አልጫ ትውልድ ከከሸፈ ታሪክ ይበቅላል


✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ

መገናኛ ብዙኃኑ፣ የመወያያ መድረኩም ትውልዱን ከእሴቱ ከአባቶቹ ታሪክና ትውፊቱ እንዲገናኝ ሳይኾን እንዲለያይ የሆዳደሩ ሊቃውንት ተባባሪ ናቸው! አልጫ ትውልድ የከሸፈ ታሪክ የሚግተውን ሲሰማ ይገኛል!

ትውልድ ከትውልድ፣ ወገን ከወገን፣ ወዳጅ ከወዳጅ፦ ተነጋግራችሁ መግባባት ሲያቅታችሁ ሁለታችሁን ያላስማማውን ነገር ግን አንድ ዓይነት የሚመስለውን ምናልባትም በልባችሁ የተዘራውን የታሪክ-እሴት ወደ ኋላ ሄዳችሁ ገምግሙ!

አንድ የታሪክ-እሴት ለሕይወትም ለጥፋትም ይዘራል! ተርጓሚው ከውስጡ ለክብር ለነፃነት አድርጎ ሲተረጉመው ለሕይወት ለነፃነት ይኾናል፤

አንድም በዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት ተመጻድቆ “በሚዛናዊነት” ሲያወላክፈው ደግሞ ለጥፋትና ሞቱ እንዲሰጥ ለባርነት ይኾናል።

አሁን፣ ዛሬ ባለንበት በዚህ ጊዜና ዘመን በመገናኛ ብዙኃን፣ በዜና ማሰራጫዎችና በዩቲዩብ መንደሮች የሚዘራው “የክሽፈት ዘር” በትውልዱ ሥነ-ልቦና ላይ የሚፈጽመው ጥፋት ከማንኛውም ወታደራዊ ወረራ የከፋ ነው።

እነዚህ መድረኮች ከሆዳደር ሊቃውንት ጋር በማበር ትውልዱን ከአባቶቹ አርበኛዊ ወኔና ከአባወራዊ ክብሩ ነጥለው “አልጫ” እንዲኾን ሌት ተቀን ይተጋሉ።

አትሞኙ! ይህ የሚኾነው በአጋጣሚ አይደለም! ኾን ተብሎ እንጂ!

በተለይም በታዋቂ ድራማዎች፣ አሰንግዶች በሚቀርቡባቸው የውይይት መድረኮች ላይ አባታዊ መሪነትን እንደ “ጨካኝ አምባገነንነት”፣ ቤተሰባዊ ሥርዓትን ደግሞ እንደ “ኋላቀር እስር ቤት” አድርጎ የመሳል ስልታዊ ዘመቻ እየበዛ መምጣቱን አስተውሉ።

ይህ በትውፊት ላይ የተነጣጠረ ጥፋት በተለይ የሴትነትን ወግ፦የሚስትነትንና የእናትነትን ክብር፤ እንደ “ባርነት” በመቁጠር ማኅበራዊ መሠረታችንን ይንድ ዘንድ ከታሰረበት የማርክሳውያን ልብ፣ እንዲጠመድ ወደ ተፈለገው የትውልዱ ጆሮ፣ በአዋቂዎቹ አፍ ተለቋል።

የሴቷን መገዛትና ማገልገል እንደ “ጭቆናና የበታችነት” በመፈረጅ፣ እናትነትንና የቤት እመቤትነትን እንደ ውርደት እንዲቆጠሩ በትረካዎች ይሠራባቸዋል።

🚨 የትውልዴ ልብ ላይ ዐዲስ ትርክት እየተጻፈ፣ በናላው ሰሌዳ ላይም የክሽፈ ታሪክ እየተሳለ ነው።

በዚህም ሳይገደቡ፣ በባልና በሚስት መካከል ያለውን አንድነትና ውሕደታቸውን የሚጠብቅበትን ተፈጥሮአዊ ልዩነት፣ የሥልጣን ተዋረድ በማጥበብ፣ ትዳርን ትውልድ የሚፈራበት የፍቅር ማዕከል ከመኾን ይልቅ የሥልጣን ሽኩቻ ያጨቀየው፣ ያቀዘቀዘው ሜዳ እንዲመስል ያደርጉታል።

ይህ “የእኩልነት” ጭንብል የለበሰ ዘመቻ፣ ቤትን የአንድነት መፍለቂያ ሳይኾን የጠብና የክስረት ጎጆ በማድረግ ትውልዱን ያለ አባትና እናት መሪነት አብነትም “መካን” ኾኖ እንዲቀር ይፈርዳል።

እነዚህ መገናኛ ብዙኃንና የመድረክ ሊቃውንት ትውልዱን ከታሪኩ በመለየት “አልጫ” አድርገው የሚያሳድጉት በወልካፋ ሚዛን በሚሰፍሩት የተዛባ የታሪክ ትንታኔ ነው።

እሴት ትውፊቱን እንደ ሸክም፣ አርበኝነትን እንደ ቂልነት፣ ቤተሰባዊ ኃላፊነትን ደግሞ እንደ ነፃነት ማጣት አድርገው በመስበክ ትውልዱን ከመጣበት እሴቱ በመለየት በቁሙ ያመክኑታል።

ስለዚህ ይህን የመገናኛ ብዙኃንና የሆዳደር ሊቃውንት የጥፋት ተባባሪነት በመረዳት፣ ትውልዱን ወደ ቀደመው የአንበሳ ግርማውና ወደ አባቶቹ የጽድቅ ፈለግ የሚመልስ አዲስ አርበኛዊ ትርክት መገንባት ለነገ የማይባል የህልውና ግዴታ ነው።

ወንድነትን በዐዲስ ማንነት መሳል፦ ፍዝ እንከፍነትን፣ ምስኪን ጃንደርባነትን ለትውልዱ ማስተዋወቅ፤ እንዲናፍቅ እንዲኖረውም ማሳየት፤ ትውልድ የመጣበትን የጀግንነትና የክብር ታሪክ ያለተረካቢ፣ ቀጣይና አቀጣጣይም ማስቀረት፣ ማቋረጥ፣ ማክሸፍም ነው።

ትውልዱ በገዛ ታሪኩ እንዲያፍር፣ በጀግንነቱ እንዲሸማቀቅና በ”ምስኪን ጃንደርባነት” ማንነትም እንዲረካ ሲደረግ፦

🚨 ታሪካዊው ሰንሰለት ይበጠሳል፤

🚨ትውልድ ከአባቶቹ፣ ከአያት ቅድማያቶቹ ይቆራረጣል፣

🚨 እነርሱን በማይመስል ጠባይ ይገለጣል፣

🚨 ስባሪ ሳንቲም የሚሰጠው ማንም ይጋልበዋል፣

🚨 እርሱም በሆዱ ተገዝቶ በባርነት የማደርን ውርደት፣ ጥፋትና ሞቱን የሚረዳበት ልብ የለውምና ልባልባ ነውና ባርነቱ በዚያ ይታተማል!

ትውልዱ አልጫ ኾኖ ስታዩ፦

ልቡ በጠንካራ ስብዕና እንዳይታነጽ፣ ጽድቅ በሚሠራበት እሴቱ እንዳይበለጽግ፣ በጀግንነትና በልበሙሉነት ለክብርና ለነፃነት እንዳይቆም ታሪኩን ማን እንዳከሸፈበት መርምሩ!

Post a Comment

0 Comments