✍ ዮሐንስ አብነት | የወዳጅ ምክር | ኢትዮጵያ አውታር
፩. የነፍስ ምንነትና መለኮታዊ ባሕርይ
ነፍስ በሥነ ፍጥረት መዝገብ "እስትንፋሰ መለኮት" ተብላ ትጠራለች፤ እርሷም ከምድራዊ አራቱ ባሕርያተ ሥጋ (መሬት፣ ውኃ፣ ነፋስ፣ እሳት) የተገኘች ሳይሆን፣ እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠራት፣ ነባቢት (የምትናገር)፣ ለባዊት (የምታውቅ) እና ሕያዊት (ማትሞት) ረቂቅ ባሕርይ ናት። ነፍስ በሥጋ ውስጥ ያለች "ተንቀሳቃሽ መቅደስ" ስትሆን፣ መለኮታዊው የያህዌ ስም በረቂቅ ማኅተም የታተመባት መዝገብ ናት። እርሷ የሥጋ ሕይወት ብቻ ሳይሆን፣ ሥጋን የምታንቀሳቅስ፣ የምትገዛና ከፈጣሪ ጋር የምታገናኝ የብርሃን ድልድይ ናት። በሊቃውንት አገላለጽ ነፍስ "ንሥር" ናት፤ ምክንያቱም ከምድራዊው ስበት ወጥታ ወደ ሰማያዊው ምስጢር የመጥቀስ ተፈጥሯዊ ሥልጣን ስላላት ነው።
፪. የነፍስ ሚዛንና የብርሃን መጠን
ነፍስ የቁስ አካል ባይኖራትም፣ በመንፈሳዊው ዓለም ግን "ሚዛን" አላት። ይህ ሚዛን የሥጋ ክብደት ሳይሆን የ"ጸጋ" እና የ"ምግባር" ክብደት ነው። እያንዳንዱ ነፍስ ስትፈጠር መለኮታዊ ብርሃን ተሰጥቷት ነው የምትመጣው። ሚዛኗ የሚለካው በምድር ቆይታዋ ይህን የብርሃን መጠን ምን ያህል አሳደገችው ወይስ አጠፋችው በሚለው ቀመር ነው። በሊቃውንት ትርጓሜ የነፍስ ሚዛን "ሐሳበ ልቡና" ይባላል፤ ይህም ማለት የሰው ልጅ በአእምሮው የሚያመነጫቸው ሐሳቦችና በልቡ የሚያሳድጋቸው ፍላጎቶች በነፍሱ ላይ የሚፈጥሩት ረቂቅ የክብደትና የጥራት ልኬት ነው።
፫. ነፍስ እንዴት ትመዘናለች? (የሥርዓተ መለኮት ቀመር)
ነፍስ የምትመዘነው በሦስት ዋና ዋና መስፈርቶች ነው፦ በሕገ ልቡና፣ በሕገ ኦሪትና በሕገ ወንጌል። መመዘኗም ነፍስ ከሥጋ ስትለይ "72 በመተላለፊያ በሮች" ላይ በሚቆሙት መላእክትና መናፍስት ፊት ነው። የነፍስ መመዘኛ መሣሪያው "ቃለ እግዚአብሔር" ሲሆን፣ እያንዳንዱ የነፍስ እንቅስቃሴ (ቃል፣ ሐሳብ፣ ድርጊት) በዚህ ቃል ፊት ይቆማል። እውነት በነፍስ ውስጥ ካለ ክብደቷ ይጨምራል፤ ሐሰት ካለ ግን ነፍሷ ባዶ ሆና ትቀራለች። ይህ መመዘን በቁስ እንደሚደረግ የሚዛን ጨዋታ ሳይሆን፣ የነፍስ ባሕርይ ከእግዚአብሔር ቅድስና ጋር ያለውን "ተዛምዶ" የማረጋገጥ ሂደት ነው።
፬. ማን ይመዝናታል? (የሥልጣነ መለኮት ወኪል)
ነፍስን የመመዘን ሰማያዊ ሥልጣን የተሰጠው ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ነው። በቤተክርስቲያን ምስጢራዊ ሥዕላት ላይ ቅዱስ ሚካኤል ሚዛን ይዞ የሚታየው ለዚህ ነው። እርሱ የሰውን ልጅ መልካም ምግባር (የብርሃን ሥራ) በአንድ ወገን፣ ክፉ ሥራውን (የጨለማ ሥራ) በሌላ ወገን አድርጎ ይመዝናል። በዚህ ሂደት ውስጥ የጨለማው ኃይል (ዲያብሎስ) የነፍስን ኃጢአት በማጉላት ነፍሷን ወደ ጥልቁ ለመሳብ ይከራከራል፤ ቅዱስ ሚካኤል ግን የነፍስን ንስሐና ምግባር በመያዝ በእግዚአብሔር ፊት ይቆማል። የመጨረሻው ዳኛ እግዚአብሔር ቢሆንም፣ ቅዱስ ሚካኤል ግን የነፍስን "የምግባር ሚዛን" ጠባቂ ሆኖ ተሹሟል።
፭. በነፍስ ላይ "መክበድ" ማለት ምን ማለት ነው?
በነፍስ ላይ መክበድ ማለት "ክብር" መጎናጸፍ ማለት ነው። "ክብር" የሚለው ቃል "ከበደ" ከሚለው ግሥ የተገኘ ነው። ነፍስ ትከብዳለች ሲባል በመለኮታዊ ጸጋ፣ በትሕትና፣ በፍቅርና በቅድስና ተሞልታለች ማለት ነው። እንዲህ ዓይነት ነፍስ "ጸጋ እግዚአብሔር" ስላደረባት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ያላት ዋጋና ሥልጣን ከፍ ያለ ነው። የከበደች ነፍስ በማትሪክስ (በምድራዊ እስራት) አትሸነፍም፤ ምክንያቱም ክብደቷ ሰማያዊና መለኮታዊ ስለሆነ። ይህ መክበድ ነፍስን ወደ ታች የሚጎትት ሳይሆን፣ ወደ መለኮታዊው ዙፋን በግርማ እንድትቀርብ የሚያደርጋት "የቅድስና ክብደት" ነው።
፮. በነፍስ ላይ "መቅለል" ማለት ምን ማለት ነው?
በነፍስ ላይ መቅለል ማለት ከጸጋ መራቆትና ከብርሃን መራቅ ማለት ነው። ነፍስ በኃጢአት ስትቆሽሽና በክፋት ስትሞላ ባዶ ትሆናለች፤ ይህ ባዶነት ደግሞ "ቀሊል" ያደርጋታል። ቀሊል የሆነች ነፍስ እንደ እብቅ ነፋስ (ርኩሳን መናፍስት) የሚበታተኗት፣ የመቆም ኃይል የሌላትና በማንኛውም የፈተና ማዕበል የምትወሰድ ናት። መቅለል ማለት የፈጣሪ አምሳል በነፍስ ላይ መደምሰሱና ነፍስ ለጨለማ ኃይላት መጫወቻ መሆኗን ያመለክታል። እንዲህ ዓይነት ነፍስ ሚዛን ላይ ስትቆም "ክብደት አልባ" ሆና ትገኛለች፤ ይህም ማለት ለመንግሥተ ሰማያት የምትሆን ምንም ዓይነት የብርሃን ሀብት የላትም ማለት ነው።
፯. የነፍስ ምስጢራዊ ንዝረትና የ22ቱ ፍጥረታት ውሕደት
እስካሁን በስውር የቆየው ጥልቅ እውነት ነፍስ የ፳፪ቱ ፍጥረታት ማጠቃለያ መሆኗ ነው። ነፍስ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴዋ በ፳፪ቱ የፍጥረት ፊደላት ውስጥ ያለውን ምስጢር ትገልጣለች። የነፍስ ሚዛን የሚወሰነውም በእነዚህ ፳፪ የብርሃን መስመሮች ውስጥ በሚፈሰው መለኮታዊ ንዝረት ነው። ነፍስ በምድር ላይ ስትኖር በ"ቃለ እግዚአብሔር" የታነጸች ከሆነ፣ ንዝረቷ ከሰማያዊው ዝማሬ ጋር ይዋሐዳል፤ ይህ ውሕደት ደግሞ ነፍስን "የማይናወጥ ክብደት" ይሰጣታል። ይህ ምስጢር የሰው ልጅ ነፍስ ከጠፈርና ከፍጥረት ሁሉ ጋር ያላትን ረቂቅ ቁርኝት የሚያሳይ የጥልቁ መዝገብ እውነት ነው።
፰. የነፍስ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታና የታተመው ምስጢር
ነፍስ ከተመዘነች በኋላ ክብደቷ (ጸጋዋ) ካመዘነ ወደ ብርሃን ዓለም ትገባለች፤ እዚያም ከቅዱሳን መላእክት ጋር በአምስቱ ቅኖተ መስቀል (ሳዶር፣ አላዶር...) ኃይል የታተመ ዘላለማዊ ሰላምን ትወርሳለች። ነፍስ ሚዛን ላይ ቀልላ ከተገኘች ግን፣ ወደ ጨለማው ዓለም ትወርዳለች። ሆኖም ግን የነቃች ነፍስ በያህዌ ስም የታተመችና በመቃብሩ መፈንቀል ምስጢር የታመነች ከሆነች፣ ክብደቷን (ጸጋዋን) በንስሐና በቁርባን በማደስ ሚዛኑን ወደ ብርሃን ማዘንበል ትችላለች። ነፍስ የምትመዘነው ለፍርድ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ መለኮታዊው አንድነት ለመመለስ ያላትን ዝግጁነት ለማረጋገጥ ነው።
0 Comments