐይ ስትጠልቅ፣ የከተማዋ ድባብ በድንገት ይቀየራል። የእልልታውና የዝማሬው ድምፅ እየራቀ ይሄድና ታላቅ ዝምታ ይሰፍናል። ይህ ዝምታ ወደ ሰሙነ ሕማማት (የመከራ ሳምንት) መሸጋገሪያችን ነው።
በዚህ ወቅት በቤተ ክርስቲያናችን የሚታዩ ለውጦች ታሪኩን የበለጠ መሳጭ ያደርጉታል፦
የመስቀል መታቀብ፦ ካህናት መስቀል አይይዙም፣ ምእመናንም መስቀል አይሳለሙም። ምክንያቱም የመስቀሉ ክብርና ድል የተገለጠው ከትንሣኤ በኋላ ስለሆነ፣ በዚህ ሳምንት ትኩረታችን በመከራው ላይ ብቻ እንዲሆን ይደረጋል።
የመሳሳም መታቀብ፦ ሰዎች በሰላምታ ጊዜ አይሳሳሙም፤ ይህም ይሁዳ ጌታን በመሳም አሳልፎ የሰጠበትን የክህደት ምልክት ለማሰብና የሰላሙ ጊዜያዊነትን ለማሳየት ነው።
የግብረሕማማት ንባብና ጸሎት ስግደት፦ ሳምንቱ በሙሉ በመከራው ላይ ያተኮሩ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን ንባቦች (ግብረ ሕማማት) የሚደመጡበትና ምእመናን በስግደትና በጾም የሚተጉበት ነው።
ሆሳዕና የደስታ መዝጊያ ሳይሆን፣ ለታላቁ የፍቅር መሥዋዕትነት መክፈቻ ነው። ከሆሳዕና እልልታ ጀርባ የቀራንዮ ዝምታ አለ። ዛሬ ዝማሬያችንን አቁመን የጌታን ሕማማት ለመካፈል ልባችን ዝግጁ ነው?
ማጠቃለያ መልእክት የዕለቱ ትምህርት ጠያቂ ክፍል፦
"ሆሳዕና የፍቅር ወረራ ነው። ጌታችን ሁሌም እኛ በማንረዳው ፍለጋ ልክ እንደ 'እብድ አፍቃሪ' ሆኖ ወደ ልባችን ሊገባ ይፈልጋል። ነገር ግን ከሆሳዕና ዝማሬ በኋላ ወደሚመጣው የሕማማት ዝምታና ስግደት መከራና የመስቀል ሸክም አብረነው ለመጓዝ እንፈቅዳለን???? ዘንባባውን በግንባራችን ስናስር፣ ክርስቶስንና ፈቃዱን ቃሉንና ፍርዱን በልባችን አንግሠነው ወደ ሰሙነ ሕማማቱ የፍቅር ጉዞ እንግባ"።
0 Comments