የሐሰት ትርክት አጥፊነት ከውሸት ዜና እጅግ ይከፋል!

✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ

የውሸት ዜና ለጊዜው ሰሚውን ያሳስታል፤ እውነት ነው ብሎ የውሸት ዜና ይዘግባል። የታሪክ-እሴትን ግን ከእውነትና እምነቱ ከእሴቱም ለይተው ሲተርኩት ግን ታሪክ ሰንሰለቱ ይከሽፋል፣ ትውልድ ይጠፋል፣ ማኅበረሰብ ይመክናል፣ ሀገር ይፈርሳል!

የውሸት ዜና ጊዜያዊ ሐቅ(fact) መዛባት ነው። አንድን መረጃ በውሸት በመዘገብ(Fake News) በማቅረብ ሰሚውን ለጥቂት ጊዜ ግራ ሊያጋባ፣ ሊያስቆጣ ወይም ውሳኔን ሊያሳስት ይችላል።

እውነቱ ሲጋለጥ ግን የዜናው ኃይል አብሮ ይከስማል፣ ዘጋቢውም ለወደፊቱ ተአማኒነት ያጣል።

የሐሰት ትርክት ግን ከዜና በላይ ነው። እርሱ በትውልድ ልብ ውስጥ የሚተከል፣ ማንነትን የሚቀርጽና ሕዝብ ራሱን የሚመለከትበትን መነጽር የሚያጠለሽ ረቂቅ መርዝ ነው።

የታሪክ-እሴትን ከእውነትና ከእምነቱ ነጥሎ፣ በ”ሊቃውንት” ወልካፋ ሚዛን ሰፍሮ ለትውልድ ማቅረብ ማለት ትውልዱን በቁሙ መሰለብ፣ ለጥፋትና ሞቱ መዳረግ፣ ለባርነትም ማጋዝ ነው።

ይህ ትርክት አንዴ ልብ ውስጥ ከሰረፀ፣ ታሪካዊው የጀግንነት ሰንሰለት ይበጠሳል፤ ይህም ማኅበረሰቡን ወደ መመከንና ሀገርን ወደ መፍረስ ይነዳታል።

ለምሳሌ ያህል የሚከተሉትን ሦስት አውዳሚ የትርክት አቅጣጫዎች ማየት ይቻላል፦

አስረጅ ፩. የአባወራነትን ግርማ በ”ጭካኔ” መተርጎም፦

አባቶቻችን ቤተሰባቸውንና ርስታቸውን ለመጠበቅ ያሳዩትን አርበኛዊ ጽናትና ቆራጥነት፣ ዛሬ ያሉት ሆዳደር ሊቃውንት “አምባገነንነትና ጭካኔ” አድርገው ይተርኩታል።

🌟 የሐሰቱ ዜና፦ “አባት ልጁን መታ” ቢል፤

🚨 የሐሰቱ ትርክት ግን “አባትነት ራሱ የግፍ የበደልም መሣሪያ ነው” ብሎ ያነሳዋል። በዚህ ጊዜ ወጣቱ ትውልድ አባት የመኾንን፣ የመሪነትን፣ የጠባቂነትን፣ ትውልድን በሥነ-ሥርዓት የመቅረጽን ኃላፊነት እንደ ሸክም ወይም እንደ ወንጀል እንዲቆጥረው ይደረጋል።

በውጤቱም ትውልዱ ኃላፊነት የማይሰማው፣ ልጆቹ፦ ሥርዓትና ፈለጉን፣ የማይከተሉ የማያከብሩት፤ ምስኪንና ጃንደርባ ኾኖ እንዲቀር ያደርገዋል።

🌟 የሐሰቱ ዜና፦ ባል ሚስቱን በኃይል ተቆጣ፤ ቢል

🚨 የሐሰቱ ትርክት ግን፦ ባልነት “በዝባዥነት፣ ጨቋኝነት፣ በዳይነትም ነው” ብሎ ያመጣዋል። በዚህም ጊዜ ሚስቱን መምራት፣ መጠበቅ፣ መምከርና መገሰጽ የነበረበት፣ ኃላፊነትም ያለበት ወንዱ ሴቷን ራሷን፣ ትውልዷን ለምታጠፋበት “ምክረ-ሃሳቧ” በእኩልነት ስም እንዲተዋት ይኾናል።

በውጤቱም ትዳራቸውን፣ ቤታቸውን፣ ቤተሰባቸውን የሚያፈርስ መርዘኛ ሃሳብ በአሳቢነትና በተቆርቋሪነት ስም በእርሷ በኩል አስተዛዝኖ ገብቶ ይበጠብጣቸዋል፣ ያለያያቸዋል፣ ቤተሰባቸውንም ያፈርሰዋል።

፪. የሴትነትን ወግ በ”ባርነት” መተካት፦

እናትነትን፣ የሚስትነትን ክብርና ለቤት መታመንን እንደ “ግርድና” የሚስለው የሐሰት ትርክት፣ በባልና በሚስት መካከል ያለውን ተፈጥሮአዊ ውሕደት ይበጥሳል።

ይህ ትርክት ቤትን የትውልድ ማፍሪያ ማዕከል(መሠረት) መኾኑን አጥፍቶ “የፉክክር ሜዳ” ያደርገዋል። ሴቷ እናትነቷን እንደ ውርደት፣ ወንዱም አባትነቱን እንደ ሸክም እንዲቆጥረው ሲደረግ፣ ቤተሰብ ይፈርሳል።

ቤተሰብ ሲፈርስ ደግሞ ማኅበረሰቡ ይመክናል፤ ምክንያቱም በራሱ ታሪክና እሴት የሚያፍር ትውልድ ዘር የመተካት ወኔውና ተስፋው አብሮ ይሞታልና።

ለምሳሌ፦

🌟 የሐሰቱ ዜና፦ እርሷ ሥራ የላትም የቤት እመቤት ናት፤ ቢል

🚨 የሐሰቱ ትርክት ግን፦ የቤት እመቤቷ ደሞዝ በማይከፈልበት የቤት ውስጥ ሥራና እንክብካቤ “በነፃ”፣ ሕልሟን መስዋዕት አድርጋ ተበዘበዘች፤ ሲል የታሪክ-እሴቱን ትርክት ይመርዘዋል።

፫. አርበኝነትን በ”ሰላማዊነትና በመንፈሳዊነት” ጭንብል ማምከን፦

ለእውነትና ለክብር መቆምን እንደ “ዕብሪት”፣ ለግፍ አለመንበርከክን ደግሞ እንደ “የሰላም ጠንቅ” አድርገው የሚተነትኑ ሊቃውንት፣ ትውልዱን ለባርነት ያጩታል።

🌟 የሐሰቱ ዜና፦ ጠላት መጣ ሊል ይችላል፤

🚨 የሐሰቱ ትርክት ግን፦ ራስን ከጠላት መከላከል፣ መክደልም ስሕተት ኃጢያትም ነው፤ ብሎ ልብን ይሰልባል።

ይህ የትርክት ስልባ ትውልዱ የመጣበትን የጀግንነት ሰንሰለት አቋርጦ፣ በወኔቢስነት ለጃንደርብነት ትውልዱን አጋልጦ ይሰጣል።

የሐሰት ትርክት በትውልድ ልብ ላይ የሚፈጽመው “የእሴት ስልባ” ከማንኛውም የሐሰት ዜና ጥፋት በእጅጉ ይከፋል፤ ያይላልም።

ትውልዱ በራሱ እንዲጠራጠር፣ በአባቶቹ እንዲያፍርና ነፃነት ሕይወት በሌለበት ጃንደርባዊ ማንነት እንዲያርፍ የሚያደርገው ይህ በሆዳደሩ ሊቃውንት የሚጋተው “የከሸፈ ታሪክ” ነው።

ስለዚህ ትውልዱን መታደግ የሚቻለው፣ የታሪክን ምስጢር ለጀግንነት የሚፈቱና የአባወራነትን ክብር የሚመልሱ አዲስ አርበኛ ሊቃውንት ሲነሱ ብቻ ነው። ታሪክን የሰለበ ትውልዱን ይሰልባል፤ ትውልዱን የሰለበ ደግሞ ሀገሩን ያመክናል!

በመኾኑም ከሐሰት ዜና ይልቅ የሐሰትን ትርክት እንድንጠነቀቅ የሚያስገድዱን ዋና ዋና ምክንያቶች፦

፩ኛ ማንነትን ስለሚሰልብ፦ የሐሰት ዜና መረጃን ሲያዛባ፣ የሐሰት ትርክት ግን “ማንነትን” ይመርዛል። አንድ ወጣት በአባቶቹ ታሪክ እንዲያፍርና በወንድነቱ እንዲሸማቀቅ ሲደረግ፣ ለጽድቅና ለክብር የመቆም ወኔው ተሰልቦ “ፍዝ እንከፍ” እና “ምስኪን ጃንደርባ” ኾኖ እንዲቀር ያደርገዋል።

፪ኛ የታሪክ ሰንሰለትን ስለሚበጥስ፦ የሐሰት ዜና ለጊዜው ያሳስታል፤ የሐሰት ትርክት ግን ትውልዱ የመጣበትን የጀግንነትና የክብር አውታር ያለ ተረካቢና ያለ ቀጣይ አቀጣጣይ በማስቀረት የታሪክ ቅብብሎሹን ያቋርጣል። ይህ ደግሞ ትውልዱን ካለፈው ክብሩ ነጥሎ በሆዳደርነት አስመሳይ፣ አድርባይና ባንዳ አድርጎ ለባርነት ያመቻቸዋል።

👉 ታሪኩ ትውልዱም ይከሽፋሉ!

፫ኛ ማኅበረሰብን ስለሚያመክን፦ በእሴቱና በታሪኩ እንዲጠራጠር የተደረገ ትውልድ፣ ለነገ ተስፋ ስለማይኖረውና የአባወራነትን ኃላፊነት እንደ ሸክም ስለሚቆጥረው፣ ዘር የመተካትና በጠንካራ ስብዕና በታነጸ ትውልድ ጠንካራ ቤተሰብ የመመሥረት ፍላጎቱ አብሮ ይከስማል። ይህ “ሥነ-ልቦናዊ መካንነት” ደግሞ ሀገርን ከውስጥ ያፈርሳታል።

የ፬ኛ የሊቃውንቱ የክህደት መሸሸጊያ ስለኾነ፦ ልባልባና አድርባይ ሊቃውንቱ የታሪክን ምስጢር ለጀግንነትና ለክብር ለሉዓላዊነትም ከመፍታት ይልቅ፣ በ”ዘመናዊነትና በመንፈሳዊነት” ጭንብል ትውልዱን የሚሰልቡት በዚህ ረቂቅ የትርክት መርዝ ነው።

የሐሰት ዜና አካልን ለጊዜው ሊጎዳ ይችላል፤ የሐሰት ትርክት ግን ትውልዱ ጽድቅ የሚፈጽምበት፣ ስብዕናው የሚታነጽበት ልቡ ይሰልባል።

ስለዚህ ትውልዱ በከሸፈ ታሪክ ወደ አልጫነት አዘቅት ከመውረድ ለመታደግ፣ ይህን የልባልባና የሆዳደር ሊቃውንት የትርክት ሴራ ነቅቶ መመከትና የአርበኛውን የአባወራነውንና የቤተሰቡን አኩሪ ታሪክ መልሶ መትከል የህልውናችን መሠረት ይኾናል ማለት ነው!

Post a Comment

0 Comments