አንድ ሕዝብ የጀግንነት፣ የክብርና የነፃነት ታሪክ እያለው ትውልዱ አልጫ፣ ልባልባ፣ ጃንደርባ ከኾነ፤ ጥፋቱ የታሪኩ ሳይኾን የተርጓሚዎቹ የሊቃውንቱ ነው!
ይህ ጥያቄ የሊቃውንቱን ስልታዊ የኾነ “ትውልድን የመስለብ” ረቂቅ መንገድ የሚመረምር ነው። ሊቃውንቱ የጀግኖችን ታሪክ በቀጥታ አይክዱም፤ ይልቁንም “በትርጓሜ” እና “በሞራል ስም” ወኔውን ሰልበው አልጫ (Demoralized) ያደርጉታል እንጂ።
ሊቃውንቱ የጀግኖችን ታሪክ በወልካፋ ሚዛን በመስፈር ትውልዱን የሚያከሽፉትበትን በዚያም በሆዳደርነት፣ በአስመሳይነትና በአድርባይነት ላደሩለት ምርኮ ያመጡበታል።
🌟 አስቀድመው ጀግንነትን ከጽድቅና ከሞራል ጋር በማላተም፣ የአባቶችን ቆራጥነት እንደ “ጭካኔና ኋላቀርነት” በመሳል፣ ሰልፋቸውን ከጦረኝነትና ከጠበኝነት ጋር በማያያዝ ትውልዱ በታሪኩ እንዲያፍርና በውሸት የሞራል የበላይነት ተገፍቶ ወኔው እንዲሰለብ ማድረግ ነው።
በዚያም ከታሪኩ የጀግንነትን ወኔ፣ የጽድቅን ቆራጥነትና የክብርን ኃይል በትርጉማቸው ነቅለው ያወጡታል። በዚህን ጊዜ ትውልዱ የሚያገኘው ደረቅ ሐቅ ብቻ ኾኖ ይቀራል፤ ታሪኩን ያውቀዋል፣ ይዘፍነዋል፣ ይገጥመዋል፣ ይለብሰዋል፣ ይተውነዋል እንጂ “በጣቱ ጫፍ ንክት” አያደርገውም፦ አይኖረውም!
ስለኾነም ትውልዱ “ታሪክ አለን፣ እኛ የአድዋ ዘማች ልጆች ነን፣ አድዋን ባመት ባመት እንዘክራለን...” ይላል እንጂ ፎቶም እየተነሳ ለታይታ ለቅብጠት ይለጥፋል እንጂ “እኔ የታሪኩ አካል ነኝ” ብሎ አይነሳም።
ይህ ደግሞ ትውልዱን ለባርነት የሚያመቻች፣ ለነገሠው ሁሉ አጎብዳጅ፣ የታሪክ መረጃ እንጂ በእርሱ ላይ የተተከለ ወኔ የሌለው ተራማጅ ትውልድን ይፈጥራል።
🌟 በቀጣይነት ደግሞጨየሽንፈትን ሥነ-ልቦና በጀግኖቹ ታሪክ ውስጥ መዝራት ነው። ሆዳደር የኾኑት ወይም የባዕዳንን ትርክት ቀጂና አሳላፊ የኾኑት ሊቃውንት የጀግንነቱን ታሪክ ትውልዱ በአጉል መንፈሳዊነት ወይም ዘመናዊ ሞራላዊነት ስም እያየ እንዲሸማቀቅበት ያደርጋሉ።
ለምሳሌ፦
👉 የጀግኖችን መስዋዕትነት እንደ “ከንቱ እልቂት” መተርጎም፤
👉👉 ይህ በትውልዱ ደምና ደምስር ውስጥ ሲሰራጭ በጀግንነት ለጽድቁ መሞት ከንቱ ሞት የኾነበት፣ ከዚያ ይልቅ በሰላምና በጤና እድሜ ጠግቦ የሚኖርበት የባርነት መንፈስ ይሠለጥናል።
👉 የአባቶችን አርበኝነት እንደ “ኋላቀርነትና ጭካኔ” መሳል፤
👉👉 ይህ በአእምሮ ሰሌዳ ላይ ሲሳል ድንበርን፣ ቤትን፣ ቤተሰብን ያለመጠበቁ ጅልነት ዘመናዊነት፣ በባዕድ ሲመዘበሩ፣ ሲበረበሩና ሲደፈሩ ደግሞ ርህራሄ ይባላል።
👉 ለሀገር መቆም እንደ “ጠባብነት” ይታያል፤
👉👉 በዚህ ዕይታ ቤት የለሽ፣ ቤተሰብ የለሽ፣ ድንበር የለሽ መኾን “ሰፊነት፣ አቃፊነት” inclusive ይኾናል።
👉 ለክብር መሞትን ደግሞ እንደ “ቂልነት” ማቅረብ፤
👉👉 ተመሳስሎ፣ አመሳስሎ፣ ተሸነጋግሎ መኖር ወግ ይኾናል። ክብራቸው ጠፍቷልና አንድም ጠፍቶባቸዋልና፦ ወንዱ ለቃሉ የማይገዛ አስመሳይ አታላይ ሲኾን ሴቷ ሰውነቷን እንደ እንሰሳ ማንም ይጋልበዋል።
እንዲህ ያለው ትንታኔ መገለጫዎቹ ከላይ እንደዘረዘርኳቸው ቢለያዩም፤ መጨረሻቸው ግን አንድ ነው ልብአልባ፣ ክብረቢስ፣ አልጫ፣ ጃንደርባ የኾነ ትውልድ ማፍራት!
🌟 ለባርነት የሚዳርግ፣ በባርነት የሚያሳድር “ሰላማዊነትን” መስበክ ሌላኛው አስመሳይ አድርባዩ ታሪክን የሚያከሽፍበት ትርጉም ነው።
ሊቃውንቱ ጽድቅ ይሠሩበት ዘንድ ባልታነጹበት እሴቱ ኾን ብለው የ”ሰላም፣ የፍቅርና የትኅትና” አስማሪ፣ ሰባኪ፣ ጸሐፊ፣ ተርጓሚ፣ ተራኪ፣ ኮማኪ ይኾናሉ።
በተለይ እነዚህን ቃላት ያለ ዐውዳቸው በመጎተትና በመለጠጥ ትውልዱ ከአባቶቹ ታሪክ በሰማው፣ በተማረውና በተቀበለው ትውፊት ለገዛ ክብሩና እሴቱ መሟገቱን፣ መታገሉን፣ መጋደሉን እንደ ኃጢአት እንዲቆጥረው ያደርጉታል።
በዚያም ለጽድቅ የሚጨክንበት፦ መልካሙን የሚፈጽምበት፣ ልኩን የሚያስተካክልበት፣ ተገቢውን የሚተገብርበት፣ ውቡን የሚስልበት ወኔው ይሰለባል፤ ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት ባይ ጃንደርባም ይኾናል!
ሀገር በጠላት ሲጠፋ፣ እውነት ስትገፋ፣ እምነትና እሴት ሲረክሱ፣ ንጹሐን ተገፍተው ተጥለውም ሲረሱ “ዝምታ” ጽድቅ፣ ማላዘንና መነፋረቅም የበለጠው እንደኾነ የሚሰብኩ ሊቃውንት የባርያ ፈንጋዩ ወገን ተባባሪዎችም ናቸው።
አዎን! ወንድሞቼ ታሪክም ይከሽፋል!
እዚህ ላይ የፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሥራ የኾነውን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” መጽሐፍ እናስታውሳለን።
በዚህ መጽሐፋቸው እንዲህ ይላሉ፦
መክሸፍ የምለው አንድ የተጀመረ ነገር ሳይጠናቀቅ ወይም ሳይሳካ እንቅፋት ገጥሞት መቀጠል ሳይችል ዓላማው ሲደናቀፍና በፊት ከነበረበት ምንም ያህል ወደፊት ሳይራመድ መቅረቱን ነው።
የአንድ ሕዝብ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ታላቅ የነበረ ሕዝብ የነበረው፣ የታወቀው፣ የሚታወቀው የጀግኖች ታሪኩ ከእሴቱ ተለይቶ እንዲከሽፍ፣ እንዳይቀጥል እንዲመክን የሚደረገው በተለይ በሆዳደሩ ሊቃውንቱ (የታሪክ አዋቂ ነኝ) ባዩ ነው።
ትርክቱን ትውልድ በጀግንነት፣ በኩራት ለነፃነት ከሚሠራበቱ እየነጠሉ በአጉል ዘመናዊነትና መንፈሳዊነት ሲለጥጡት፤ ታሪኩን የሚቀበል፣ በእርሱ የሚኮራ፣ ለጽድቅና ለክብር በጀግንነት የሚቆም ትውልድ ይጠፋል።
ትናንትን ከዛሬ የሚያስተሳስርበት ሰንሰለቱ ይበጠሳል፣ ራስ ጠልነት ይነግሣል፣ አስመሳይ አድርባይነት ይወደሳል፣ ባንዳነት ያሸልማል፣ የእናት ጡት ነካሽነት ያሾማል።
መቼ?
ታሪክ የከሸፈለት!
ትውልዱን ከአልጫነት ለማውጣት ታሪኩ-እሴቱን በእውነትና በእምነት የሚተረጉሙ፣ ትውልዱን ለክብር በጀግንነት የሚያቆሙ፣ ምስጢሩን ጠንካራ ስብዕና የሚገነባበት አድርገው የሚፈቱ፣ አርበኛ ሊቃውንት መነሳት አለባቸው።
ታሪክ-እሴቱን የሰለበ የሕዝቡን ልብ፣ ወኔ ይሰልባል፤ ሕዝቡን የሰለበ ደግሞ ትውልዱ ይጠፋል፣ ማኅበረሰቡ ሀገሩም ይመክናል።
አንድም ሕዝቧ ከታሪክ-እሴቱ ተጥሎባት ልባልባ የኾነባት ሀገር ትውልዷ ጠፊ፣ ማኅበረሰቧም መካኝ፣ እርሷም ፈራሽ ነች!
0 Comments