አንድ ትውልድ ስለ ራሱ የሚሰጠውን የሰውነት ክብር እና በዚያም በጽድቁ ለመኖር በሚያስፈልገው ጀግንነት ይታነጽበት ዘንድ በአባቶቹ እውነት፣ እምነትና እሴቱ ሊቃውንቱ ሊሠሩት ይገባል፤ አለበለዚያ ግን ታሪኩም ትውልዱም ይከሽፋል!
የአንድ ሕዝብ የጀግንነት ታሪክ ልክ በመሬት ውስጥ እንዳለ፣ ዋጋውም እጅግ እንደከበረ ማዕድን ነው፤ በባለሙያዎች ተቆፍሮ ካልወጣ፣ ካልጸዳና ካልተቀራረጸ ለትውልድ ኃብት፣ ልማት ሊኾን እንደማይችል፤
በብዙ የጀግኖች ጀብድ የደለበ፣ የሰባና የታፈረ የታሪክ እሴትም እንዲሁ ከተቀመጠበት ማኅደሩ፣ ከተሸከመው ሐቁ፣ ከሠሪው ትርጉሙ፣ ለዘመኑ ከሚሰጠው ጭብጡ በደንብ ተበልቶና ተዘርዝሮ መሰጠት አለበት አለበለዚያ ለዚህኛው ትውልድ የሚሰጠው አንዳችም የጽድቅ ኃይል አይኖረውም፤ እንደውም ከሽፎ የሚያጠፋው ይኾናል እንጂ።
ይሁን እንጂ የታሪክ መክሸፍ የሚጀምረው ኾን ብለው የትውልዱን ወኔ ለመስለብና በባርነት የሚያሳድር ትንታኔ የሚሰጡ “አድርባይ” ሊቃውንት መድረኩን ሲቆጣጠሩት ነው።
እነዚህ ሊቃውንት የጀግኖችን መስዋዕትነት እንደ “ከንቱ እልቂት”፣ አርበኝነትን ደግሞ እንደ “ኋላቀርነት” እየተረጎሙ ትውልዱን በረቂቅ ትርክት ማምከን ይያያዙታል። በዚህ ጊዜ ታሪካቸው የሞተ በድን ቅርፊት ሲኾንባቸው እነርሱ(ትውልዱ) ደግሞ አልጫና ልባልባ ይኾናሉ።
በተለይ ልባልባና ይበልጡንም አድርባይ ሊቃውንት ታሪክን ሲጽፉት፣ የጀግንነት ጀብዱ፣ የጽድቅ ወኔው፣ ኩራትና ክብሩ ከውስጡ ተሰልቦ ይወጣል።
ትውልዱ በታሪኩ እንዲያፍርና በራሱ እንዲጠራጠር የሚያደርግ “የጥፋተኝነት ስሜት” በትምህርትና በስብከት ከእነዚሁ ልባልባና አድርባይ “ሊቃውንቱ” አፍ ይጋቱታል።
ጀግናን በሊቃውንት ትንታኔ፣ በሞራል ክለሳ እየከሰሱ ማኮሰስ መጨረሻው ልባልባ፣ አልጫ፣ ወኔቢስ፣ አድርባይ ትውልድ መፍጠር ነው።
እንዲህ ዓይነት ትውልድ ለገዛ ክብሩና እሴቱ የመቆም ድፍረት ስለሚታጣው፣ ለባዕዳን ትርክትና ለባርነት እጅ የሰጠ በራሱ ዘርና ትውልዱ ተስፋ አጥቶ፣ ቆርጦ በባርነት የሚያድር “የጃንደርባ” ማንነት ይላበሳል።
ይህ በሊቃውንት የሚከናወን “የመንፈስ ስልባ” ውጤቱ ማኅበራዊ ምክነት(መምከን) ነው። አባቶቹን የሚንቅ፣ የጀብድ ሥራቸውንም የሚኮንን፣ ጭራሽም “ከእነርሱ የተሻለ መንፈሳዊ ነኝ” ሲል የሚመጻደቅ፣ በታሪኩ የሚሸማቀቅና የራሱን እሴት እንደ ሸክም የሚቆጥር ወንድ፣ የአባወራነትንና የመሪነትን ኃላፊነት ለመሸከም ወኔው አይፈቅድለትም።
ከዚያ ይልቅ የሚቆምለት ክብር፣ ጠንካራ ስብዕናም ስለማይኖረው ምን ቢማር ማስትሬትና ዶክትሬት ቢኖረው፣ ሊቅና ሊቀሊቃውንትም ቢባል ማንም በመጣ ቁጥር የሚገዛው አስመሳይ፣ አድርባይ፣ አገልጋይ፣ ባንዳና ጃንደርባ የመኾን እድሉ ይሰፋል።
ዛሬ በዓለም ዙሪያ የሚታዩ “የከሸፉ ትውልዶች” የአርበኝነት እሳታቸው በሆዳደር ሊቃውንት “የሞራል ክለሳ” ስለጠፋባቸው የተገኙበት ውድቀት ነው። ታሪክን የሰለበ ትውልዱን ይሰልባል፤ ትውልዱን የሰለበ ደግሞ ሀገሩን ያመክናል!
ትውልዱን ከአልጫነትና ከባርነት ለመታደግ፣ የታሪኩን ምስጢር ለጀግንነት የሚፈቱ፣ የክብሩን ትርጉም ለጽድቅ የሚያመሰጥሩና የአባቶችን እውነት፣ እምነት፣ እሴት በትውልዱ ደም ውስጥ የሚያሰርጹ “አርበኛ ሊቃውንት” ያስፈልጋሉ።
የታሪክ ምስጢር ሳይፈታ ትውልድ አይገነባም፤ ትውልድ ደግሞ ወኔ ሳይታጠቅ ጽድቅን አይፈጸምም! “እፈጽማለሁ” ቢል እንኳ አስመሳይ አድርባይ የሚኾንበት እንጂ በተግባር በፈተና ወቅት የሚጸናበት ጠንካራ ሥረ-መሠረት ያለው ስብዕና አይኖረውም!
የሆዳደር አድርባዩ ሊቃውንት፣ በተለይም የታሪክ “አዋቂና ጸሐፊው” ክህደት የትውልዱን ተስፋ ይቆርጣል፣ የጥፋትና ሞቱንም መቃብር ይቆፍራል!
ስለኾነም ተጣሞ የተተከረውን፣ የሚተረከውን፣ የተጻፈውን ጽድቅ መፈጸሚያ ጠንካራ ስብዕና ይገነባ ዘንድ ባዲስ ብያኔ ወደ ትውልዱ ልብ ደምና ስጋው ማስረጽ ያስፈልጋል!
ታሪክ ይከሽፋል ወይ?
አዎን! የሀገሬ ታሪክ በሆዳደር ሊቃውንቱ ከሽፏል! ልባም ትውልድ ያፈራ ዘንድ ሊዘራ የተገባው በዓለም የታወቀው የጀግኖቻችን ታሪክ አልጫ፣ ልባልባና ጃንደርባ ያፈራ ዘንድ በሆዳደሩ ሊቃውንት ኾን ተብሎ ትርክቱ ተዛብቷል!
አንድም በአጉል መንፈሳዊነት የታጀሩ፣ ከአባቶቻችን በላይ “አዋቂ ነን” ሲሉ የታበዩቱ፤ የታሪክ ጥቅም ያልገባቸው ልባልባ አልጮቹ “የጦርነት ታሪክ ነው ያለን” ሲሉ በእነርሱ ወልካፋ የሞራል ሚዛን ኮንነው ያቀሉታል።
አዎን ታሪክም ይከሽፋል! በዚያም በከሸፈ የጀግኖች ታሪክም አስመሳይ፣ አድርባይ፣ ባንዳ፣ የእናት ጡት ነካሽ፣ አልጫ፣ ጃንደርባ ትውልድ ይወጣል!
0 Comments