✍ ሔኖክ ኃይለገብርኤል | አባወራ | ኢትዮጵያ አውታ
እንደ ጀርመን በታሪኩ እንዲያፍር፣ በብሔራዊ ስሜቱ እንዲሸማቀቅ የተደረገ በዚያም ጀግንነቱንና ክብሩን እንዲጥል የተገደደ፣ የእርሱ የነበረውን ሁሉም ለባዕዳን እንዲሰጥ የተኮነነ፤ ይህም ጽድቅ ነው ተብሎ የተሰበከለት ማን አለ?
(ፕረሺያ ጀርመን፣ ፖላንድ፣ ራሺያ፣ ዴንማርክ እና ሌሎችንም የሰሜን አውሮፓ ሀገሮች ጠቅልሎ የያዘ በመናዊ የወታደርና የአስኳላ ትምህርት ሥርዓት የታወቀ “ጀርመናዊ” ግዛት ነበር)
ታሪክን ዝም ብሎ የትናንት ትውስታ አድርገው የሚቆጥሩ ሰዎች፣ በትረካ አማካኝነት ትውልድን የመስለብ ረቂቅ ጥበብ አይታያቸውም።
ጀርመን በአንድ ወቅት የፕረሺያ (Prussia) የጀግንነት እሴት መፍለቂያ፣ የቆራጥነት በተለይም የዲሲፕሊን ተምሳሌት ነበረች(ከዲስፕሊን ጋር ተገናኝቶ በአባወራ ውይይታችን አንስተናት እናውቃለን)።
ዛሬ ግን ያ “የአንበሳ ግርማና መንፈስ” በታሪካዊ የጥፋተኝነት ስሜት ካራ ተሰልቦ፣ ሀገሪቱ በገዛ ልጆቿ ላይ፣ በሴቶች ልጆቿ ላይ የሚደርስን ወንጀል እንኳ የሚፈጸመውን ግፍ እንኳ መከላከል ወደማትችልበት የሞራል ሽባነት ወርዳለች።
ፕረሺያን በታሪክ መነጽር ተመልከተን፣ በትውፊት ስልክ ደውለን ስለ ነበራቸው ጀግንነትና ስለ ሀገር አጥርነት ብንጠይቅ የምናገኘው መልስ፣ ዛሬ በጀርመን አደባባዮች ከሚታየው፣ በወንዶቻቸው ልብ ውስጥ ከተሰነቀረው ወኔ-ቢስነት ጋር ሲነጻጸር እጅግ ያሳዝናል፤ ያስለቅሳልም።
አንድን ማኅበረሰብ ለመስለብ የግድ የጦር መሣሪያ አያስፈልግም፤ ታሪኩን እንዲጠላና በጀግኖቹ እንዲያፍር ማድረግ፣ በክብሩ እንዲሸማቀቅ ማድረግ ብቻ በቂ ነው።
ጀርመናዊው ትውልድ ባለፉት አባቶቹ “ስህተት” ምክንያት “ዘረኛ” ወይም “ጨካኝ” ተብሎ እንዳይፈረጅ ካለው ከፍተኛ ፍርሃት የተነሳ፣ እውነተኛ ወንጀልን እንኳ በድፍረት መኮነን፣ ወንጀለኛንም መቅጣት የማይችል “ልባልባ” ኾነ።
የሀገሪቷ መሪዎች ማንኛው ብሔራዊ ሕብረትና አንድነት በሕዝቡ ውስጥ የሚያቀጣጥል ክስተት መጥቶ እስኪያልፍ ድረስ ጭንቅ ውስጥ ይገቡ ነበር። ለምሳሌ፦ የጀርመን የእግርኳስ ብሔራዊ ቡድን ሲጫወት።
ምንም ዓይነት ሕዝቡን የሚያቀራርብ፣ ብሔራዊ ስሜት የሚያቀጣጥል፣ አንድነቱንም የሚያሳልጥ ሀገራዊ አጀንዳ የማይፈልጉ ኾነ።
ወንጀለኞች ሴቶችንና ሕጻናትን አጥቅተው በዳኛ ነፃ ሲለቀቁ፣ ከሕጉ ፍትሐዊነት ይልቅ፣ የአጥቂዎቹ “ጉዳት” የሀገራቸው የታሪክ ጠባሳ ነው የሚያሳስባቸው።
ይህ ጤናማ ያልኾነ ርሕራሔም ኾነ የጥፋተኝነት ስሜት ትናንት ለተፈጠረው “ሰሕተት” ማስተሰረያ (ይቅር ማስባያ) የዛሬውን ትውልድ አሳልፎ የሚያሰጠው የመንፈስ መውደቅ ስልበትም ነው።
የጀግናውን ግርማ በመስበር ጀግናው እንደ ተራ ኃጢአተኛ ብቻ እንዲታይ ማድረጉ፣ ትውልዱ ስለ አባቶቹ የሚሰማው፣ የሚያውቀው፣ የሚረዳው ክስና ውርደት ብቻ እንዲኾን አድርጎታል።
ዛሬ በጀርመን የሚታየው “የወንድ” መጥፋት፣ የዚሁ የታሪክ ስልባ ውጤት ነው። አንድ ወንድ ልጁንና ሚስቱን ከጥፋት፣ ሀገሩን በሸፍጠኛ ሊቃውንት ከተነጣጠረባት የትውልድ ጥፋት የመጠበቅ “የአንበሳ ወኔው” ከተሰለበ፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነቱ አብሮ ተሰልቧል።
ይህ የታሪክ ክለሳና ብረዛ ትውልዱን መካን አድርጎታል። ጀርመን በቁጥርም ኾነ በመንፈስ እየመከነች ያለችው፣ ትውልዱ ስለ ነገ ተስፋ እንዲኖረው የሚያደርገው የጀግንነት የክብርም እሳት-ወኔው ስለጠፋ ነው።
የጀርመን ውድቀት ለሌላው ዓለም ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው። ታሪክህን በ”ሞራል ክለሳ” ሰበብ ለጠላት አሳልፈህ ከሰጠህ፣ መጨረሻህ እንደ ጀርመን በራስህ ታሪክ እያፈርህ መመከን ነው።
🚨 የጀርመን ቤተክርስትያን ጀግኖቿን በመስለብ ሂደት (የኢትዮጵያዋንም በዚሁ ትይዩ ታዘቧት፤ እስክመጣላት)
የጀርመን ቤተ ክርስቲያን (በተለይም የፕሮቴስታንቱ ዘርፍ) በአርበኛዊ ታሪክ ኩነናው እና በትውልዱ የሥነ-ልቦና ስልባው ውስጥ የነበራት ድርሻ እጅግ ከፍተኛና መሠረታዊ ነበር።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ቤተ ክርስቲያኗ የጀርመናውያን “የነፍስ ሐኪም” ኾና ከመቅረብ ይልቅ፣ ትውልዱን በታሪኩ እንዲያፍርና እንዲሸማቀቅ የሚያደርገውን የ”የጋራ ጥፋተኝነት” ትርክት በግንባር ቀደምትነት ስታስተጋባ ቆይታለች።
ጦርነቱ እንዳበቃ በ1945 ዓ.ም. የጀርመን የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች “የእስታትጋርት የጥፋተኝነት መግለጫ” የተባለውን ሰነድ አወጡ።
በዚህ ሰነድ ቤተ ክርስቲያኗ በጀርመን ሕዝብ ስም “ለዓለም ሁሉ ጥፋተኞች ነን” የሚል ይፋዊ ኑዛዜ አቀረበች። ይህ ኑዛዜ ምንም እንኳ በወቅቱ የሞራል ንጽሕና ፍለጋ ቢመስልም፣ በሂደት ግን ትውልዱ ስለ አባቶቹ ጀግንነትና አርበኝነት እንዳይናገር፣ ይልቁንም ሁልጊዜ “አንገቱን ደፍቶ” እንዲኖር የሚያደርግ የዘላለም የውርደት ቀንበር ኾነ።
ከጦርነቱ በኋላ የጀርመን ቤተ ክርስቲያን ብሔራዊ ስሜት ወይም አርበኝነት፦ ኃይለኝነት፣ ጀግንነት፣ ድፍረት፣ ጥንካሬ፤ የሚሉ እሴቶችን ከወንጌል ጋር የሚጋጩ “ጣዖታት” አድርጋ መሳል ጀመረች።
የፕረሺያ የጀግንነት እሴቶችና ለሀገር የመሞት ወኔ “በፈጣሪ ላይ ከማመ፣ በወንጌል ካለመታነጽ” ጋር ተያይዞ ቀረበ። ይህም ትውልዱ ለሀገሩና ለክብሩ በጀግንነት የመቆም ድፍረት እንዳይኖረው፣ ይልቁንም ወኔ-ቢስ የኾነ የጃንደርባ አገልጋይነሰት መንፈሳዊነት እንዲላበስ አደረገው።
ጀግናን ማኮሰስና የጀግንነትን ግርማ መስበር፣ ትውልዱ ቀና ብሎ እንዳይሄድ ማስጎንበስ፣ ዘወትር ለዘለዓለም ይቅርታን መለመን፣ ማላዘን በቤተ ክርስቲያኗ ስብከት ውስጥም ሰርጎ ገባ።
ልብ በሉ!
ቤተ ክርስቲያኗ “በክርስቶስ ዘንድ አይሁዳዊ ወይም የግሪክ፣ ወንድ ወይም ሴት የለም” የሚለውን ቃል ያለ አውዱ በመውሰድ፣ የጀርመንን ልዩ ማንነትና ታሪካዊ እሴት ማጥፋት ጀመረች።
“ክርስቲያን ከኾንክ ለጀርመን ሳይኾን ለዓለም ሕዝቦች ሁሉ ነው ማሰብ ያለብህ፤ ምክንያቱም እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ነንና” የሚለው ሲሰሙት “ደሰ የሚል” ነገር ግን የማይኖር የማያስኖር ስብከት፣ ትውልዱን ለገዛ ሀገሩና ለገዛ ወገኑ የማይቆረቆር አልጫ፣ የመጣውን ሁሉ የሚያገለግል ታማኝ ጃንደርባ አደረገው።
የጀርመን ቤተ ክርስቲያን “ኃይል፣ ጀግንነት፣ ድፍረት፣ ቆራጥነት” የሚሉትን ቃላት ከጥፋትና ከኃጢአት ጋር በወንጌልም ካለመታደስ ጋር አያይዛ መሳል ጀመረች።
በታሪክ ድርሳናት ውስጥ የነበሩት አርበኛ ነገሥታትና የፕረሺያ ጀግኖች “ትዕቢተኞችና ደም አፍሳሾች” ተደርገው ተሰበኩ። በምትኩ “ለስላሳ፣ ቀለስላሳ፣ ኮሳሳ፣ ፈዛዛ፣ የማይጋደልና ሁልጊዜ ይቅርታ የሚጠይቅ” ሰብአዊነት እንደ ብቸኛ ክርስቲያናዊ ምግባር ቀረበ።
ቤተ ክርስቲያኗ ለተፈጸመው “ስሕተት” የሚኾን ንስሐን “ታሪክን ወደ መጥላትና ወደ መሸማቀቅ” ቀየረችው። “ጀርመናዊ መኾን ማለት የአባቶቻችንን፣ የአያት ቅድማያቶቻችንን የጥፋተኝነት ሸክም መሸከም ማለት ነው” የሚለው ትርክት በመቅደሱ ውስጥ ጸደቀ።
ይህ ደግሞ ትውልዱ ስለ አባቶቹ ጀግንነትና ኩራት እንዳይሰማው፣ ይልቁንም እነርሱን ባሰበ፣ ታሪካቸውን ባስታወሰ ጊዜ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር የሚያደርግ የሥነ-ልቦና እስራት፣ ስልበት፣ መኮላሸትም ኾነ።
የጀርመን ቤተ ክርስቲያን አርበኝነትን እንደ ጣዖት፣ ጀብደኝነትንም እንደ ሰይጣናዊ ኃይል፣ አርበኛንም አጋንንት እንደተጣባው በመሳል፣ ትውልዱን ከነበረበት የጀግንነትና የክብር ማማ ላይ አውርዳ አፈረጠችው።
ዛሬ ጀርመን “ወንድ”፦ ጀግና፣ ልባም አጥታ የምታለቅሰውና በገዛ ታሪኳ የምትሸማቀቀው፣ ቤተ ክርስቲያኗ አባታቸው የሰጣቸውን የወኔውን እሳት “በታሪካዊ ጥፋተኝነት” ስም አጥፍታ የውርደቱን አመድ ስላከናነበችው ነው።
ታሪክን በሃይማኖት ሰበብ መበረዝ፣ መጨረሻው ትውልድን መግደልና ሀገርን ማስመከን ነው! ትውልዱን ቤተመንግሥት የገባው ሁሉ የሚነዳው፣ የሚያዘው እንከፍ፣ ምስኪን እርሱም ለማንም የሚያደገድግ አስመሳይ፣ አድርባይ፣ ስልብ ጃንደርባ ኾነ! አስረጅ፦ ጀርመን በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ብትመድብም ትውልዱ መውለድ የማይፈልግ፣ የዘር ፍሬውን የሚበጥስ፣ ሴቷም ማኅጸን የምታስወጣ ኾኑ! በቁም መሞት!
በዚያም የቤተክርስትያኗ ድርሻ እጅግ ከፍተኛ ነበር! ሊቃውንቱ ትውልድ የሚድንበትን የአርበኝነት የጀግንነትና የክብር ታሪክ ኮንነነው፤ ጃንደርብነቱን የሚያጸናውን(ማንንም፣ ጠላቱንም ጭምር አደግድጎና አጎንብሶ የሚያገለግለውን) እንከፍ ምስኪንነት ጋቱት!
ገና ነን፤ ወደ ኢትዮጵያ “የጀግኖቹ ማማ፣ የጠንካራ ስብዕናው ፋፋ” አልደረስንም! አንድ ሌላ አርበኛዊ ሀገር እንዴት ተሰልቦ ጃንደርባ ኾኖ ከምድረ ገጽ ሊጠፋ እንደደረሰ ልንገራችሁ።
0 Comments